ሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በመተከል ዞን በድባጤ እና በቂዶ ወረዳዎች የሚገኙ የጉሙዝ የሚሊሻ አባላት ከጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው ለአሸባሪ ቡድኖች የሚላላኩ ሽፍታዎችን መደምሰሳቸውን የመተከል ኮማንድ ፖስት የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
ኃይሉ ተወካይ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ዋለልኝ ታደሰ እንደተናገሩት፤ የሚሊሻ አባላቱን ከግል ፍላጎት ወደ ቡድን አንድነት አደረጃጀት በመቀየር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕወሓት ተላላኪ ሽፍቶችን በመደምሰስ እና የጦር መሳሪያዎችን በመማረክ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።
የሚሊሻ አባላቱ ቡድን መሪ የሆኑት ብድኡከም በታሐኒ በበኩላቸዉ የሕወሓት ተልዕኮ አስፈፃሚዎችን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ እና ሕዝቡን ከጥፋት ቡድኖች ለመታደግ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን ብለዋል፡፡
የሚሊሻ አባላቱ በበኩላቸው፤ ከጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ ቀን ከሌሊት የሚደክሙ የአሸባሪ ኃይሎች ላይ አስፈላጊውን የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡





