ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቤት አቅርቦትን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዓመት 200 ሺህ እና ከዚያ በላይ ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ያስሚን ዉሀቢረቢ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በመተባበር የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር ውይይት በዛሬው ዕለት አድርጓል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት፤ ያስሚን ዉሀቢረቢ የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጃቸውን አማራጭ የቤት ልማት ሞዳሊቶችን ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ለሪል እስቴት አልሚ ድርጅቶች ለመጡ ተሰብሳቢዎች አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር በመተባበር፣ የሚችሉ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና ሌሎችም በአቅማቸው ልክ ቤቶቹ ተገንብተው በተመጣጣኝ ዋጋ ተከራይተው የሚኖሩበትን ኹኔታ ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ኹሉ ጋር የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀዋል፡፡
ባለሀብቶች የልማት አጋር እንደመሆናችሁ መጠን የተዘጋጁ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር በመመልከት ለተግባራዊነቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ለመስራት እንቅስቃሴ ልታደርጉ ይገባል ብለዋል
አያይዘውም የከተማ አስተዳደሩ፤ የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት በሂደት ለመቅረፍ አምስት የቤት ግንባታ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር አዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ኹሉ ለማድረግ አጋርነታችሁን እየተጠባበቀ የሚገኝ በመሆኑ፤ እናንተም በነፍስ ወከፍ በአጭር ግዜ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት የየድርሻችሁን አሻራ ለማኖርና የታሪክ ተከፋይ ለመሆን ልትሰወስኑ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የውጭ አገር አልሚዎችን የአዋጭነት ደረጃን በመፈተሽ እንዲሳተፉ ለማድረግ ይሰራልም ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የቤት አቅርቦትን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዓመት 200 ሺህ እና ከዚያ በላይ ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ ያስሚን ዉሀቢረቢ ሲሆኑ፤ አሁን ያለው ወቅታዊ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ አልሚዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ የተዘረጉ ሞዳሊትዎችን መሠረት በማድረግ ልትሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የግሉ ዘርፉ በተለይ የቤት ልማትን በሚመለከት የፌደራል መንግስትና ከተማ አስተዳደሩ የጀመሩትን በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ የለውጥ ሥራዎች መሠረት በማድረግ በሽርክናና በሌሎችም ተስማሚ አማራጮች ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ መስራት ከአልሚዎች ይጠበቃል ሲሉ አስታውቀዋል ኃላፊዋ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በቅርበት የሚሰራ ግብርሃይል በውይይቱ መጨረሻ መቋቋሙን የከተማ አስተዳደሩ መረጃ አመላክቷል።







