የቱርክ ባለሀብቶች በአፋር ክልል የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

0
1422

ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቱርክ ባለሃብቶች በአፋር ክልል የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፒራክ አልፒ ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰመራ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንደተናገሩት፤ ቱርክና ኢትዮጵያ የቆየ ወዳጅነት ያላቸዉ አገሮች ናቸዉ።

እንዲሁም ቱርክ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት አጀንዳዎችና ኢንቨስትመንት ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

የቱርክ አምባሳደሮች በተለያዩ ግዜያት በአፋር ጉብኝት ማድረጋቸዉን ገልጸው፤ ከዚህ በፊት በክልሉ በነበረዉ ድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በተግባር አረጋግጠዋል።

የዛሬዉ አምባሳደሯ ጉብኝትም ይህን ወዳጅነት የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ቱርካዉያን ባለሀብቶችም በክልሉ በጨዉ አይወዳይዜሺን እየተሳተፉ ሲሆን፤ በተጨማሪም በሪል እስቴትና ኬሚካል ኢንዱስትሪ መስክም ኢንቨስት ለማድረግ ቦታ የወሰዱ መኖራቸዉን ጠቁመዋል።

ክልሉ በማዕድንና በግብርና መስክ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ያለዉ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዘርፎቹ ለሚሠማሩ ቱርካዉያን ባለሀብቶች ክልሉ አስፈላጊዉን ድጋፍ ያደርጋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፒራክ አልፒ በበኩላቸው፤ የኹለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር ሃላፊነታቸዉን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አምባሳደሯ አክለውም ቱርክ በኢትዮጰያ የልማት እቅዶችን ከመደገፍ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠና ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንቨስትመንት መስክም የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ዋነኛ የኢንቨስትመንት አጋር መሆናቸዉን ገልጸዉ በቀጣይም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፏቸዉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አምባሳደሯ በክልሉ በሚኖራቸዉ ቆይታ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን፤ የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋዉረዉ እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here