አየር መንገዱ አምስት ተጨማሪ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ሊገዛ መሆኑን አስታወቀ

0
1448

ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአፍሪካ ትልቁ እና ቀዳሚው የአቪዬሽን ግሩፕ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖቹን ቁጥር ለማሳደግ አምስት ተጨማሪ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን ማዘዙን አስታውቋል።

አየር መንገዱ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ እንዳስታወቀው ለመግዛት ያዘዛቸው አምስቱ አውሮፕላኖች የቅርብ ጊዜ እና ዘመናዊ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ “እነዚህ አምስት የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ከዚህ በፊት በነበሩት የካርጎ አውሮፕላኖች ላይ መጨመራቸው እያደገ የመጣውን የካርጎ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት ያስችለናል።” ብለዋል።

አዲሱ ትዕዛዝ አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለውን አጋርነት የበለጠ ከማጠናከር ባሻገር የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች መጠን ማደጉ የድርጅቱን የማጓጓዣ አገልግሎት አቅምን እና ቅልጥፍናን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰውም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ማቅረብ በሚችለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ደንበኞቹን ለማገልገል ኹልጊዜ የሚተጋ መሆኑንም መስፍን ጨምረው ገልፀዋል።

የቦይንግ የሽያጭ እና ግብይት ምክትል ፕሬዚዳንት ኢህሳን ሙኒር በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎቱን ለማሟላት በቦይንግ ላይ ለጣለው አመኔታ አመስግነው ተጨማሪ አውሮፕላኖቹ የአየር መንገዱን የቅርብ ጊዜ ፍላጎት የሚያማሉ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን፤ አምስት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ያዘዘው የጭነት አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በገበያው ላይ መሪ የሆነው ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን የዓለማችን ግዙፉ እና ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችል ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል።

ከቀድሞዎቹ ጋር ሲነፃፀርም በ17% ያነሰ ነዳጅ የሚጠቀም እና አነስተኛ የበካይ ጋዝ ልቀትን መያዝ ይችላል ተብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here