ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ መሰረዙን የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ግዥ ጠያቂነት የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ2014 በጀት ዓመት የወባ መከላከያ አጎበር ግዥ ለመፈጸም ሕዳር 10 ቀን 2021 በወጣው የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ በጨረታ ቁጥር Tender No:ICB/EPSA6/MOH-GF/LLINS/MS/23/ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ከወጣው የግዥ ጨረታ ጋር በተያያዘ የግዥ ሂደቱ “ህግን የተከተለ አይደለም ” የሚል ጥቆማ ለፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ፤ ከየካቲት 8 እስከ 24/2014 በአስቸኳይ የሙስና መከላከል የማጣራት ሥራ ማከናወኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የቀረበውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ ባደረገው የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ አሸናፊ ተደርጎ የተመረጠው ድርጅት የአገር ውስጥ የወባ መከላከያ አጎበር የማረጋገጫ ፍቃድ (የምስክር ወረቀት) የሚሰጡና የሚያድሱ አካላት ኃላፊነት በግልፅ አለመቀመጡን እንደ ምክንያት አድርጎ በመውሰድ፤ ካስቀመጣቸው ሦስት ወኪሎች በአንደኛው ተወካይ ህግን ባልተከተለ መልኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ህገ-ወጥ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የወሰደና በጨረታው እንዳይወዳደር የተሰረዘበት መሆኑን አረጋግጧል።
በተጨማሪም በሌላኛው ተወካይ በተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት በመወዳደር የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን መደረጉ፣ የዋናውን ድርጅት (Principal Agent) ከተጠያቅነት እንደማያድነውና የግዥው ሂደት ጤናማ አለመሆኑ ከማጣራት ሂደቱ ለመረዳት መቻሉን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ባረጋገጠቸው ግኝቶች ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ግዥውን ከሚፈፅመው ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ መያዙ ተገልጿል፡፡
ይህ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ ለ17 ሚሊየን 809 ሺህ 388 የወባ መከላከያ አጎበሮች ግዢ ጨረታ የወጣ ሲሆን፤ ሂደቱ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በማጣራት ግኝቱ የማስተካከያ ምክረ-ሀሳቦችን የያዘ ሪፖርት ለጤና ሚኒስቴር እና ከላይ ለተመለከቱት መንግሥታዊ ተቋማት አሳውቋል፡፡
ከዚህ በመነሳት የኤፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ግንቦት 09 ቀን 2014፤ በቁጥር መጠ1/17/40/723 በፃፈው ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እያሉ የዓለም አቀፍ ጨረታ ሂደቱን ባለበት ሁኔታ ማስቀጠል በግዢዉ ሂደት ላይ የነበረን ስጋት እንዲቀጥል የሚያደርግና ውጤቱ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አሉታዊ ተፅኖ ሊፈጠር እንደሚችል በመጥቀስ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን ሰርዟል፡፡ ይህንኑ ውሳኔ ተጫራቾች እንዲያውቁት እንዲደረግ ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ማሳወቁንም የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመረጃው አመላክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረ-ሀሳብ ተቋማት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በራስ ውሳኔ ወደ መከላከል የሚያደርስ በመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህንኑ ምክረ ኃሳብ በመቀበል የእርምት እርምጃ መውሰዱ አርያነት ያለው ተግባር ነው ሲልም ገልጿል፡፡




