ፋና ብሮድካስቲንግ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመለት

0
679

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት በቀለ ሙለታ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 13/2011 የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ከምስረታው ጀምሮ ተቋሙን የመሩትን ወልዱ ይመስልን በመተካት ሥራ መጀመራቸው ታወቀ።

በዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል በሃላፊነት ሲሠሩ የቆዩት በቀለ፣ ከሰኔ 2006 ጀምሮ የኢዜአ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ላለፉት ሦስት ወራት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድጋሚ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ውስጥ በቦርድ ሰብሳቢነት ሲሠሩ ቆይተዋል። ሹመታቸውን ተከትሎ ከኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጆች ጋር ባሳለፍን ማክሰኞ ትውውቅ አድርገዋል።

በተቋሙ ውስጥ ሲነሳ የቆየውን የሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል ያሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢዜአ ሠራተኛ፣ በድርጅቱ ውስጥ ካለው ያረጀ የኤዲቶሪያል አሠራር አለማላቀቃቸውም ከሚተቹባቸው ድክመቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። በዜና አገልግሎቱ ውስጥም ከፍተኛ የሠራተኞች ፍልሰት መኖሩን እኚህ ሠራተኛ ይናገራሉ።

‹‹በ2006 ከተቀጠሩ 62 ወጣት ጋዜጠኞች ውስጥ ከ40 በላዩ ድርጅቱን ለቀው ሄደዋል፣ እሳቸውም ይህንን አስተካክለው ቢሄዱ መልካም ነበር›› ያሉት ግለሰቡ ‹‹ድርጅቱን ከሥራ አስፈፃሚው ቁጥጥር ነፃ በማውጣት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጠራ በማድረግ የሠሩት ሥራ እንደሚያስመሰግናቸው ተናግረዋል።
ከ1982 በፊት ደርግን ለመጣል በተደረግው ትግል ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ራዲዮ ፋና ከ1987 በኋላ የአራቱ አውራ ፓርቲዎች የልማት ድርጅቶች በጥምረት የገንዘብ መዋጮ በማድረግ መስርተውታል።

ኢፈርት፣ ጥረት፣ ቱምሳ እና ወንዶ በተባሉት አራቱ የኢሕአዴግ የልማት ድርጅቶች የአክሲዮን ባለቤትነት የሚተዳደረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የራሱን የቴክኖሎጂ፤ ጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት የማማከርና የማሰልጠን አገልገሎት እየሰጠ ሲሆን በስሩ ከ 1ሺ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል።

ላለፉት 75 ዓመታት ለሀገሪቱ የዜና ምንጭ በመሆን ሲያገለግል የቆየው ኢዜአ፣ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ከ38 በላይ ቅርንጫፎች በመክፈት በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ፋና ቴሌቪዥን የሙከራ ስርጭቱን 2009ዓ.ም የጀመረ ሲሆን ከታህሳስ 2010 ጀምሮ መደበኛ የፕሮግራም ስርጭቱን ጀምሯል። በሬዲዮ አገልግሎቱም ኤፍ ኤም 98.1 ጨምሮ 11 ማሰራጫ ጣቢያዎችን በክልል ከተሞች በመክፈት በ8 ቋንቋዎች አገልገሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በብቁና በበቂ የሰው ኃይል እንዲደራጅ የራሱን ገቢ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ ተቋሙን እንደ አዲስ ለማቋቋም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት መንግሥት ከሚመድብለት በጀት በተጨማሪ ማስታወቂያ መሥራት፣ በህትመት ሚዲያ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር ሥራ ላይ በመሳተፍ ገቢውን በማሳደግ ተወዳዳሪ ሙያተኞች ቀጥሮ ተልዕኮውን ለመወጣት እንደሚያስችለው ከወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድጋሚ መቋቋሙ የሚታወስ ነው።

የቀድሞውን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወልዱ ይመስልን እና አዲሱን ሥራ አስፈጻሚ በቀለ ሙለታን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here