ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ያሉበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ባለቤታቸው ተናገሩ

0
1346

ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ አዲስ አበባ ውስጥ ከቤታቸው እንደወጡ አለመመለሳቸውን ባለቤታቸው መነን ኃይሌ ገለፁ።

መነን ስለ ባለቤታቸው ሲናገሩ ትናንት ሰኞ ግንቦት 08 ቀን 2014 ከቤታቸው 5 ሰዓት 15 አካባቢ የወጡት ከጓደኛቸው ጋር ቀጠሮ እንደነበራቸው ገልፀው መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚያ በኋላ ግን ወደ ቤታቸው ባለመመለሳቸው ደጋግመው ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ቢደውሉም ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋ።

ጄኔራል ተፈራ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም በቅርቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው መስራታቸው ይታወሳል።

እንደ መነን ገለፃ ከሆነ፤ ጄኔራል ተፈራ ያገኟቸው ሰዎች በዕለቱ እስከ 10 ሰዓት ድረስ አብረው መቆየታቸውን እና ከዚያ በኋላ እንደተለያዩ ነግረዋቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን የደረሱበትን ለማወቅ እንዳልቻሉ ባለቤታቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጄኔራል ተፈራ ሞሞ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥነት ከተነሱ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ አስተያየታቸውን ይሰጡ ነበር።

መነን የባለቤታቸውን መጥፋት አስመልክቶ ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ በመሄድ ቢጠይቁም ግለሰቡ “በቁጥጥራቸው ሥር እንደማይገኝ” እንደገለፁላቸው ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓትም ባለቤታቸውን ለማግኘት ሊኖሩበት ይችላሉ ወደተባሉ የተለያዩ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት በመሄድ ፍለጋቸውን መቀጠላቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ጄኔራል ተፈራ ማሞ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን የገለፁት ባለቤታቸው የታዘላቸውን መድኃኒት እየወሰዱ አንደነበር አመልክተው፣ መድኃኒታቸውን ካልወሰዱ አንደሚታመሙ በመጥቀስ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ባለቤታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሚኖሩበት ባሕርዳር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በእግራቸው ውስጥ የሚገኙትን ጥይቶች በተመለከተ የሕክምና ክትትል ለማድረግ እንደነበረም ጨምረው አስረድተዋል።

“እስሩን ለምዶታል ያለፈበትም ነው፤ የሚያሳስበን ጤናው ሁኔታ ነው” ብለዋል።

የጄነራሉን መሰወር በተመለከተ የፌደራልም ሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስካሁን ያሉት ነገር አለመኖሩን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዲዬር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ጋር ተከሰው ለዓመታት በአስር ላይ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በቅርቡም የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here