የኢትዮጵያዊነትን ትርጉም እንድንጠይቅ ያደረገን የእሴቶች መሰበር ነው

0
1209

ሰላም ዓለሙ
የኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት የቦርድ ኃላፊ

ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት በተቋም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመሠረት የሆነው በ1984 ነበር። በወቅቱ ይህን ድርጅት ለመመሥረት ኅብረት ከፈጠሩት መካከል የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ጄነራል ጃገማ ኬሎ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ፣ ዮዲት እምሩ፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ዶክተር ፀሐይ ብርሃነሥላሴ እንዲሁም አፈ ንጉሥ ሀጎስ ተወልደ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በኋላም ድርጅቱ በ2004 በአዲስ መልክ መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ አድርጎ ተቋቁሟል።

በ2013 መስከረም ወር ላይ ነው ይህ ድርጅት በኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ እንቅስቃሴዉን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የቀጠለው። ኢትዮጵያዊ ሥነምግባር፣ መተሳሰብ፣ አገር ወዳድነት እንዲሁም አካታችነት እሴቶቼ ናቸው የሚለው ኢትዮጵያዊነት ድርጅት፣ አንድነቷን ያስጠበቀችና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተጎናጸፈች ኢትዮጵያን የማየት ርዕይ አለው።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዲሁም የድርጅቱን የቀደሙና ቀጣይ ሥራዎችን በሚመለከት ጥያቄዎችን በማንሳት ከድርጅቱ የቦርድ ኃላፊ ሰላም ዓለሙ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ቦርዱን ምን ያህል ጊዜ አገለገሉ? መጀመሪያስ ሲቀላቀሉ የነበረዎት ስሜት ምን ይመስል ነበር?

መደበኛ ሥራዬ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የተቀላቀልኩት ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት፣ ድርጅቱን ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የመጡ ጊዜ ነው። ከዛ ጀምሮ የቦርድ ሰብሳቢ ሆኜ እያገለገልኩኝ ነው።

ኃላፊነቱ ከባድ እንደሆነ አስብ ነበር። በወቅቱ ብዙ የቦርድ አባላት የሆኑት ሰዎች ከውጪ የመጡ ነበርና፣ ተደጋጋሚ ስብሰባ ሲያደርጉ፤ ሁሉም ሰላም ትሁን ብለው መረጡኝ።

ከዚህ በፊትም በእርግጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁሞ ስለመሠራት አስብ ነበር። ከእኛ ጋር አብሮ የሚሠራ አንድ የሥራ ባልደረባችን አለና እንዲህ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማቋቋምና የመሥራት ፍላጎት ነበረን። እሱም አሁን እኛ ጋር የቦርድ አባል ነው።

‹ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?› የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ የሚነሳበት ጊዜ ላይ ነን። በሺሕ ዘመናት የሚቆጠር እድሜ ባላት አገር ላይ ወደኋላ ተመልሶ ይህን ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ያለን ምንድን ብለው ያምናሉ?

ኢትጵያዊነትን መተርጎም በጣም ይከብዳል። በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊነት በአጭር ቃል የሚገለጽም አይደለም፣ ብዙ ነገሮችን የያዘ ነው። በአንድ ወቅት እንደውም አፄ ኃይለ ሥላሴ የተናገሩትን መጥቀስ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው ተብለው ተጠይቀው ለውጪ ዜጎች ሲያስረዱ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠርና ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ያስፈልጋል ብለዋቸው ነበር። እና ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ሲቻል ነው ሰው ኢትዮጵያዊነትን መረዳት የሚችለው።

እንደ አገር የሚያስተሳስሩን እሴቶች አሉን። ጀግንነት፣ አምላክን መፍራት፣ ሰው ማክበር፣ መቻቻል የመሳሰለውን መጥቀስ ይቻላል። ሁሉም እንዳለ ሆኖ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ከሀምሳ ዓመታት ወደዚህ ትርክቶች እየተቀየሩ መጥተዋል።

ይህም ምንድን ነው፣ የምዕራብያውን አስተዳደር መቅዳትና ያንን መተግበር ይታያል። ያ ጎድቶታል ብዬ አስባለሁ፤ እንደ ድርጅትም እሱን ነው የምናምነው። መሪዎች ያንን ያደረጉት ለክፋት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ብዙ ችግሮችን ይዞ መጥቷል። አሁንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ ላይ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በደንብ ያለመረዳት ችግር እየተፈጠረ ነው። ያም አሁን ላሉና እየተባባሱ ለመጡ ችግሮች ቀዳሚ ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ።

እንዳሉት በኢትዮጵያ በጥቅሉ እሴቶች እየጠፉ ነው በሚለው ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። መፍትሄ ለማግኘት የችግርን ምንጭ ማወቅ ተገቢ እንደመሆኑ፤ የስብራቱ መንስኤ ምን ይመስልዎታል? ማኅበሩ ይህን እንዴት መጠገን ይቻላል ብሎ ያምናል?

እነዚህ ነገሮች በትውልድ ቅብብሎሽ የመጡ ቢሆኑም፣ አሁን በወጣቱ ትውልድ ግን ጎልቶ ይታያል። እንደሚታወቀው ትምህርት የሚገኘው ከትምህርት ቤት፣ ከቤት፣ ከማኅበረሰብ እንዲሁም ከእምነት ተቋማትና ከመሳሰለው ነው። ነገር ግን ትምህርት ቤቶች ደግሞ ጉልህ ሚና መውሰድ አለባቸው፤ ቤተሰብም እንደዛው።

እነዚህ ሁሉ ባለድርሻዎች ተቀናጅተውና አንድ ሆነው ከሠሩ ይጠገናል፣ ይቀየራል ብዬ ነው የማስበው። የእኛ ማኅበርም ይህን ለመጠገን የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናትና በማስጠናት የተለያ መድረኮች እንዲዘጋጁ የማመቻቸት ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል ብሎ ያምናል።

በዚህ እንግዲህ ሁሉም ድርሻ ይኖረዋል፤ መንግሥትም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም፣ የሲቪል ማኅበራትና የተለያዩ ድርጅቶች በዚህ ሥራ ላይ ተሳትፈው መሥራት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ። እና ይህ ሲሆን በአጭር ጊዜ ነገሮችን መቀየር ይቻላል።

በትምህርት ካሪኩለም ኢትዮጵያዊነትን ስለማካተት በተለያዩ ቃለመጠይቆች ሲነሳ እንሰማለን። በምን መልኩ ነው ያንን ማድረግ የሚቻለው?

አስቀድሞ እንዳልኩት ኢትዮጵያዊነትን ለመተርጎም በጣም አስቸጋሪ ነው። ኢትዮጵያ የተገነባችው በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እሴት ነው ብለን እናምናለን።

በትምህርት ስርአት ውስጥ ይህን ለማካተት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት የምንላቸው የጀግንነት፣ ፈጣሪን የመፍራትና ጥሩ ጥሩ እሴቶቻችንን በትምህርት ስርዓቱ ማካተት እንችላለች። እንዲሁም ያሉንን የተለያዩ አገር በቀል እውቀቶች ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ የትምህርት ስርዓቱ አካል እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቃል። የምዕራቡን ብቻ ይዘን የምንጓዝ ከሆነና የራሳችን ባህልና እውቀት ትተን የእነሱን ብቻ ይዘን ከሄድን፣ አሁንም ችግር ይፈጠራል።

እንዲሁም የሥነ ምግባር ትምህርቶችን መስጠት ያስፈልጋል። አሁን ላይ የጥንትና የቆየ ሥልጣኔአችንንም እያጣን ነውና ያለነው፣ እሱንም በዚሁ ማካተትን ነው ያሰብነው።

የሲቪክ ማኅበራት በብዙ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። ግን በተግባር ከሚታየው አንፃር ምን ታዘባችሁ? አቅማቸውን ምን ያህል እየተጠቀሙ ነው ትላላችሁ? እየተጠቀሙስ ካልሆነ ችግሩ ምንድን ነው?

የሲቪክ ማኅበራት ብዙ ዓይነት ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ ከእኛ ከኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ውጪ ያሉ ሌሎችም ድርጅቶች አሉ። እኔ የምመክረው ሁሉም በተበታተነ መልኩ ሳይሆን በቅንጅት ሥራ ሠርቶ በአንድ ጊዜ ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ እንቅስቃሴ ቢኖር ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ሁሉም በየራሱ ለየብቻው ከሚሮጥ፣ አቅምና እቅዳቸውን አስተባብረው፣ የተወሰነ ሀብት በጋራ አሰባስበው ለአገር የሚጠቅም ነገር ቢሠራ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። እስከ ዛሬ ያለውን ነገር ግን ብዙም ለመገምገም አልችልም።

ትልቁ ችግር ሊሆን ይችላል አንድ ሆኖ አስተባብሮ የመሥራት ችግር ነው። እኛም እንደ ሲቪክ ድርጅት ብዙ ችግሮች አሉብን። የሰው ሀብት ሊሆን ይችላል፤ ሌላም አለ። እናም ያለንን አስተባብሮ ለአገር የሚጠቅም ነገር ቢሠራ ለውጥ ይመጣል ብዬ ነው እኔ የማምነው።

የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ማኅበሩ በሚፈልገው ጊዜ ሊተባበሩ ፈቃደኛ ሆነው እንደነበር ይታወሳል። ድጋፍ እየተደረገላችሁ ነው? በምትጠይቁትስ መልስ ታገኛላችሁ?

የሰላም ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የትምህርት ተቋማት ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። እንደዛው ያነጋገርናቸው ተቋማትና ግለሰቦች አሉ። አብረን እንሠራለን፣ ከጎነችሁ ነን የሚል ነገር አለ።

ግን እስከ አሁን የእኛም ድርጅት ገና በመቋቋም ላይ ስለሆነ፣ ሰፊ ነገርም ስለሚጠይቅና ብዙ ነገሮችን ማየትም ስላለብን እኛም ገፍተን ወደ ሥራው አልገባንም። እነሱ ግን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸውልናል። አንዳንዶቹ ተቋማት እንደውም የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ሂደት ላይ የደረስንባቸው አሉ።

አዲስ አበባ ላይ ካደረግነው ትውውቅ በኋላ አባላትን በመሰብሰብ ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው። የቴሌግራም ቡድን አለን፣ የተለያዩና ብዙ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው። ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነን።

ቀድሞ የፖለቲካ ርዕዮት ነበር፤ በኋላ ብሔር ከዛ ደግሞ አሁን ሀይማኖት አጀንዳ ሆነው በልዩነቶች መለያየት እየሰፋ መጥቷል። ማኅበሩ ትውልድን እያሰበ የሚሠራ እንደመሆኑ ምን ተስፋ ይታየዋል? ተስፋንስ እውን ለማድረግ ትውልድን በምን መልክ መቅረፅ ያስፈልጋል?

ብዙ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ኢትዮጰያዊ የሆኑ የጋራ እሴቶቻችንን አጉልቶ በማሳየት፣ በትምህርት፣ በሥነምግባር፣ በሞራል ወጣቱን መቅረጽ ያስፈልጋል፤ በኢትዮጵያዊነት ማንነት። እንደ እኔ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፤ ግን ቶሎ ይቀየራል ብዬ ነው የማምነው።

አገር በቀል እውቀቶች በስርዓተ ትምህርት እንዲካተቱ በማድረግ፣ ወጣቶችን በማነቃቃትና ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዲያውቅ ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ ሊመጣ ይችላል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ምን ያህል ተስፋ ጥላችኋል? ምንስ ስጋት አላችሁ?

የምክክር መድረኮች መካሄዳቸው በጣም ጥሩ ነው። እንደ ድርጅትም እንዲህ ያሉ የምክክር መድረኮች ለውጥ ይመጣሉ ብለን እናምናለን። የተለያዩ ችግሮች ካሉና የሚፈጠሩ ከሆነም፣ በመነጋገር መፍታት ይገባል። ቅድሚያ ግን የሕዝብ ጥያቄ ነው መታየት ያለበት የሚል እምነት አለን።

እናም አዎን በምክክር ኮሚሽኑ ላይ ተስፋ እናደርጋለን፤ ደግሞም የምናምንበት ነው። ግን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱም መፈታት ይኖርባቸዋል፤ የሕዝብን ጥያቄ ነው ማስቀደም የሚገባው።

ኮሚሽኑ ታምኖበት ነውና የተቋቋመው በእምነት ሥራቸውን ይሠራሉ ብዬ ነው እንደ ግለሰብም እንደ ድርጅትም የማምነው። በእምነት መሥራት ነው ያለብን፣ የሚጠቅመንም የሚገባንም ያ ነው ብለን እናምናለን። እንዳልኩት ችግር ካለ በመነጋገር መፍታት ነው፤ እንጂ ገና ለገና ይህ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት መቀመጡ አግባብም አይመስለኝም። እምነት ተትሎባቸዋል፤ እንዲሁም ሕዝብም የመረጣቸው ስለሆኑ፣ ተስፋ አድርጎ በመጠበቁ መቀጠል ያስፈልጋል ባይ ነኝ።

ማኅበሩ በ1984 ተመሠረተ፣ ዳግም በ2004 በአዲስ መልክ ቅርፅ ያዘ። በ2013 ደግሞ ፈቃድ አውጥቶ በኢትዮጵያም መቀመጫ አግኝቷል። ብዙ ማኅበራት ለውጥ መጣ የተባለ ሰሞን ነበር ከውጪ ወደ አገር ቤት የገቡት። ኢትዮጵያዊነት ወደ አገር ቤት ለመመለስ ለምን ዘገየ? በሰሜን አሜሪካ በነበረበት ጊዜስ ምን ምን ሥራዎችን ሠርቷል?

የለውጡ ጊዜ ነው የመጣው። ከዚህ በፊትም ወደ ኢትዮጰያ መጥቶ፣ እንቅስቃሴው ተጀምሮ የቀረበት ምክንያት አለ። በወቅቱ የነበሩ የአስተዳደር ችግሮች ነበሩ። ኢትዮጵያዊነትን እንደውም አብልጠው ይቃወሙ የነበረው፣ የብሔር ፖለቲካ ይራመድ ስለነበር ለእኛም እንቅፋት ይሆናል፣ ችግር ይፈጥርብናል ብለው አስበው ሊሆን ይችላል፤ ብዙም አይደግፉትም ነበር። በዛም የተነሳ እዚህ እንዲከስም ተደርጓል።

አሁን ለውጡ ከመጣ በኋላ የዛሬ ሦስት ዓመት ነው የመጣነው። ግን በሰው ኃይልና በመሳሰለው ችግር የተነሳ ወደ ሥራ ቶሎ አልገባንም። እንጂ ሦስት ዓመቱ ወደኢትዮጵያ ገብቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ።

ውጪ በነበረው ቆይታ ብዙ ሰፋፊ ሥራዎችን ይሠራ ነበር። አንድ ጥሩ የተሠራ፣ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ሰነድ የሥራ መመሪያ የማውጣት ሥራ ተሠርቷል። የተለያዩ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎችን ምሁራን እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ ያቀረቡትንም ወረቀት ለህትመት በማብቃት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር የታተሙ የጥናት መጽሔቶች (ጆርናሎች) አሉ፤ እነዚህ ሥራዎች ተሠርተዋል። ጥናቶቹ ለፖሊሲ ግብዓት ይሆናሉ።

ሌላው በዐባይ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት እንዳላት ለውጪ አገራት በማሳወቅ የተያዩ ተጽእኖ የመፍጠር ሥራዎች ሲሠሩ ከርመዋል። እንደውም ኢትዮጵያዊነት ይህን ንቅናቄ ካመጣና ካስጀመረ በኋላ፣ የተለያዩ ድርጅቶች ተመሥርተዋል። እነዚህም ዐባይ ግድብን በሚመለከት የተለያዩ እንቅስቃሴ የሚደርጉ ናቸው።

ሌላው የኮቪድ 19 ወርርሽኝ ወቅት፣ አገር ሲጎዳ በተለያየ ዘርፍ መደገፍ ተገቢ እንደመሆኑ፣ ከግሎባል አሊያንስ ጋር በመተባበር የሳኒታይዘር ፕሮጀክት ሥራዎች ነበሩ። ሌሎችም ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። እንዲህ አገር በምትታመምና ብዙ ችግሮች በሚደርሱ ጊዜ፣ ለውጪ አገራት መንግሥታት አቤት የማለትና የማሳወቅ ሥራዎች በብዛት ይሠሩ ነበር።

ኢትዮጵያዊነት ቀጣይ እቅዱና ሥራዎቹ ምን ምን ናቸው? ምን ተስፋስ ይታየዋል?

ብዙ ነገሮችን ለመሥራት ታስቧል። ይህ አሁን የተፈጠረው ችግር የአንድና የኹለት ዓመት ችግር አይደለም። በጣም ይዙ ዓመት ተደራራቢ ችግሮች ናቸው። ለመፍታትም እንደ ኢትዮጵያዊነት ድርጅት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኛ ሆኖ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

ነጻ የምሁራን መድረክ ማመቻቸት፣ አስቀድሞ እንዳልኩት ኢትዮጵያዊ ማንነቶችንና ጥሩ ጥሩ የሚባሉ እሴቶችን በትምህርት ስርዓት እንዲካተቱ የማድረግ፣ አገር በቀል እውቀቶቻችን በሚገባ ጎልተው እንዲወጡና በትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ የማድረግ ሥራዎችን ለመሥራት አቅደናል።

ሌላው የምሁራን የውይይት መድረክ ነው። ይህም በጣም ወሳኝ ነበር ነው። ነጻ የምሁራን ውይይት መድረክን ማመቻቸትም ሥራችን ነው። የኢትዮያዊነትን ቀንን በብሔራዊ ደረጃ ማክበር ከእቅዳችን አለ፤ ይህም እኛ ተነሳሽነት የፈጠርንበት ጉዳይ ነው። እነዚህን ለቀጣይ ዓመት አስበናል።

እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት ክበቦችን በትምህር ት ቤት ማቋቋም፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ማዘጋጀት፤ እነዚህ የቅርብ ጊዜ እቅዶቻችን ናቸው። መተግበሪያውም ጥሩ ጥሩ የሠሩ ኢትዮጵያዊያንን የማሞገስ፣ የመሸለም፣ የመዘከር ሥራዎችን ለመሥራት የሚያግዘን ነው የሚሆነው።

በረጅም ጊዜ የኢትዮጰያዊነት ተቋም ማቋቋም የሚል የያዝነው እቅድ አለ። በዚህም ጥሩ እሴቶቻችን ናቸው የምንላቸውን ነገሮች ጥናት እንዲደረግባቸው፣ የጥናቱ ውጤትም ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚየስችል ተቋም መፍጠር ነው ያሰብነው።

ኢትዮጰያዊነት እስከ አሁን ድረስ ለየት ያለ ድርጅት ነው ብዬ ነው መግለጽ የምፈልገው። ምክንያቱም ሀብት እንኳ ማሰባሰብ የምንፈልገው ከአገር ውስጥ ነው። እንዲህ ያለ አገር በቀል ድርጅት የመጀመሪያ ነው ብለን ነው የምናስበው። እናም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ማእከል ሆኖ የሚያገለግል ድርጅት ነውና። ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለየት ያለ ነው ብዬ ነው ብገልጸው ደስ ይለኛል። እንደ ማዕከል ሆኖ ሕዝብን ለማገልገል የተፈጠረ የሕዝብ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here