በአሶሳ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤት የተከማቸ 50 በርሜል ነዳጅ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ዋለ

0
1395

ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአሶሳ ከተማ ፖሊስ በህገ-ወጥ መንገድ በግለሰቦች ቤት የተከማቸ 50 በርሜል ነዳጅ ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማው ለኑሮ ውድነት ምክንያት እየሆነ የመጣውን ህገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ለመቆጣጠር ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ሰሞኑን ህብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ በግለሰቦች ቤት በተደረገ ፍተሻ 50 በርሜል ቤንዚን እና ናፍጣ ከአራት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል፡፡

በተጠርጣሪዎች ላይ የተጠናከረ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማው ቤንዚን እና ናፍጣ በጥቁር ገበያ በሊትር እስከ 200 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይቱ ምንጭ በህጋዊ መንገድ ከነዳጅ ማደያዎች ተቀድተው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ጥቂት ግለሰቦች እጅ መግባት እንደሆነ ፖሊስ እንደደረሰበት ኮማንደር ቡሽራ አስረድተዋል፡፡

ከህብረተሰቡ እይታ የሚሰወር ወንጀል የለም ያሉት ኮማንደሩ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የ90 ቀናት እቅድ በማውጣት ህብረተሰቡን ከማወያየት ጀምሮ ህገ-ወጥ ነዳጅ ሽያጭን ለመቆጣጠርና ገበያ ለማረጋጋት ከተቋቋመው ግብረሃይል ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት የአገር መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስን ጭምሮ በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ በአሶሳ ከተማ በግለሰብ ቤት በበርሚል የተከማቸ ቤንዚን ባስነሳው የእሳት አደጋ በአንድ ሰው ላይ ጉዳት ሲያደርስ በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ካወደመ በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ኮማንደር ቡሽራ አስታውሰዋል፡፡
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here