አፋር በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በተለይ የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ ከሚታወቁት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። በተለይ በድንቅ ተፈጥሮ የቱሪዝም መዳረሻነቱ የሚታወቀው አፋር ክልል ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካሳደረበት ተጽዕኖ ሳይላቀቅ፣ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በእጅጉ እንደጎዳው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብትነት የምትጠቀማቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እና የማይዳሰሱ ደማቅ የማኅበረሰብ በዓላት ያሏት አገር ናት። እነዚህን ሀብቶች ለመጎብኘት ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
ይሁን እንጂ ሳይጠበቅ ተከስቶ የዓለምን ኢኮኖሚ የተፈታተነው ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት 2012 ወዲህ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በእጅጉ እየተፈተነ ነው። በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 መከሰቱን ተከትሎ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ በ2013 በጀት ዓመት ከውጭ ጎብኚዎች ይገኝ የነበረውን ውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ መጠን ማሳጣቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም መፈተን የጀመረው ኮቪድ ከተከሰተበት 2012 ጀምሮ ሲሆን፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በ2013 መጀመሪያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሌላ ተደራቢ ፈተና ገጥሞታል።
ኮቪድ-19 በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ባሳደረው ጫና ተጎጅ ከሆኑት መካከል አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ የቱሪዝም መዳረሻ ፓርኮች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች እና በዘርፉ በተሠማሩ ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ግለሰቦችና አጋዥ ተቋማት፣ እንዲሁም በቱሪስት መዳረሻ አካባቢ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።
በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ኢትዮጵያ የምታገኘውን የቱሪዝም ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል። ኹለት ዓመት ሊሞላው አምስት ወራት በቀሩት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ወረራ ባደረገባቸው የአፋር አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ መሐመድ ያዩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አስተባባሪው እንደሚሉት የሰሜኑ ጦርነት በክልሉ ቱሪዝም ላይ ያሳደረው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው።
የሰሜኑ ጦርነት በክልሉ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሳደረው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው የሚሉት መሐመድ፣ ጦርነቱ ቱሪስት ወደ ክልሉ እንዳይመጣ ከማድረጉ በተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎች በጦርነቱ ጉዳት ያስተናገዱበት ሁኔታና የማኅበረሰቡ መፈናቀል ችግሩን ውስበስብ እንዳደረገው ያብራራሉ።
በሰላሙ ወቅት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚስቡት በዞን ኹለት ውስጥ የሚገኙ እንደ ኤርታሌ ያሉ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው። የኤርታሌ እሳተ ገሞራ በአፋር ክልል በዞን ኹለት የሚገኝ፣ ከባህር ወለል በታች 430 ጫማ (130 ሜትር) ዝቅታ ላይ ያለ ስፍራ ነው። ኤርታሌ በተለይ በውጭ ጎብኝዎች ከሚጎበኙ አካባቢዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን፣ የሰሜኑ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው ለጉብኝት ማቅናት የማይታሰብ ሆኗል።
በዚህም የተነሳ በአካባቢው በአስጎብኚነት፣ ግመሎችን በማከራየትና በተለያዩ ቱሪስት አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጦርነቱ ወደ አፋር ክልል ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሥራ አጥ መሆናቸውን አስተባባሪው ለአዲስ ማለዳ ይገልጻሉ።
ሰሜኑ ጦርነት በክልሉ የፈጠረው ችግር ከቱሪዝም ገቢ በላይ ሰዎች በሕይወት የመኖር አለመኖር ጉዳይ ነው የሚሉት አስተባባሪው፣ በክልሉ ከሚጎበኙ አካባቢዎች መካከል ቀዳሚ የሆነው ዞን ኹለት በእጅጉ የሚጎበኝ ቦታ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የቱሪዝም አገልግሎቱ ቆሟል ይላሉ። ክልሉ ከቱሪዝም የሚያገኘው ገቢ ከመቋረጡ በተጓዳኝ፣ በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አስጎብኚዎችና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለቱሪስቶች የሚሰጡ ሰዎች መተዳደሪያቸውን በማጣታቸው ለችግር መጋለጣቸውን አስተባባሪው ይናገራሉ።
የክልሉ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው ዞን ኹለት አሁንም ከጦርነት ቀጠና ውስጥ መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪው፣ አጠቃላይ እንደ ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎች ስጋት ውስጥ ናቸው ይላሉ። በዚህም በቱሪስት ገቢ ላይ የሰሜኑ ጦርነት አደጋ ፈጥሯል ነው የሚሉት አስተባባሪው። መጀመሪያውኑ ኮቪድ-19 ካሳደረው ተጽዕኖ ባልተላቀቀው ቱሪዝም ላይ ተደርቦ የመጣው ጦርነት፣ በቱሪዝም ዘርፍ የሚተዳደረውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ በእጅጉ እየፈተነው እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ባስተጓጎለው አፋር ክልል ቱሪዝም ክልሉ እንደ ክልል፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዲሁም እንደ ማኅበረሰብ የክልሉ ማኅበረሰብ ያጣው ገቢ ከፍተኛ ነው ይላሉ መሐመድ። አዲስ ማለዳ በአፋር ክልል በተገኘችበት ወቅት ከውጭ ጎብኚዎች አስከ አገር ውስጥ ጎብኚዎች ተቀብላ በሽር ጉድ የምታስተናግደው የክልሉ መዲና ሰመራ ከተማ ከነዋሪዎቿ ውጭ እምብዛም እንግዳ አይታይባትም ነበር።
አሁን ላይ ሰመራ ከተማ እንደወትሮው በክልሉ የሚገኙ ድንቅ የተፈጥሮ መስህቦችን ለመጎብኘት የሚያቀኑ ጎብኚዎችን ሳይሆን፣ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርሱ ወይም በአፋር ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ወደ ቦታው ያቀኑ እንደ ቀይ መስቀል፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የተባበሩት መንግሥታት ዓይነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ረጅ ድርጅቶችን ነው በብዛት የምታስተናግደው።
በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሠመራ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባባር በክልሉ በተከሰተዉ ጦርነት ምክንያት በዞን አራት (ፈንቲ ረሱ) እና ዞን አምስት (ሃሪ ረሱ) ባሉ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ላይ ጦርነቱ ያስከተለዉን ጉዳት እና የጉዳት መጠን ለመለየት የመስክ ጥናት ማድረጉን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። የጥናት ቡድኑ ያገኘውን ውጤት አዲስ ማለዳ የተመለከተች ሲሆን፣ ጥናት የተደረገባቸው ኹለቱም ዞኖች የሚገኙ ባህለዊና ታሪካዊ ቦታዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው በጥናቱ ላይ ተመላክቷል።
ጦርነቱ ዘለግ ላለ ጊዜ የተካሄደባቸዉና የትግራይ አጎራባች የሆኑ ወረዳዎች በአንጻራዊነት ከፍ ያለ የጉዳት መጠን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ጦርነቱ አጠር ያለ ጊዜ የቆየባቸዉና ራቅ ያሉ ወረዳዎች በአንጻራዊነት መጠነኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ጥናቱ ይጠቁማል።
በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት በተመለከተ በጥናቱ ይፋ የተደረገው፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸዉ አካባቢዎች የሚገኙ የወረዳ የባህልና ቱርዝም ጽሕፈት ቤቶች፣ በቅርቡ በአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተቋቋመ ሙዝየም፣ በአካባቢዉ የተቋቋሙ የባህልና የኪነት ቡድኖች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል።
ጥናቱ በተካሄደባቸዉ ኹለቱም ዞኖች ማለትም ዞን አራትና አምስት የሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች የባህል ማእከላት እና ከለዋን ወረዳ የሚገኘው ሙዝየም ከፍተኛ ዝርፍያና ውድመት የደረሰባቸዉ መሆኑን መገንዘብ እንደተቻለ የጥናት ቡድኑ አባላት ሀምዴ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሁሉም ወረዳዎች ላይ ጽሕፈት ቤቶች በደረሰባቸው ውድመት እና ዝርፊያ ምክንያት አሁን ላይ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጡበት ደርጃ ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል የሚሉት የጥናት ቡድኑ አባላት፣ በአንዳንድ ቦታዎች እንደተገነዘብነው ከሆነ የአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ የጽሕፈት ቤት ባለሞያዎች ቅርሶችን ለመታደግ አለመሞከርና ከዚያ በዘለለም የጥፋቱ ተሳታፊ ሲሆኑ ተስተውለዋል ብለዋል።
የጥናት ቡድኑ ባገኘው ውጤት መሰረት፣ ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ሐሳቦች በጥናቱ አካቷል። በዚህም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ እና የተዘረፉ እቃዎችን ከለጋሽ አካላት ይሁን ከሚመለከታቸው መፈለግ እና እንደአስፈላጊነታቸው ቅደም ተከተል በማሟላት እቅድ አዉጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
ሥራ ያቆሙ ጽሕፈት ቤቶችን በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገቡ ሙሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ የአካባቢዉ ማኅበረሰብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እቃዎችን የወሰዱ ካሉ እንዲመልሱ ማስተባበር እንደሚያስፈልግና፣ ታሪካዊው የአስበር መስጊድ ቅርስ ያለበት ሁኔታ እጅግ በጣም አስጊና አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልገዉ መሆኑን ጥናቱ ያሳስባል።
አፋር ክልል የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያላት ቅሪተ አካል ሉሲ ወይም ድንቅነሽ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1974 በክልል “ሀዳር” በተባለው ቦታ በአሜሪካዊዉ የቅሪተ አካል ተመራማሪ ዶናልድ ጆሃንሰን የተገኘችበት ነው። የሉሲ አጽም በተገኘበት “ሀዳር” የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው። የሙዚየሙ ግንባታ ለማስጀመር ክልሉ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን በትብብር እየሠራ ነው ተብሏል።
ክልሉ በጦርነት የተጎዳውን ቱሪዝም ለማነቃቃት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑንም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገልጻል። በዚህም በቅርቡ “ከፈንታሌ እስከ ኤርታአሌ” የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን ቢሮው ጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014



