ከእነዚህም ውስጥ 210 የሚሆኑት በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ናቸው ተብሏል
ሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሰሞኑን በተካሄደ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ4 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ የቢሮው ኃላፊ ዳሳለኝ ጣሰው መንግሥት የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ በተሰራው የህግ ማስከበር ሥራ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ4 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው የነበሩ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ 210 በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ሕገ ወጦችን ለመያዝ ከሚደረግ ሥራ ውጭ ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ላይ እንደሚገኝም የቢሮው ኃላፊ ገልጸዋል።
መንግሥት የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ትክክለኛውን የፋኖ ሥም የማይወክሉ፣ በፋኖ ሥም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስም ደሳለኝ ገልጸዋል።
ትክክለኛ የፋኖ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ሥር በማድረግ እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑንም ሀላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡



