የሄፓታይተስ ወረርሺኝ

0
1121

ሄፓታይተስ በመባል የሚታወቀው ጉበትን የሚያጠቃ በሽታ በወረርሺኝ መልክ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አሳውቆ ነበር። ካንሰርን ከመሳሰሉ ለማከም ከፍተኛ ወጪን ከሚጠይቁ በሽታዎች ተርታ የሚመደበው ይህ ገዳይ በሽታ የተለያዩ የቫይረስ ዝርያዎች ያሉት ነው።

በሽታውን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ተመራማሪዎች ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ እስከ አሁን ግን ምንም ዓይነት በሽታውን ጨርሶ ማጥፋት የሚያስችል ዘዴን ማግኘት አልቻሉም። በበሽታው የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ መቀነስ ቢቻልም፣ ዘንድሮ ግን በአስገራሚ ሁኔታ የወረርሺኝ ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቋል።

የሄፓታይተስ ወረርሺኝ ሲከሰት አሁን የመጀመሪያ ባይሆንም፣ በዚህ ሠለጠነ በሚባለው ዘመን መሆኑ ተመራማሪዎችን አስደንቋል። ይባስ ብሎ በአዳጊ ልጆችና ሕፃናት ላይ በብዛት መከሰቱ ነገሩን ልዩ እንዳደረገው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ አድርገው የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዉታል። ወረርሺኙ የተከሰተው ሠሞኑን በኮንጎ እንደተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ አፍሪካ ውስጥ ወይም እንደ ኮሮና እስያ ውስጥ ሳይሆን አውሮፓ ውስጥ መሆኑም ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ሆኗል።

እስከ አሁን አንድ ሕፃን ብቻ በበሽታው ሕይወቱን አጥቷል የተባለ ሲሆን፣ ሕመሙ ታይቶባቸው በሕክምና ላይ ከሚገኙትም 10 በመቶ ያህሉ የጉበት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን በመጥቀስ ተቋሙ የወረርሺኙን ድንገተኛነትና አሳሳቢነት ለማስረዳት ሞክሯል። የሕክምና ባለሙያዎችንና የዘርፉ ተመራማሪዎችን ግራ ያጋባው የዚህ ወረርሺኝ መንስኤ እስከ አሁን በምርመራ ባይረጋገጥም፣ ‹አዴኖ ቫይረስ› የሚባል ተዋህስ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

ሪፖርቱ እስከወጣበት የሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት ድረስ በአውሮፓ ውስጥ ባሉ 12 አገራት የሚገኙ 170 ሰዎች ላይ መከሰቱ የተመዘገበ ሲሆን፣ በየቀኑ ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚሄድ ታውቋል። 10 በመቶ የሚሆኑት የጉበት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት በተለያየ እድሜ ክልል ያሉ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ከአንድ ወር ጨቅላ እስከ 16 ዓመት የሆናቸው አዳጊዎች ናቸው። በበሽታው ከተያዙት አዳጊዎችም አብዛኞቹ ከ10 ዓመት በታች ሲሆኑ፣ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑም በርካታ መሆናቸው ተመዝግቧል።

የሄፓታይተስ ወረርሺኝ ከተገኘባቸው 170ዎቹ መካከል 114ቱ እንግሊዝ ውስጥ፣ 13ቱ ስፔን፣ 12ቱ እስራኤል፣ 11ዱ አሜሪካ ፣ ስድስቱ ዴንማርክ፣ አምስቱ አየርላንድ፣ አራቱ ኔዘርላንድ፣ አራቱ ጣሊያን፣ ኹለቱ ኖርዌይ፣ ኹለቱ ፈረንሳይ፣ አንዱ ሮማኒያና ሌላ አንድ ቤልጅየም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው ተብሏል። ሕይወቱ ያለፈው ሕፃንን ማንነትም ሆነ እድሜን ግን የዓለም ጤና ድርጅት ከመናገር ተቆጥቧል።

የሳንባ መቆጣት የሚያስከትለው ይህ የሰሞኑ ወረርሺኝ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተከስቶ የተገኘበት ቁጥር አነስተኛ ነው ተብሎ መናቅ እንደሌለበት የተጠቆመ ሲሆን፣ በልጆች ላይ ያልተለመደ በሽታ በመሆኑ አሁን ባህሪውን የመቀየሩ ምክንያት እስኪታወቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተነግሯል።

ስለወረርሺኙ የመጀመሪያውን ጥቆማ የሰጠችው ስኮትላንድ ስትሆን፣ ባለፉት ኹለት ወራት ብቻ በ17 ሕፃናት ላይ በሽታውን ማግኘቷን አሳውቃለች። በዓመት ከአራት የማይበልጥ ሕመምተኛን ታስተናግድ የነበረችው ይህች አገር፣ በኹለቱ ወራት ብቻ ከሦስት እጥፍ በላይ ታማሚዎችን ማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ሕፃናት መሆናቸውም ነገሩን ግራ አጋቢ አድርጎታል።

በሁሉም አገራት የተከሰተው የሄፓታይተስ ወረርሺኝ አይነት በጣም አደገኛ በመሆኑ ተመራማሪዎችን ስጋት ላይ እንደጣለ ተጠቁሟል። ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ በመባል የሚታወቁ የሄፓታይተስ ቫይረስ አይነቶች ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑንም ማወቅ ተችሏል።
ታማሚዎቹ ሕፃናት ክፉኛ ጉበታቸው የተጎዳ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት የሄፓታይተስ አይነቶች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ታውቋል። በሽታው በተለያዩ አገራት ቢከሰትም መንስኤው በትራንስፖርት አማካኝነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ተላልፎ ስለመሆኑም ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተገኘ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

የበሽታው ስርጭት የተከሰተው በምን ምክንያት ወይም ከምን ላይ ተነስቶ እንደሆነ እስከ አሁን የታወቀ ነገር የለም ያሉት ተመራማሪዎቹ፣ በአካባቢ አማካኝነት ይሁን በመድኃኒትም ሆነ ምግብን በመሳሰለ በሌላ ሳቢያ ይከሰት አልታወቀም ብለዋል። በተለያዩ አገራት ያሉትን ታማሚዎች መረጃ አቀናጅቶ በመመርመርም፣ ምንም ታማሚዎቹንና የበሽታውን ስርጭት የሚያቆራኝ ምክንያት አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

መንስኤው የኮቪድ ክትባት ይሆናል የሚባልን መላምት ለመፈተሽ ሞክረውም አብዛኞቹ ታማሚዎች ምንም ዓይነት ክትባት ያልወሰዱ ናቸው ብለዋል።

አዴኖ ቫይረስ የተሰኘው ተዋህስ ለበሽታው መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀር በርካቶች ቢገምቱም፣ የዚህ ቫይረስ ዝርያዎች በሕፃናት ላይ የሄፓታይተስ በሽታን ሲያመጡ ታይቶ ስለማይታወቅ ነገሩን አስገራሚ አድርጎታል። ነገር ግን ከ170ዎቹ ታማሚዎች ውስጥ 74ቱ ላይ ይሄው አዴኖ ቫይረስ ስለተገኘባቸው መንስኤው እሱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል። 18ቱ ደግሞ ታይፕ 41 የተባለው የቫይረሱ ዝርያ የተገኘባቸው ናቸው ሲሉ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል።

አዴኖ ቫይረስ የሚባለው ዝርያ የሆኑ 50 አይነት ቫይረሶች ሰዎችን የሚያጠቁ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የመተንፈሻ አካልን፣ ዐይንን ወይም የምግብ መፍጫ አካላትን በመጉዳት የሚታወቁ ናቸው። የአሁኑ ግን ጉበትን የሚያጠቃ እንደመሆኑ የተለየ ስለሆነባቸው ተመራማሪዎቹን ግራ አጋብቷል።

ቫይረሱ ከሄፓታይተስ ጋር ግንኙነት የሚኖረው አጋጣሚ ቢኖርም በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተጎዳባቸው ሕፃናት ላይ እንደሚዘወተር ይታወቃል። ከሄፓታይተስ ጋር ግንኙነት የሌለው ታይፕ 41 የተሰኘው የቫይረስ ዝርያ ተቅማጥ፣ ማስመለስና ትኩሳትን ጨምሮ የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ ነው።

አሁን በአውሮፓ እየተስፋፋ የሚገኘው ሄፓታይተስ በሽታ መንስዔው አዴኖ ቫይረስ ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢገመትም ኹሉንም ሊያስማማ አልቻለም። አሁን ለምን ተስፋፋ የሚለውና ሕፃናት ላይ ለምን አተኮረ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልተቻለም። ይህ የሆነው ከጊዜው አጭርነትና ከተገኘ ማስረጃ አነስተኛነት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ ሌላ መላምታቸውን ያስቀመጡም እንዳሉ ተመዝግቧል።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ወዲህ ሕፃናቱ ነፃነታቸውን ስላገኙ ሊሆን ይችላል ያሉ መኖራቸው ታውቋል። ይህን የመሳሰሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ቢኖሩም፣ የአዴኖ ቫይረስን የመሰለ ጠንካራ ሐሳብ ያቀረቡ የሉም ማለት ይቻላል። ይህም ቢሆን ግን ከትችት አልዳነም። ቫይረሱ የተገኘባቸው ሕፃናት በአጋጣሚ ዝርያው በጣም ተላላፊ ስለሆነ ተገኘባቸው እንጂ፣ ያን ያህል ከሄፓታይተስ በሽታ ጋር የሚያቆራኘው ሳይንሳዊ ምክንያት የለም ይላሉ። ከዚህ ይልቅ የተለያዩ በሽታዎች ቅንጅት ሊሆን ይችላል ብለው ግምታቸውን የሚያስቀምጡም አሉ። ከዛም ባሻገር የኮቪድ (SARS-CoV-2) እና የአዴኖ ቫይረስ ቅልቅል ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ስለወረርሺኙ የተለያየ ሐሳብ ቢቀርብም የዓለም ጤና ድርጅት ለውሳኔ ከመቸኮል ይልቅ ተጨማሪ ምርመራና ሥራ ይፈልጋል ብሏል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለውን መረጃ የማሰባሰብ፣ የማጠናቀርና የማጥናት እንዲሁም የተገኘን መረጃ የማሰራጨትና ሕዝብን የማሳወቅ ተግባር በስፋት መሠራት እንዳለበትም ተጠቁሟል። የበሽታው መንስኤ ከታወቀ በኋላ ለማከምም ሆነ መከላከያውን ለማዘጋጀት ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል።

የሄፓታይተስ ቫይረስ ጉበት እንዲጎዳ በማድረግ ለከፍተኛ ሕመም የሚዳርግ ሲሆን፣ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ በስተቀኝ ከጎድን በታች ሕመም መሰማት፣ መገጣጠሚያ ቦታዎች ሕመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የሽንት መጥቆርና አነስተኛ ትኩሳት በታማሚዎች ላይ የሚታዩ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው። የተለመደው የሄፓታይተስ በሽታ አልኮልን በማብዛት አልያም መድኃኒትን መውሰድና በመሳሰሉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here