ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፍ ከ458 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ ለምክር ቤቱ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ ከማዕድን ዘርፍ ከ458 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ገቢው የተገኘው ከወርቅ፣ ጌጣጌጥና ኢንዱስትሪ ማዕድናት መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንጂነር ታከለ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ንግድን በማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት መደላድል መፍጠር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ላይ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የወርቅ ማዕድን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 6 ሺህ 947 ኪሎግራም ተመርቶ ለብሄራዊ ባንክ የቀረበ ሲሆን፤ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 106 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን እና ከ2013 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸርም የ12 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
የጌጣጌጥ ማዕድናትን በተመለከተም 2 ሺህ 317 ኪሎ ግራም ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን ከዕቅዱ አንጻርም የ103 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡






