የኦሮሚያ ፖሊስ ኮለኔል ገመቹ አያና የታሰሩበትን ሁኔታ ቀርቦ እንዲያስረዳ ቢታዘዝም ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ቀረ

0
982

ሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሚያ ፖሊስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር የሆኑት ኮለኔል ገመቹ አያና የታሰሩበትን ሁኔታ ቀርቦ እንዲያስረዳ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት የታዘዘ ቢሆንም ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ቀረ።

የኦሮሚያ ፖሊስ በሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀርቦ የኮለኔል ገመቹን የእስራት ሁኔታ በጽሁፍና በአካል እንዲያብራራ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በነበረ የችሎት ቀጠሮ መታዘዙ ይታወሳል።

በትዕዛዙ መሰረት ዛሬ ረፋድ ላይ በነበረ በችሎቱ ቀጠሮ ጥሪ ቢደረግም ከኦሮሚያ ፖሊስ ማንም አካል ሳይቀርብ ቀርቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር የሆኑት ኮለኔል ገመቹ አያና በግንቦት 09 ቀን 2013 በስር ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ነጻ ከተባሉ በኋላ፤ በነጋታው ግንቦት 10 ቀን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወጡ በኦሮሚያ ፖሊስ ተይዘው በገላን ፖሊስ ጣቢያ እና በወታደሪዊ ካንፕ እንዲሁም በአዋሽ መልካሳ በአንድ ጀነራል ዶሮ ዕርባታ ውስጥ ለ6 ወራት ታስረው እንደነበር እና ከስድስት ወር በኋላ ከህዳር 16 ጀምሮ ደግሞ በፌደራል ፖሊስ በእስራት ላይ መሆናቸውን ከዚህ በፊት ለፍርድ ቤት አስረድተው ነበር።

ኮነሬል ገመቹ አያና ነጻ በተባሉበት የሽብር ክስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዓቃቢህግ ይግባኝ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፤ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱም ኮነሬል ገመቹ ታስረው በነበሩበት የእስራት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙና አለመፈጸሙ ማረጋገጪያ ባልቀረበበት ሁኔታ ክርክር ማስቀጠል አይቻልም ሲል መዝገቡን መዝጋቱ ይታወሳል።

ይሁንና ዓቃቢህግ በድጋሚ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በጠየቀበት በዚህ መዝገብ፤ የኮነሬል ገመቹ አያና የእስር ሁኔታ ላይ ባሳለፈው አርብ ዕለት በነበረ ቀጠሮ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኮነሬል ገመቹ አያና ላይ ምንም አይነት የተከፈተ የወንጀል ምርመራ መዝገብ እንደሌለው ምላሽ ሰጥቷል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱም በኮነሬል ገመቹ የእስር ሁኔታ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ቀጠሮ ሳይቀርብ መቅረቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

ጉዳዩን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በይደር ቀጠሮ መያዙም ታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here