በባቡር የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል

0
1170

ለአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ገለጸ።
በዚህም ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የአገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ ነው ተብሏል።
በ2013 በጀት ዓመት ብቻ በዚሁ የቀላል ባቡር መስመር ላይ በተዘረጋ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል 1 ሚሊዮን 293 ሺሕ 350 ብር የሚገመት ርዝመቱ 1 ሺሕ 55 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት እንደተፈፀመ ታውቋል።
በ2014 በጀት ዓመትም 24 ሚሊዮን 800 ሺሕ 725 ብር በላይ የሚገመት ርዝመቱ 15 ሺሕ 347 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት መፈፀሙ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ከ2013 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 16 ሺሕ 402 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ስርቆት ተፈፅሞ 26 ሚሊዮን 94 ሺሕ 75 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱ ነው የተገለጸው።
አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ስርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በልደታ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑም ተመላክቷል።
መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀምን የስርቆት ድርጊት ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በሥራ ላይ ቢውሉም፣ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣና ከፍተኛ የአገር ሀብት እየተዘረፈ መሆኑ ተገልጿል።
በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በአገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here