ልጅሽ የአንቺ ነው!

0
1096

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አገር ቤተሰብ ከሚባል ትንሽ ከሚመስል ኅብረት ድምር የሚገኝ ውጤት ነው። አማካዩ የቤተሰብ አኳኋንም የአገር መልኮ ሆኖ መታየቱ አይቀርም። ብዙ ጥሩ ቤተሰብ አንድ ጥሩ ትውልድ፤ ከዛ አንድ ከትላንትናዋ የተሻለች አገርን ያስገኛል።

ቤተሰብ የሚባለው ይህ ኅብረት ወይም ተቋም ሲፈርስ፣ ሥራውንና ግዴታውን መወጣት ሳይችል ሲቀር፤ ይህም መጠኑ እየጨመረ ከሆነ ውጤቱ አገር ላይ በጉልህ ይታያል። ቢያንስ በጎዳና ላይ የምናያቸውን፣ በተለያየ ሱስ ተዘፍቀው የሚገኙትን ልጆችንና ወጣቶች ቁጥር ጨምሮ እናገኘዋለን። ከዛም <መንግሥት ለምን አያነሳቸውም?> ከሚል ጥያቄ፤ ቀስ በቀስ <ቤተሰብ ለምን ልጆቹን በአግባብ አይዝም?> ወደሚል ይደረሳል።

መንግሥትና የመንግሥት አሠራር ጎልቶ ይወቀሳል እንጂ፣ የቤተሰብ መድከም ትውልድ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው።
በዚህ መካከል የቤት ውስጥ የቤተሰብ ኃላፊነትና ድርሻ ሊናቅ አይገባም።

ወትሮ ልጅን ቀርፆ በወጉ በማሳደግ ውስጥ በቅርበት የነበሩ እናቶች ናቸው። ሥነምግባርን እንዳይረሳ አድርገው በልጆቻቸው ልብ ይከትባሉ። ልጆቻቸው በሁሉም የተሻሉ እንዲሆኑላቸው በመደገፍ ይከታተላሉ። አባቶችም በተመሳሳይ ድርሻቸውን ይወጣሉ።
የቤት ውስጥ ድርሻ አሁን የተናቀ ይመስላል። ግን ትልቅ ኃላፊነት ነው። አንዲት ሴት ሥራዬ ቤት ቆይቶ ልጆችን ማሳደግ ነው ስትል፤ በኩራት ልትለው ይገባል። የሥራ ሁኔታዋን ስለልጆችዋ ስትል የምትቀይር እናት ባደረገችው ልታዝን አይገባም።

ስለእናትነትና ብዙዎች ስለሚግባቡበት ትርጓሜው ሲባል አይደለም። የተሻለ ዜጋ ቀርፆ ለማውጣትም ነው እንጂ። አሁን ላይ የበተደጋጋሚ የሚባለውን <ሰላምና ሴቶች> የሚለውን ትስስር የምንቀበል ከሆነ፤ ትውልድና እናቶች መካከልም ያለው ግንኙነት ሊታይ ይገባል።
ሥልጣን ለያዘች፤ በሀብት ለተሳካላት፣ ብዙ ድርጅት ለከፈተችና ብዙውን ለምትመራ፣ መድረክ ስትናገር አንደበቷ በሚረታና የራስ መተማመኗ ለጎላ ሴት ብቻ አይደለም መዘመር ያለብን። እንዲያ ያለች ሴት እንድትገኝ ላስቻለ ቤተሰብ፣ ልጇ እንደዛ እንድትሆን ፍላጎቷን ሁሉ ለሰዋች እናትም ጭምር እንጂ!

እናም እህቴ! ልጅሽ የአንቺ ነው። በልጅሽ እድገትም ሆነ ቀጣይ ሕይወት ውስጥ ሱታፌሽ ወሳኝ ነው። ልጅሽን በአሉታዊ አስተሳሰብ፣ በአውሮፓና የባህር ማዶ ፊልምና በመሳሰለው አይወሰድብሽ። ልጅሽ የአንቺ ነው…የተሻለ ስርዓት የሚመጣው እንደአገርም ሴቶች የተሻለ ዓለም የሚሆንላቸው ልጅሽን በሚገባ ስታሳድጊ ነው። አትጠራጠሪ! የምትከፍይው መስዋዕትነት ይከፍልሻል፤ ትልቅ ዋጋም አለው።
ሕልምሽን አቆይተሽ ልጆችሽን ቤትሽ ቆይተሽ ማሳደግን የመረጥሽው እህታችን ሆይ! እናከብርሻለን! ቤተሰብሽንም እናመሠግናለን!

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here