የተጎዳው የላሊበላ ከተማ ቱሪዝም

0
1343

ከአዲስ አበባ ከ600 ኪሜ በላይ ርቃ፣ በስተሰሜን የምትገኘዋ ላሊበላ ከተማ እንደወትሮው የቱሪስት መኪና ሲወጣና ሲገባ ወይም ቱሪስቶች ሲርመሰመሱባት አይታይም። በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈረ፣ ለወትሮው በበርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኝ አስደናቂ ቅርስ የያዘች ከተማ አትመስልም።
ይልቅስ ወጣ ገብ በሚበዛባት ከተማ በመንገዶቿ የተወሰኑ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አልፎ አልፎ ሲሯሯጡ፣ እንዲሁም ነዋሪዎች ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከማየት የዘለለ የቱሪስት ከተማ ሊያስብላት የሚችል ሞቅታ በአሁኑ ወቅት የለም።
በተለይ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ካገኘች ወራትን ማስቆጠሯ ያለውን ችግር አባብሶታል ይላሉ ነዋሪዎቿ።

በከተማዋ ትንሽ መሸት ሲል አልፎ አልፎ የጀነሬተር ጩኸት ይሰማል። ሆኖም ግን ሰዓታትን ሳይቆይ ከተማዋ በጥቁር ጨለማ ትዋጣለች። ይህም የነዋሪዎችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ክፉኛ እንዳመሰቃቀለው ይገልጻሉ። በተለይ የከተማዋ የውሃ ችግር የመብራት ችግሩን መንስኤ አድርጎ የጎላ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ላሊበላ ከተማ አስደናቂ የሚባሉት የአስራ አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መገኛ እንደመሆኗ፣ የነዋሪዎቿ ሕይወት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከዚሁ ቅርስ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ይነገራል።

የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ
እንደ አገር የኢትዮጵያ ቱሪዝም ክፉኛ የተጎዳው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ሆኖም ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› የሆነው የሰሜኑ ጦርነት በተለይ ለላሊበላ ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ ፈተና ይዞ መምጣቱን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይስማሙበታል።
ይህን ሲገልጹም፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በርካታ ቱሪስቶች ይመጡ በነበረበት ወቅት ጫማ ከሚያጸዱና ጋሪ ከሚገፉ፣ ሱቅ በደረቴ ከሚሠሩ ጀምሮ እስከ ባለሀብቶች ዋናው የሕይወት መሠረታቸው ይህ ነበር። አሁን ብዙዎቻችን ሥራ ፈት ሆነን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነናል ነው የሚሉት።

ከአገር ውስጥ ቱሪስት የሚገኘው ገቢ ያን ያህል ነው ባይባልም ለአስጎብኚዎች ግን ቀላል የማይባል ነበር ይላሉ። አሁን ላይ ችግር ውስጥ የወደቁ ከ200 የማያንሱ የአስጎብኚ ማኅበራት መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የውጭ ጎብኚዎች የጉዞ እቅዳቸውን የሚያወጡትና ቆይታቸውን የሚያውቁት ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ስለሆነ፣ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሆኖ መቆየቱ፣ አሁንም ከስጋት ያልተላቀቀ መሆኑና አሰፈላጊ መሠረታዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ለመምጣት ዕቅዳቸውን እንዲሰርዙ አድርጓል ነው ያሉት።

በቤተ ክርስትያኑ ውስጥ አገልጋይ የሆኑት ዲያቆን ሙላት ላቀው፣ ከውጭ ጎብኚዎች በአማካይ እስከ 1 ሺሕ ብር እየተከፈለኝ በቀን ብዙ ቱሪስቶችን ሳስጎበኝ ኖሬያለሁ ካሉ በኋላ፣ ሆኖም ግን አሁን ላይ በሳምንት አንድ የውጭ ጎብኚ እንኳን ማስጎብኘት አልችልም ነው ያሉት።

ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት በቀን እስከ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ የውጭ ቱሪስቶች ይመጡ እንደነበር ገልጸውም፣ በዚህ ወቅት ግን በሳምንት ከኹለት በላይ የውጭ ጎብኝ አይመጣም ሲሉ ተደምጠዋል። በዚህ የተነሳም ዘጠኝ መቶ የሚደርሱ የገዳሙ መነኮሳት፣ ካህናት እና ልዩ ልዩ ሥራዎችን የሚሠሩ ሌሎች ሠራተኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም ቤተሰብ የሚመሩ ካህናትና ሠራተኞችን ሕይወት ለአደጋ አጋልጧል የሚሉት ሙላት፣ ጎብኚዎች ቢመጡም የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖሩ ከአንድ ቀን በላይ እንዲቆዩ አያደርግም ብለዋል።
የከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ አላማጣ ላይ መሆኑና ቦታው በሕወሓት ቁጥጥር ስር መሆኑ መብራት የማግኘት ተስፋችንን ሩቅ አድርጎታል ነው ያሉት።

ላለፉት ሦስት ዓመታት በኮሮና ቫይረስ እና በጦርነቱ የተነሳ ክፉኛ የተጎዳው የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደፊት በወረርሽኙ ምክንያት ተጥለው የነበሩ ዓለም ዐቀፍ የጉዞ እገዳዎች ከተነሱ እንዲሁም ቦታው አሁን ካለበት የዳግም ጦርነት ስጋት ነጻ ከሆነ ምናልባት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሊነቃቃ ይችላል የሚል ተስፋ ተይዟል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የከተማዋ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት ወደነበረበት መመለስ ለቱሪዝሙ መንሳሳት አይነተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ በተጨማሪም በርካታ ሆቴሎች በሕወሓት ወረራ ወቅት ዝርፊያና ውድመት እንደተፈጸመባቸው አንስተው፣ መንግሥት ሆቴሎችን መልሶ ለመገንባት መሥራት እንዳለበትና ከተማዋ ከቱሪዝም ውጭ የኑሮ አማራጭ ስለሌላት መንገድን ከመሳሰሉ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ጀምሮ የሚቻለውን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታም ከ40 በላይ የሚደርሱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ከ200 በላይ ሕጋዊ አስጎብኚዎች ከቱሪዝም እንቅስቃሴ መዳከሙ ጋር ተያይዞ ከሥራ ውጪ ናቸው ተብሏል። 206 በቅሎ አከራዮች እና 179 የሚሆኑ የቱሪስት ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዲሁ የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

የቱሪስት እንቅስቃሴው በምን መልኩ ሊነቃቃ ይችላል?
በከተማዋ በችግሩ ያልተጠቃ ማኅበረሰብ የለም የተባለ ሲሆን፣ ሕወሓት ከተማዋን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው አምስት ወራት ውስጥ የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶች ንብረት መዘረፉ ለመልሶ መቋቋሙ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱ ተመላክቷል።

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዲሴ ደምሴ (ዲያቆን) ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ የከተማዋ ኢኮኖሚ መሠረቱ ቱሪዝም መሆኑን ጠቅሰዋል። ሆኖም ቀድሞ በወረርሽኙ ከዚያም በጦርነቱ የቱሪስት ፍሰቱ መሉ ለሙሉ ቆሟል ማለት ይቻላል ነው ያሉት።

በዚህም ሆቴሎች፣ የቱሪስት ድጋፍ ሰጪዎች፣ በቅሎ አከራዮች እንዲሁም ካህናት በቀጥታ የተጎዱ ሲሆን፣ ሎሎች አጋር አካላትና የከተማው ማኅበረሰብ በአጠቃላይ ተጎድቷል ሲሉ ገልጸዋል።
የላሊበላ ከተማ በዚህ ወቅት በኢኮኖሚ ደቃለች ያሉት ኃላፊው፣ ለወራት በጨለማ ውስጥ የምትገኝ ከተማ መሆኗም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲቀንስ የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል።

‹‹የመብራት ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል ኹለት ጀኔሬተሮች መጥተው ነበር። ሆኖም በወር ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር ለነዳጅ የሚያስወጡ በመሆናቸው 20 ቀን እንኳን ሳያገለግሉ እንዲቆሙ ተደርጓል።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ውሃም እንዲሁ ከዝቅተኛ ቦታ ተስቦ የሚመጣ በመሆኑ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተገኘ አራት ሚሊዮን ብር ለአራት ወር የሚሆን ድጋፍ እስከ አሁን ሲቀርብ መቆየቱን አንስተው፣ ይህም ሊጠናቀቅ አንድ ወር የቀረው በመሆኑ ቀጥሎ ምን እንደምናደርግ አናውቅም ብለዋል።
ከወር በፊት በተለይ በገዳሙ ያሉ መነኮሳትና ካህናትን ለማገዝ በሚል በአዲስ አበባ የተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያን አስመልክቶም፣ የታሰበውን ያህል ችግር የሚፈታ እንዳልሆነና ታላላቅ ተቋማትም ያን ያህል እንዳልተሳተፉበት ገልጸዋል።

በተቋረጠው የቱሪስት ፍሰት የተነሳ ሆቴሎች ሲዘጉም ሠራተኞች ሙሉ ለሙሉ መበተናቸውን ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ከክልል እና ከፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አንስተውም፣ በተለይ ላቀረብነው የመብራት ጥያቄ የላሊበላ የመብራት ጉዳይ በዚህ ቀን ይፈታል የሚል ምላሽ የሰጠን አካል የለም ነው ያሉት።

የቱሪስት ፍሰቱን ወደ ነበረበት ለመመለስም ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በርከት ላሉ የቱሪስት ሠራተኞች የሥነ ልቦና ሥልጠና ተሰጥቷልም ብለዋል። ለቱሪዝም ፍሰቱ መነቃቃት ቢያንስ ሆቴሎች መብራት ማግኘት አለባቸው ያሉት ኃላፊው፣ የመብራት ችግሩ ቢፈታ በርካታ ተያያዥ ችግሮችም አብረው ሊፈቱ እንደሚችሉ ነው ያስገነዘቡት።

በተጨማሪም የአሜሪካን ጨምሮ፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችንና የዩኔስኮ ዳይሬክተሮችን ወደ ቦታው በመጋበዝ ዜጎቻቸው ወደ ላሊበላ መጥተው እንዲጎበኙ የማነቃቃት ሥራ እንዲሠሩ ግንዛቤ ፈጥረናል ሲሉ አክለዋል።

ጥቂት ስለቅርሱ
ቅርሶች አሁንም ድረስ የመሰነጣጠቅና የማርጀት አደጋ የተጋረጠባቸው መሆኑ በዐይን የሚታይ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፤ ነዋሪዎችም ያንኑ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከአደጋ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል የተሠራው ጥላ ፎቅ፣ ከ15 ዓመት በላይ መቆየቱ አደጋ ፈጥሮበታል ነው የተባለው።
ቅርሱ በመጠኑም ቢሆን ፀሐይና ዝናብ ማግኘት ያለበት ቢሆንም፣ አሁን ያለው መከላከያ ጥላ ፎቅ ቅርሱ ይህን እንዲያገኝ የማያደርግ በመሆኑ በቶሎ መቀየር እንዳለበት ተገልጿል።

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀውና በፈረንሳይ መንግሥት እርዳታ የሚሠራው ፕሮጀክት በአንጻሩ፣ ቀን ቀን እየተከፈተ ቅርሱ ፀሐይ እና ዝናብ እንዲያገኝ የሚያስችል፣ ክብደቱም ቀላል ሆኖ የሚሠራ በመሆኑ ይህን ችግር የሚፈታ ነው ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፤ የገዳሙ አገልጋዮች።
የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊው በበኩላቸው፣ በቅርቡ ከዩኔስኮ ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ምክክር መከላከያ ክዳኑን ለማንሳት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል። አያይዘውም ክዳኑ ሲነሳ ግን የሚቆሙት አምዶች አሰራርና አለቱ የት ላይ ነው የሚበሳው ከሚለው በተጨማሪ የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃውም እንዴት እንደሚሆን ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

ሂደቱም በችኮላ የሚደረግ ሳይሆን ሳይንሳዊ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን አመላክተው፣ ባለሙያዎቹ የአካባቢ ተፅዕኖ ዳሰሳ ጥናቱን ከጨረሱ በኋላም፣ በቅርቡ ሊያነሱት እንደሚችሉ አሳውቀዋል ነው ያሉት።
አዲስ ማለዳ ከአማራ ብሔራዊ ክልል ቱሪዝም ቢሮ እና ከቱሪዝም ሚኒስቴር ተጨማሪም ማብራሪያ ለማግኘት ደጋግማ ብትደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።
በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ አለት እንደታነጹ የሚነገርላቸውን አስራ አንዱ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ በ1970 በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here