ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በቆቦ ከተማ በጋሪ ብረቶች ውስጥ ተደብቆ ለህወሃት ቡድን ሊደርስ የነበረ 3 ሚሊየን ብር በቆቦ ከተማ ህዝብ፣ በከተማው ፓሊስና በሕዝባዊ ሚኒሻ ሠራዊቱ አማካኝነት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።
የቆቦ ከተማ አስተዳደር ሠላም እና ፀጥታ ሀላፊ ሀምሳ አለቃ አበበ ደርሶ እንደተናገሩት፤ “ብዙው ነገር ሲደረስበት ባልተነቃ መልኩ ለጁንታው እናደርሳለን ያሉት የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ወገናቸውን አሳልፎ እንዲሰጡ ቢደረግም በኹሉም የፀጥታ ሃይላችን አማካኝነት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።”
የቆቦ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ ፅ /ቤት ሀላፊ ኮማንደር ታደሰ ተሰሜ በበኩላቸው፤ ጋሪው የተሰራው ሙሉ በሙሉ ውስጡ ክፍት በመሆኑ፤ ሥም የተፃፈበት ብር በእያንዳንዱ ብረት በማድረጋቸው ላለመያዝ የተጠቀሙበት መንገድ ያልተጠበቀ ቢሆንም የቆቦ ከተማ ህዝብም ይሁን የፀጥታ አካሉ በመግባባቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።
ኮማንደር ታደሰ እና ሀምሳ አለቃ አበበ በጋራ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ኹላችንም በጋራ ከሰራን ከዚህ የበለጠ ችግር ቢገጥመንም በጋራ የማንወጣው አስከፊ ችግር ስለማይኖር አገር የማዳን ሥራችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ገልፀው፤ የቆቦ ከተማ ህዝብ ካጠገባችን በመሆኑ ኹሌም ኩራት ይሰማናል ማለታቸውን ከቆቦ ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።






