ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮለኔል ገመቹ አያናን ከኦሮሚያ ፖሊስ በአደራ ከመቀበል ውጪ ምንም የወንጀል የምርመራ መዝገብ በሥማቸው እንደሌለው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።
ይህ የተገለጸው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ በነበረ ቀጠሮ ላይ ነው።
ኮለኔል ገመቹ አያና ባለፈው ዓመት ግንቦት 9 ቀን 2013 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና ህገ መንግስታዊ ወንጀል ችሎት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል በነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።
ሆኖም በነጻ ከተሰናበቱ በኋላ በነጋታው ግንቦት 10 ቀን 2013 ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወጡ በር ላይ በኦሮሚያ ፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸውንና 6 ወር በገላን ፖሊስ ጣቢያ እና ወታደራዊ ካንፕ እንዲሁም በአዋሽ መልካሳ በአንድ ጄነራል ዶሮ እርባታ ውስጥ ታስረው እንደነበር፤ ከህዳር 16 ቀን 2014 ጀምሮ ደግሞ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፈው እንደተሰጡና እንደታሰሩ ተገልጾም ነበር።
ዓቃቢህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የእስር ፍርድ ቤት በነጻ ያሰናበታቸውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ፤ መዝገቡን የመረመረው ይግባኝ ሰሚ ችሎት ኮለኔል ገመቹ በእስር የቆዩበት ሁኔታ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም አይፈጸም ማረጋገጫ ባልቀረበበት ኹኔታ በጉዳዩ ላይ ክርክር ማስቀጠል አይቻልም ሲል መዝገቡን የዘጋ ቢሆንም፤ ዓቃቢህግ በድጋሚ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠይቋል።
በዚህ ይግባኝ መነሻ በትናንትናው ዕለት በነበረው የ3ኛ የሰበር ሰሚ የችሎት ቀጠሮ የኮለኔል ገመቹን ማን እንዳሰራቸው እንደማያውቅ ነገር ግን ከኦሮሚያ ፖሊስ ለፌደራል ፖሊስ በአደራ መሰጣታቸውን ደብዳቤ እንደጻፉላቸው ዓቃቢህግ ገልጾ ነበር።
3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ሀላፊ ቀርቦ በምን ሁኔታ እንደታሰሩ እንዲያስረዳ በይደር ለዛሬ የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተወከሉት ኮማንደር ኦልርትሮ ኦቦ ቀርበው ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም ኮለኔል ገመቹ አያናን በአደራ የኦሮሚያ ፖሊስ እንደሰጣቸው የገለጹ ሲሆን፤ ኮነሬል ገመቹን ይዘን ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ በመሔድ ተረከቡን ብለን ስንጠይቅ ኦሮሚያ ፖሊስ እኛ ጋር ጉዳይ የለውም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ኮማንደር ኤርትሮ ለችሎቱ አብራርተዋል።
ኮማንደር ኤርትሮ በኮለኔል ገመቹ አያና ላይ በፌደራል ፖሊስ በኩል የተከፈተ የወንጀል ምርመራ መዝገብ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ዓቄቢህግ በበኩል ኮለኔል ገመቹ መታሰራቸውን አንፈልግም ቢለቀቁ አልቃወምም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ኮለኔል ገመቹ አያና በፍርድ ቤቱ በኩል ምን እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከጠበቃቸው ቱሊ ባይሳ ጋር ተማክረው ፍርድ ቤት ነጻ እንዳለኝ ኹሉ በነጻ እንድፈታ ነው የምፈልገው ሲሉ ገልጸዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት፤ የዓቃቢህግና የፌደራል ፖሊስ ምላሽን በመመዝገብ ለፊታችን ግንቦት 15 ቀን የኦሮሚያ ፖሊስ ሀላፊ ስለ ኮነሬል ገመቹ አያና የእስር ሁኔታ የሚገልጽ መልስ በጽሁፍና እንዲያቀርብና በአካል ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዛዙን የፌደራል ፖሊስ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።።
ማንኛውም ዜጋ ባለስልጣንም ቢሆን የሚዳኝበትን የአገሪቱን ፍርድ ቤት ማክበር እንዳለበት በችሎቱ ዳኞቹ ተገልጿል።
ኮነሬል ገመቹ አያናን አጅበው በቀረቡ በኹለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ችሎት የተገኙ ጋዜጠኞችን ደብዳቤ ካላመጣችሁ በስተቀር መግባት አትችሉም ተብለው በመከልከላቸው ምክንያት ጋዜጠኞች በችሎት በር ላይ ቆመው ጉዳዩን ለመከታተል መገደዳቸውም ታውቋል።




