“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
መከባበር ወሳኙ የማኅበራዊ ትስስር ምንጭ ነው፤ ደግሞም በሰውነት ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ግለጽ ነው። በአንጻሩ በሰዎች መካከል መስፈርት አውጥቶና መደብ ለይቶ በሚደረግ የአክብሮት ልዩነት የተነሳ ሁሌም ችግር ይፈጠራል። ለሰው ልጅ የሚገባው ክብር የትኛውንም ቅድመ ሁኔታ መጠየቅ የለበትም። በእርግጥ በምግባር የደከሙና እኩይ ሥራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ይኖራሉ፤ ከእነዚህ ጋር አብሮ መውረድ ተገቢ አይደለም። ስለዚህ በቦታቸው ይቀመጣሉ፤ ሰው እንደመሆናቸው ግን እንደዛም ሆኖ ክብርን አይነፈጉም።
እዚህ ላይ አለቃ ገብረ ሀና አሉ ወይም አደረጉ የሚባለውን ነገር አስታወስኩ። አለቃ ከአንድ ባላባት ቤት ትልቅ ድግስ ተጠሩ። እርሳቸውም ለአለባበሳቸው ብዙም ሳይጨነቁ ወደድግሱ ቦታው ያቀናሉ። ገና ከመግቢያቸው ላይ ግን በአለባበሳቸው የተነሳ ዘቦቹ አትገቡም ብለው በንቀት አባርረው መለሷቸው።
አለቃ ብልህ ነበሩና ወደቤታቸው ሄደው ያማረውን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ ድግሱ ተመለሱ። ሲመለሱ አስቀድሞ ሰድበው ያበረሯቸው ዘቦች አሁን እጅ ነስተው ግቡ አሏቸው። አስተናባሪዎቹም ጎንበስ ቀና ብለው አስተናገዷቸው። ታድያ ገበታ ሲቀርብ አለቃ ከእንጀራና ወጥ እያነሱ ልብሳቸውን ይቀቡት ጀመር።
ይሄንን ያዩ ሰዎች ደንግጠው ምነው ቢሏቸው፤ ‹እኔ መች ተጠራሁ! የተጠራው ልብሴ ነው። ይኸው! ልብሴን እያበላሁት ነው› አሉ ይባላል። አልተሳሳቱም!
ሰዉን ለማክበርና መብቱን ለመጠበቅ ሌላ መስፈርት አያስፈልግም። ለዛ ነው የሴቶች ነገር ሲነሳም፣ ‹ሴት እናትህ ናት፣ እህትህ ናት፣ ልጅህ ናት…› እያሉ ማባበልን የምንቃወመው። ለዛ ነው ሰው ብሔሩ ተጠርቶ፣ የእገሌ ብሔር ስለሆነ ቅድሚያ ይሰጠው ሲባል ቅር የሚለን። ስለዛም ነው እነ እገሌ የባለሥልጣኑ ዘመድ ስለሆኑ በልዩ ሁኔታ ይስተናገዱ ሲባል ደስ የማይለን። ለዛም ነው ዛሬ ላይ የምናየው ቀውስ እንዲህ ማባሪያ አጥቶ የተገኘው።
ሴት ልጅ ሰው ናት። መብቷ ሊከበር የሚገባው እናት፣ እህት ወይም ልጅ ስለምትሆንና ስለሆነች አይደለም፤ ሰው ስለሆነች ነው። ይህን ከልባችን ማኖር ብንችል የሴት ልጅ ጾታዊ ጥቃት የሰው ልጅ ሰብአዊ መብት መደፈር እንደሆነ በተረዳን ነበር።
በሴቶች ላይ መድሎን የሚፈጽሙና ጥቃትን የሚያደርሱ ሰዎች፣ በእናታቸው ወይም በእህታቸውና በሴት ልጃቸው ላይ ያንን አያደርጉ ይሆናል። ግን በሌላው እናት፣ እህት ወይም ልጅ ላይ ጥፋት ያደርሳሉ። እንግዲያው የየትኛውም ወንድ እናቱ፣ እህቱ ወይም ሴት ልጁ የተጠበቁ አይደሉም ማለት ነው።
ይህ ሊቀረፍ የሚችለው በአንድ መንገድ ነው፤ ሴት ልጅ በተሰጣት ማኅበራዊ ኃላፊነት መጠን ሳይሆን በሰውነቷ ስትከበር። ክብር ለሰው ልጆች ሁሉ!
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014


