የገጠሩ ነዋሪ ማነቆዎች

0
1505

ከመራቤቴዋ መራኛ ከተማ ተነስተን ፀበለ ማርያም ወደምትባል ጥንታዊ ገዳም ነበር ያመራነው። ሰሜን ሸዋን ተሻግረን ወደ ወሎ ግዛት ከገባን ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ጃማ ደጎሎ ከተማ ልንገባ ትንሽ ሲቀረንመ፣ ከነበርንበት ፒስታ ተገንጥለን ወደቀኝ የሚወስድ የባሰ ኮረኮንች መንገድ አገኘን። ለበርካታ ኪሎሜትሮች መኪናን የሚፈትነው ይህ መንገድ በአንድ የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብት ድጋፍ የተሠራ መሆኑንም በጉዟችን መካከል ተረዳን።

አልፎ አልፎ አጀብ አጀብ ብለው የተመሠረቱ መንደሮችን እያለፍን በተጓዝንበት ወቅት፣ ጊዜው ጠዋት ስለነበር ከሚኖሩበት ርቆ የሚገኝ መሬታቸውን ለማረስ ሞፈርና ቀንበራቸውን ተሸክመው በሬዎቻቸውን እየነዱ የሚሄዱ በርካታ አርሰው አደሮችን ማየት ችለናል። ከቦታው ገጠራማነት የተነሳ ወደ ውስጥ ዘልቀን በገባን ቁጥር ተመልካቹ በአግራሞት የሚመለከትበት አካባቢ ነው። የገጠር ነዋሪ መገለጫ የሆነው ከልብ የመነጨ ሰላምታንም ሳይሰጠን የሚያልፍ የለም ማለት ይቻላል።

የጉዟችን መዳረሻ ወደሆነችው ጥንታዊት ገዳም ለመድረስ መኪና ስለማያስገባ የሰዓታት መንገድን በእግር መጓዝ ይጠይቃል። ኃይለኛ ቁልቁለትና ዳገትን መውጣት የሚጠይቀውን መንገድ የአካባቢው ነዋሪዎች ያቀላጥፉታል። ፎቅ ላይ የሚኖር ከተሜ እንኳን አንድ ፎቅ ለመውጣት ሲተነፍስ የምናየውን ዓይነት የድካም ስሜት እቃ ተሸክመው ከ20 እስከ 30 ፎቅ ሊረዝም የሚችል ዳገትን በፍጥነት ሲወጡት ማየት ያስገርማል። አንድ እኛን ሊቀበል ከታች ከቆላው የመጣ ወጣት፣ የሰዓታቱን ጉዞ ሦስቴ ተመላልሶ ሲታይ በእኛ በከተሜ ዕይታ ‹ልዕለ ሰብእ› ሊያስብለው ይችላል።

የተጓዝንበት ቦታ የወሎና የሸዋን ግዛት የሚለየው የጀማ ወንዝን ታኮ የተመሠረተ እንደመሆኑ፣ የኹለቱ ክፍላተ አገሮች መለያ የሆነው ሸለቆ ውስጥ ገብቶ መውጣትን ይጠይቃል። ወንዙ በክረምት ካልሆነ በቀር በበጋ ያንያህል ስለማያሰጋ፣ የኹለቱን አካባቢ ነዋሪዎች ከማቀራረብ እንቅፋት አልሆነም። ኦሮሚያን አልፈን ወደ አማራ ክልል ስንገባ የሚለይና ወሰን ማቋረጣችንን የሚነግረን ኬላም ሆነ ምንም ዓይነት ምልክት እንዳለመኖሩ፣ በዚህም አካባቢ ነዋሪው ሲጠየቅ ከሚናገረው ውጭ ልዩነቱን የሚገልፅ አንዳችም ዓይነት ምልክት የለም።

ቦታው እጅግ ከከተማ የራቀ እንደመሆኑ በቆርቆሮ የተሠራ ቤት የሚታየው አልፎ አልፎ ነው። ብዙ የምንባል የከተማ ነዋሪዎች የሳር ቤት ጎጆ ስናይ የምንደሰተውን ያህል ነዋሪዎቹ እንደጥንቱ መቀጠል ባይፈልጉም፣ አማራጭ አጥተው የተገደዱ እንዲህ አይነት አካባቢዎች በብዛት ማየት ቀላል ነው። የሳር ቤት ወጪው አነስተኛ ቢሆንም፣ እንደቆርቆሮ ቤት እድሜ ስለማይኖረው ተቀባይነቱ ዝቅተኛ ነው። ልጅ የወላጆቹ ቤትን ወርሶ ውስጡ መኖር ነውር በነበረበት በጥንት ዘመን ከአንድ ትውልድ በላይ የሚቆይ መኖሪያ ቤትን መገንባት እንደጅል የሚያስቆጥር ልፋት ተደርጎ ይወሰድ ነበር። አሁን አሁን ግን ይህ ባሕል ከድህነታችንና ከመሬት ጥበት አኳያ ተቀባይነት እያጣና ጭራሽ የማይታወቅ ኋላቀርነት ተደርጎ ስለሚወሰድ፣ የሚገነባ ቤት ሁሉ ከትውልድ ወደትውልድ እየታደሰ እንዲተላለፍ ይፈለጋል።

ከመኖሪያ ቤቶች ባሕላዊነት አኳያ፣ ክብ ቤትን ለወደፊት ማየት ብርቅ እስከሚሆን ድረስ በገጠር ያሉ ቤቶች ጭምር ወደ አራት ማዕዘን እየተቀየሩ ይታያሉ። ዘመናዊነት ስለሆነ ይሁን ወይስ የአናፂዎች እውቀት የተገደበ በመሆኑ ባይታወቅም፣ በቆርቆሮ ተደርጎ ክብ የሚሠራ ቤት ማየት ከባድ ነው። ከቤተክርስቲያን ውጭ መኖሪያን ክብ አለማድረጉ ከቆርቆሮ ቁጠባ አንፃር ሊታይም ይችላል።

አንድ የገጠር ነዋሪ ስለቤቱ ስፋት ሲናገር ካሬሜትርን መጠቀም እንግዳ ነገር ነው። ቤቱን ሲያሠሩ አናጢ ከሚነግራቸው ተነስተው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ 40 ቆርቆሮ ወይም ይህን ያህል ቆርቆሮ የፈጀ ቤት ነው እያሉ ሲገልፁ መስማት አይገርምም።

በእንዲህ ዓይነት የተለመደ ልኬት የሚናገሩት ቤታቸውን ብቻ ሳይሆን የእርሻቸውንም ስፋት ነው። ማሳቸውን በቆርቆሮ ብዛት ሳይሆን በሚያርሰው ጥማድ በሬ ልክ ይህን ያህል ጥማድ ነው ብለው ሲጠየቁ ይናገራሉ። በዚህ መንገድ እነሱ የሚግባቡትን ያህል እኛ ከተሜዎች ለመገመትም አንችልም። አንድ ጥማድ የሚሉት አንድ ካሬ ሜትር ይሁን አንድ ሄክታር ለመገመትም ከባድ ነው። እነሱ ግን ለማዳበሪያም ሆነ ለሚያስፈልጋቸው የዘር እህል በጥሩ መንገድ እንደሚገምቱበት ማወቅ ይቻላል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በ1985 ለአዲስ ትውልድ አራሾች ከተሰጠ አዲስ የእርሻ መሬት ውጭ እስከ አሁን ምንም ዓይነት አዲስ መሬት እንዳልተሰጠ ይነገራል። አንድ አባወራ የነበረችውን ጋሻ መሬት ለሁሉም ልጆቹ ማካፈል ግዴታ ሆኖበት ቦታዋ እያነሰች መሄዷ ግልጽ ነው። ስምንት ቤተሰብን ታስተዳድር የነበረች መሬት ስትከፋፈል ልጆች አነስተኛ ኩርማን መሬት ስለሚደርሳቸው፣ እነሱ በዘመናቸው የወላጆቻቸውን ግማሽ ያህል እንኳን ወልደው ማሳደግ አይችሉም።

በዚህ መንገድ ድሃ ሆነው የሚያድጉ የእነሱም ልጆች መሬታቸውን ሲያካፍሉ እየባሰ ሄዶ ትውልድ እንደሚከሽፍ የሚናገሩ አሉ። የሕዝብ ቁጥርን ያለሕዝቡ ፍላጎት ለመቀነስ አስበው ይህን ሴራ የሸረቡ የቀድሞ ባለሥልጣናትን ተግባር አሁንም እያስቀጠሉ መሄድ የአርሶ አደሩ ትልቁ ስጋት ነው። ልጅ ተምሮ የመንግሥት ሥራ ከያዘ የአባቱን መሬት መውረስ እንደማይችል የሚደረገው አሠራርም የራሱ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

ይህ የመሬት እጥረት እንዳለ ሁኖ ገበሬው የሚያረባቸውን ከብቶች እንዲወስን የሚያደርግ የቅርብ ጊዜ መመሪያም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ይነገርለታል። የጋራ ከብት አሰማርቶ ማስጋጫ የነበሩትን ቦታዎች ለተወሰኑ ገበሬዎች በማከፋፈል ማንም ከመሬቱ ውጭ የትም ሄዶ እንዳያሰማራ የሚያዘው ገደብ የብዙዎች ከብት እንዲወረስ ከማድረጉ ባሻገር፣ ትውልድ ቁጥሩ ሲጨምር ከፍላጎቱ እኩል የሚያመርተው እንዲያድግ ስለማያደርግ በእጅ አዙር ወሊድን በመቆጣጠር ትውልድን ማደህየትና መቅጨት ነው ብለው የሚቃወሙት በርካቶች ናቸው።

በሌላ በኩል፣ መንገድ ለአንድ አገር የደም ስር ነው ሲባል በተደጋጋሚ ብንሰማም የሚመለከተው አካል የደም ስር ጥቅም ስላልገባው ይሁን የገጠሩ ነዋሪን ከቁብ ስለማይቆጥረው ባይታወቅም፣ ትኩረት ተሰጥቶት እንደከተማ ጎዳናው ሲሠራ ማየት ይናፍቃል። ከሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች (ቴሌን ሳይጨምር) የመንገድ ሥራው የተሻለ ነው ሊባል ቢችልም፣ ሕዝቡ ከሚፈልገው አንፃርም ሆነ ለሌሎች መናፈሻንና ቤተመንግሥትን ለመሳሰሉ ሀብታሙን ማዕከል ካደረጉ ግንባታዎች አኳያ ሲታይ ጭራሽ ታስቧል ማለት የሚያስደፍር አይደለም።

በመንገድ እጦት ሆስፒታል በሸክም የሚሄዱትን ማየት ለማንም የማይደንቅበት ዘመን ላይ ነው አሁንም የምንገኘው። ለባጃጅ የሚሆን መንገድን መጥረግ እንኳን የተሳነው ድሃ ማኅበረሰብን ያቀፈ አካባቢ እጅግ በርካታ መሆኑን ለመገንዘብ፣ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት አንፃር ያሏትን መንገዶች ርዝመትና የሚያዳርሱትን የኅብረተሰብ ክፍል ማነፃፀር በቂ ነው።

እንዲህም ሆኖ ከተማ ላለ ለተቸገረ ልጃቸው በተገላቢጦሽ ብር ለመላክ የሙሉ ቀን መንገድ በእግራቸው ተጉዘው ከተማ ዘልቀው በባንክ በኩል ከድሃ ሀብታቸው ላይ ቀንሰው በእንግልት የሚልኩ መኖራቸውን ማየትም ልብ ይሰብራል።

ጉዞው ቀጥሏል፤ ወደዛው ልመልሳችው። ወደ ጥንታዊቷ ገዳም የሚያደርሰንን መንገድ ተያይዘነዋል። በመንገዱ ለሰዓታት ሲጓዙ ቢውሉ ምንም ዓይነት የንግድ ተቋም ማየት ብርቅ ነው። በግለሰብ ደረጃ የተሠራ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንደመሆኑ፣ አንድም አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ሙሉ ቀን ማየት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ይመስላል ለረጅም ርቀት አንዲት አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ እንኳን ማግኘት ከባድ የሆነው።

ምግብ ቤት ከፍሎ ለመብላት ማሰብ ነዋሪውን የሚያስቅ ምኞት ነው። ደግነቱ የተራበን ምንም ሳይሰስቱ የሚያበሉ በርካቶች ለመሆናቸው የጠየቅናቸው የመጀመሪያዎቹ ያለማመንታት ወዲያው በሀዘኔታ ያላቸውን ምግብ ሲሰጡ ማይት በቂ ማስረጃ ነው። ከሩቅ የሚቀዱትን ውሃ ሳይሰስቱ ሰጥተውን ብንረካም፣ አብረውን ላልመጡ ተሽከርካሪው ጋር ለቀሩት መንገደኞች መውሰጃ እቃ ማግኘት ግን ትልቅ ፈተና ነው።

አነስተኛ ፌስታል ከአንድ ቤት ብቻ ሳይሆን ከመንደሩም ፈልጎ ለማግኘት የሚታየው ፍዳ ምን ያህል ከከተማ እንደራቁ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመናዊነት ካመጣቸው ኑሮን ከሚያቀሉ ምርቶች ምን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው።
ታች ገዳሙ ቀድመው የደረሱት፣ ከላይ ለቀሩት ብለው ያመጡት ምግብ እንደጥንቱ አሁንም ለገጠሩ ነዋሪ ምሳ ዕቃ በሆነው በአነስተኛ አገልግል የተጠቀሰ ነው። የገዳሙ አካባቢ ማኅበረሰብ እንግዳ እንደመጣባቸው ሲሰሙ ተጠራርተው ሁሉም ቤቱ ያፈራውን አዋጥቶ ነው ግብዣ የተደረገው። ብርዝን ጨምሮ የተሟላ ምርጥ ግብዣ ለማያውቋቸው ሰዎች ማድረግ ለከተማ ነዋሪ የሚያስተምረው ነገር ብዙ ነው።

‹የኔ ቢጤ› ብለን እየጠራናቸው፣ በር ሲያንኳኩና ሲለምኑን ግን የምንቆጣ በመሆኑ፣ አሁን አሁን ዞሮ በየቤቱ የሚለምን ባለመኖሩ ተርፎ የሚባክነውን ምግብ ቤቱ ይቁጠረው። ቢያንስ በየደጃፉ ላይ ቀበሌ አንጠልጥሉ ብሎ እንዳስገደደው የመንገደኛ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት፣ ውሻ እንዳይለክፈው ለተረፈ ምግብ መስቀያ የሚሆን ማስቀመጫ አድርጎ፣ ልግስና በፍላጎት የሚደረግበት መንገድ እንደሌላ አገር አለመመቻቸቱ የነበረንን በጎ ባህል በምን ፍጥነት እያጣን እንደሆነ አመላካች ነው።

ይህን እጅግ ገጠራማ አካባቢ ትተን ወደ ደጎሎ አቅጣጫ አረፋፍደን ተነስተን ከተማው ስንገባ ሊመሽ ተቃርቦ ነበር። የተለመደውን የወረኢሉ ደሴን መንገድ ትተን አዲስ እየተሠራ ያለን ከደጎሎ ወደ ከላላ ወረዳ የሚያቋርጠውን መንገድ ከመሸ ነው የተያያዝነው። አልፎ አልፎ ከሚታይ የከተማ መብራት ውጭ ለረጅም መንገድ ድቅድቅ ጨለማን አቋርጠን ስናልፍ መብራት ለዚህ ያህል ሕዝብ አዳረስን የሚለው የመንግሥት ሪፖርት እነሱን ሳይቆጥርና ከግምት ሳያስገባ ነው ወይ ያስብላል።

መንገዱ ግማሽ የተሠራ እንደመሆኑ በከፊል ጥሩ ቢሆንም፣ ያልተጀመረው ደግሞ ለመኪና እጅግ አደገኛ እንደሆነ ከምሽቱ የዝግታ ጉዞ ማስተዋል ይቻላል። የምንወጣው ዳገትና ቁልቁለት አካባቢው ተራራማ እንደሆነ ቢያሳብቅም፣ ጨለማ እንደመሆኑ ሩቅ ማየት ሳንችል ነው፣ ‹ያበራል ጥይቱ› እየተባለ የሚዘፈንላቸው ከላላዎች ምድር የገባነው።

ጉዟችን ጋስጫ ወደተባለው በጥንት ዘመን 47 መንፈሳዊ መጽሐፍትን ወደደረሱት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ነው። እንደ ደብረ ዳሞ ገዳም ዙሪያዋ በገደል የተከበበች ስትሆን በገመድ ፋንታ እንጨት በተረበረበበት ረጅም መሰላል ተወጥቶ የሚደረስበት ጥንታዊ ገዳም ነው። እንደደረስን እቃችንን ያለምንም ክፍያ ለበረከት ተሸክሞ፣ እየደገፈ ቀጭኑን ዳገታማ መንገድ አውጥቶና እግር አጥቦ እንግዳን በሚያስተናግድ ማኅበረሰብ ነው አቀባበል የተደረገልን።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ውጥንቅጥ የሚያስረሳ ሌላ ዓለም ውስጥ ያለን የሚያስመስል እርጋታና ዝምታ ውስጥ ገብተን፣ ከተማ የማናያቸውን የደመቁ ከዋክብት ቅርብ ያሉ እስኪመስለን አንጋጠን እየተመለከትን ሌሊቱን አጋምሰን ቀኑን በእንቅልፍ አገባደድን።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here