የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማደፍረስ በአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ያሏቸውን ከ340 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸወን የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቁ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሚያዚያ ወር አጋማሽ የሕግ ማስከበር ስራ እንዲሰራና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውሰው ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት አዲስ አበባ ላይ ትኩረት ሰጥተው ጠንከር ያለ የህግ ማስከበር ስራ ሰርተዋ ብለዋል፡፡
በጦር መሳሪያ ጭምር ተደራጅተው ዝርፊያ የፈጸሙ፣ ተሽከርካሪዎችን የዘረፉ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በመደበቅ በዝርፊያ ላይ በተሰማሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ ጠንካራ የክትትልና የምርመራ ስራ ተሰርቶ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ኮሚሽነር ሐሰን ገለፃ ከግለሰብና ባንክ ዘረፋ ጋር በተያያዘ 10 ተጠርጣሪዎች፣ ከመኪና ስርቆት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ 22 ተሽከርካሪዎችን የዘረፉ 33 ተጠርጣሪዎች ከነግብረአበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የሚዲያን ነፃነትን ተገን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና አገርን ለማፍረስ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ሽብር ሲነዙ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ በበኩላቸው የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማወክ ከተንቀሳቀሱና ከአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው 84 ግለሰቦችን ከሶማሌ ክልል ፖሊስ ጋር የጋራ ስራ በመስራት በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከሸኔ የሽብር ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀስ የነበሩ ግለሰቦች ተይዘው በምርመራ እያጣራን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የህዝብ እና የመንግስት ሀብትን ለመመዝበር ከባለስልጣናት ጋር ተመሳጥረው በሙስና ወንጀል ከ580 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ የመንግስት ባለስልጠናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014


