እግረኛው ሕዝብ

0
1691

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም በደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ ገዳም ነው። ብዙዎች እንደሚያውቁት እንደ ደብረ ዳሞ ገዳም ጠረጴዛ የመሰለ ተራራ ጫፍ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ብቸኛ መወጣጫውም እንደመሰላል ተደርጎ የተረበረበ የእንጨት ክምር ነው።

ገዳሙ ለመሄድ ከደሴ ወደ ደቡብ ወሎ፣ በገራዶ አድርጎ ወደ ወረዳው የሚወስደውን መንገድ መከተል አንዱ አማራጭ ነው። ሌላው ደግሞ አሁን እየተሠራ ያለ የወሎ ደቡባዊ ጫፍ ላይ ካሉ ከተሞች አንዷ ከሆነችው ጃማ ደጎሎ ተነስቶ የሚጓዝ አዲስ መንገድን ተከትሎ የሚኬድበት ነው። ይህ መንገድ በቅርቡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክልል በነበረው ጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ከጦር ቀጠናው ሸሽተው የወጡበት መሆኑ ይነገርለታል።

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የሚገኝበት ጋስጫ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ እጅግ ኋላቀር ሊባል የሚችል አካባቢ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን መመልከት ይቻላል። ሙሉ ቀን መኪና ዝር የማይልባቸው መንገዶችን ማየት አያስገርምም። መኪና ሲዘልቅ ግን ትኩረትን የሚስብ ሂደት መሆኑን ከነዋሪዎቹ ሁኔታ መመልከት ይቻላል። ከገዳሙ ወረድ ብሎ ያለ ወንዝ አካባቢ የሚገኝ እርሻ አካባቢ መኖሪያ ቤት የሚባል ጭራሽ አይታይበትም። አልፎ አልፎ ዝር ከሚሉ ውሃ ለማጠጣት ከሚመጡ ከብትና ፍየል ጠባቂዎች በቀር፣ ነዋሪ እንደልብ የሚታይበት አካባቢ አይደለም።

ወቅቱ በጋ እንደመሆኑ አካባቢው መራቆቱ በግልፅ ይታያል። ዐይን ማየት እስከሚችልበት ድረስ ምንም ዓይነት የደን ሽፋንን ማየት አይቻልም። ቦታው ተራራማ እንደመሆኑ የሚታረሰው መሬት ድንጋያማነት ሲያዩት ያሳዝናል። ለዓመታት የታረሰ አብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ እርሻ ድንጋያማ ቢሆንም፣ አንዳንዱ አፈር ማየት እስኪያቅት ድረስ ኮረኮንቻማ ሜዳ እንጂ ማሳ አይመስልም። የተወሰኑት ድንጋዩን አንስተው ዳር ዳር አጥር አስመስለው እርሻቸውን እንደ እርከን ለመጠበቅ ቢጠቀሙበትም የሚያልቅ አይመስልም።

እርሻቸው በድንጋይ የተሞላባቸው አርሶ አደሮች ከሚያሳጣቸው ምርት ባሻገር የሚያስከትልባቸው ድካምም ያሳዝናል። ለእነሱ ብቻ ሳይሆን የሚያርሱባቸውን ከብቶች በማድከምም ውጤታማነታቸውን እንደሚቀንስባቸው ይናገራሉ። በተቃራኒው ደግሞ መሬቱ ተዳፋት ያለው ከሆነ በቶሎ ተሸርሽሮ ለሙ መሬታቸው እንዳያልቅባቸው ድንጋዩ በተወሰነ ደረጃ እንደሚከላከልላቸው የሚናገሩም አሉ።

ወደ ገዳሙ ሕይወት ስንመለስ፤ ነዋሪዎቹ መነኮሳትና ካህናት ብቻ አይደሉም። የቆሎ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የአብነት ተማሪዎችም ከጎጃም ጭምር ከሩቅ የመጡ አዳጊ ልጆችን መመልከት ይቻላል። እነዚህ አዳጊዎች የሚማሩት የቀለም ትምህርትን ብቻ ሳይሆን ሥነምግባርንም በመሆኑ፣ እንግዳ ሲመጣ እግር አጥቦ ከመቀበል ጀምሮ እቃ ተሸክምው ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ አድርገው ይሸኛሉ።

እድሜያቸው ከ12 ጀምሮ እስከ 16 የሚሆኑት በተለይ ያለምንም ማመንታት ለማገዝ ሲጣደፉ ማየት ምነው ኹሉም ልጆች እነሱ ባለፉበት የሥነምግባር መንገድ ታንጸው ባደጉ ያስብላል። የገዳሙን ቆይታችንን ጨርሰን ልንወጣ ስንል፣ እነዚህ ልጆች ድንገት ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው አብረው ለመጓዝ ለመንፈሳዊ ዓላማ ከመጣ የማኅበር መኪና ጎን ተኮልኩለው ነበር።

ቀጣይ ጉዟችን ሦስት ሺሕ ዓመታትን ልታስቆጥር 4 ዓመታት የቀሯት ተድባበ ማሪያም ነበር። የአማራ ሳይንት ዋና ከተማ ከሆነችው አጅባር 25 ኪሎሜትር የምትርቀው ይህች ጥንታዊትና ገናና ቤተክርስቲያን፣ ከአራቱ ዋና ዋና የኢትዮጵያ ደብሮች መካከል የምትጠቀስ ናት። ዓመታዊ የንግሥ በዓል የሚከበርበት የግንቦት ልደታ ቀን ለመገኘት የአካባቢው ምዕመን ብቻ ሳይሆን ሌላውም ከሩቅ ይመጣል። ቦታው እጅግ ተራራማ ከመሆኑ የተነሳ ለእግር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለተሽከርካሪም በጣም አስቸጋሪ ነው።

ክብረ በዓሉ ላይ በመገኘት ከከተማ የመጡ ጳጳሳትን አግኝቶ ድቁና ለመቀበል የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ተማሪዎች የማኅበሩ መኪና እንዲያሳፍሯቸው ከምሽት ጀምረው ነበር በአባቶች አማካይነት ከማኅበሩ ባለቤት ጋር ቃል የተገባቡት። ጠዋት ግን ከታሰበው በላይ ስለመጡ 10 ተማሪዎች ተፈቅዶላቸው በክፍት ቦታና ትርፍ ሆነው ተጓዙ። ከ13 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ ተቀራራቢ እድሜ ላይ ያሉት እነዚህ ተማሪዎች በጣም የሚተሳሰቡ ናቸው። ዐስሩም ለቀናት የሚሆናቸውን ስንቅ የያዙት አንድ ላይ በአንድ አነስተኛ ማዳበሪያ የተቋጠረ ድርቆሽን ብቻ ነበር።

አንዳንዶቹ የሚቀይሩት ልብስ እንኳን ሳይኖራቸው ያጣፏት አነስተኛ ኩታ ስር የተቀዳደደ ልብሳቸውን እንዳደረጉ ነበር ለምርቃታቸው የሚጓዙት። ይህን እድል ያገኙት መኪና አካባቢያቸው ስለመጣ እንጂ፣ የማኅበሩ መኪና ባይኖር ጭራሹኑ ድቁናቸውን በዛን ወቅት ማግኘት ባልቻሉ ነበር።

የተማሪዎቹ ችግር የጉስቁልናና የምግብ አልያም የአልባሳት ሳይሆን በቀላሉ የማይፈቱት የትራንስፖርት እጥረትና ጭራሹኑ መጓጓዣ አለመኖር ነው። በአገሪቱ ካሉ ትላላቅ ተቋማት በቀዳሚነትና በግዙፍነት ከሚጠቀሱት በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ቤተክርስቲያን፣ ተተኪ ተማሪዎቿን የምታጓጉዝበት እንደዘመኑ ሥልጣኔ እንግልታቸውን የሚቀንስላቸው ተሽከርካሪ ማመቻቸት አለመቻሏ ያስገርማል።

ስንት ሕንፃዎችና የተለያዩ ገቢ ማስገኛ መንገዶች ያሏቸው አብያተ ክርስቲያናት በትራንስፖርት ረገድ ካህናቱንና ተማሪዎችን ከችግራቸው መታደግ አለመቻላቸው ያሳዝናል። ምዕመናንም ቢሆኑ ለተለያዩ ማኅበራት ብዝበዛ ሲጋለጡ እየታየ፣ እንደ ቅልቅ ተቋም ምንም ስርዓት የሚያሲዝ ሕግም ሆነ አማራጭ ተሽከርካሪ ማቅረብ አለመቻሉ ልብን ይነካል።

በዚህ ዓይነት አማራጭ እጦት ሳቢያ ወደ አንዳንድ ደብሮች የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች በአንድ ማኅበር በኩል ብቻ እንደሚደረጉም ይሰማል። ከአንዱ ማኅበር ውጪ ሌላ እንዳይደርስ ከሚደረግባቸው ታላላቅ ደብሮች መካከል በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ደብሮች በቅሬታ መልክ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ብሶቱን ምንም ሳይፈራ ቢናገርም የሚሰማው በማጣቱ ምሬቱን ይገልፃል።

በእንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ጉዳዮች መንግሥት እጁን ማስገባት ስለመቻሉ የሚከራከሩ ቢኖሩም፣ ማኅበራት ከተጓዡ ከሚያገኙት ገቢ ግብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በመጥቀስ የተጓዡን መብትም በተመለከተ ሕግ ሊበጅ ይገባል የሚሉ አሉ።

ስለማኅበራቱ ይህን የጠቀስኩት ወደ ተድባበ ማርያም አብረው የተጓዙት ተማሪዎች የገጠማቸውን ለማውሳት ነው። መኪናው አድርሶ እስከ ገዳማቸው መገንጠያ ሊመልሳቸው ቃል ገብቶ እንደወሰዳቸውና እንደተካዱ በመጥቀስ፣ በማብቂያው ሲያዝኑ ስለመተለከትን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። በግሉ ተጉዞ ክብረ በዓሉን አክብሮ ሊመለስ ከነበረ ምዕመን መካከል ወደ አዲስ አበባ ውድ የሚባል ብር ከፍለው መመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ሲገኙ፣ የማኅበሩ ባለቤት እነዚያን ታዳጊ ዲያቆናት ውረዱና በእግራችሁ አገራችሁ ግቡ ማለቱ ነው።

ይህን ያላቸው በመመለሻቸው ቀን ዋዜማ ላይ እራት ጋብዞ እንደሆነ የሰሙ የማኅበሩ ተጓዦች ወሬውን አሰራጭተዉታል። ልጆቹ ብር ቢኖራቸው እንኳን የማያውቁትን አገር አቆራርጠው እንዴት እንደሚገቡ ነበር የጨነቃቸው። ሰውየው በመንፈሳዊ ጉዞ ሥም ይህን ማድረግ እንደሌለበት ቢነገረውም፣ “ምን አገባችሁ! የሚያዋጣኝን እኔ ነው የማውቀው። ከፈለጋችሁ ከፍላችሁ በሌላ አሳፍሯቸው” ብሎ ሜዳ ላይ ጥሏቸው እንደሚሄድ ያረጋግጣል። በሁኔታው ያዘኑና የቻሉትን ሲያደርጉላቸው የነበሩ በመለየታቸው ያዘኑ ተጓዦች፣ ብር አዋጥተው ሊያሳፍሯቸው ቢሞክሩም መኪና ባለመኖሩ በእግራቸው ለመጓዝ ተገደዋል።

25 ኪሎሜትር ዳገትና አነስተኛ ቁልቁለትን ግማሹን ቀን ተጉዘው ምሽት የደረሱበት ቤተክርስቲያን አድረው በነጋታው ግማሽ መንገድ የሚያስኬዳቸውን መኪና ተሳፍረው ብዙውን መንገድ በእግር ተጉዘው በሦስተኛው ቀን ገዳማቸው መግባታቸውን ስልክ ደውለው ላዋጡላቸው አሳውቀዋል።

ይህ ዓይነት ተግባር ባለማኅበሩን ብቻ የሚያስኮንን ሳይሆን፣ ትራንስፖርት ፈላጊ ባለበት መኪና መመደብ የሚጠበቅበትን መንግሥትን ጭምር ነው። ከሁሉም በላይ ግን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪ ማቅረብ የሚችሉ የእምነቱ ተከታዮችም ሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ፣ በትራንስፖርት ረገድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ማስተዋል ይቻላል።

የጉዟችን መዳረሻ የሆነችው ተድባበ ማርያም የሚገኘው ምዕመን ቁጥር በቅርብ ርቀት ካለው ግሸን ከሚመጣው ጋር ባይወዳደርም፣ ከልምድ ማነስ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ የተቀላጠፈ መስተንግዶም ሆነ መጓጓዣ የለም። አብዛኛው በእግሩ ተጉዞ የመጣ ሲሆን ጥቂት በማኅበር ሌላው ደግሞ በትራንስፖርት የመጣ እንደሆነ ከተሽከርካሪዎቹ ብዛትና ዓይነት ጋር እያነፃፀሩ መናገር ይቻላል። ብዙኀኑ መሬት እንዳደረ ሁሉ በዓሉ ሲያበቃ መሬቱን ሳይለየው ወደየመጣበት በእግሩ የሚኳትን ነው።

ጥቂቶች ባገኙት ተሽከርካሪ ለመጠቀም ሲጋፉ ይታዩ ነበር። ጭነት መኪኖች ላይ እንደሰርዲን ብሎ መግለፅ እፍንፍኑን ባያስረዳውም፣ ፊቱ መፈናፈኛ እስኪያጣ ተጨምቆ 25 ኪሎ ሜትሯን የመጀመሪያዋን ጉዞ ለመሳፈር 150 ብር ሲጠየቅ ሳያመነታ ለመክፈል ሲጋፋ የሚታየው ሕዝብ ምን ያህል ተራራማነቱን እንደሚፈራው የሚያሳይ ነው።

ወንበር ይዞ መጓዝ ብርቅ የሚሆንበትና እንደኛ መመለሻ የማያሳስበው ምን ያህል የታደለ እንደሆነ ለመመልከት ዞር ዞር ማለት አይጠበቅም።

ይህን የመሰለ የትራንስፖርት ችግር ያለበትን ኅብረተሰብ ትተን ያመራነው ወደ ጎጃም ግዛት ነው። ከአክሱምና ተድባበ ማርያም ቀጥላ ርዕሰ አድባራት የሆነችው ትንታዊቷ መርጦ ለማርያም ገዳም መተላለፊያ ስለሆነች አስፋልት ያቋርጣታል። ለተጓዥ ምቹ የመሆኗን ያህል ግን ጥንታዊ የፈራረሰ ቅርሷን የሚጎበኝ ሕዝብ እምብዛም የለም። ጥንታዊ የሚያምር የቤተክርስቲያን ቅሪትን ጨምሮ የተለያዩ ድንቅ ድንቅ ቅርሶችን ብትይዝም፣ ከወቅታዊው ሁኔታ አንፃር እንደተድባበ ማርያም ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርበው ጥቂቱ ነው።

ምሥራቅ ጎጃም ከአባይ ወንዝ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ይህችን ቦታ በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ መሠራት እንዳለበት የሚያሳብቁ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ከሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የማያንስ እንዲያውም ጥናት ቢደረግ ሊልቅ የሚችል ቅርስን ይዛ መደነቂያዋን ጊዜ በአርምሞ የምትጠብቅ ይመስላል።

ከመርጦ ለማርያም ቀጥሎ ደብረወርቅ የተሰኘችውና ጉልላቷ በወርቅ የተሠራችውን ጥንታዊት ገዳም ከተመለከትን በኋላ፣ ወደ ገናናዋ ዲማ ጊዮርጊስ ገዳም ፒስታ መንገድ ታጥፈን ነበር ያመራነው። በፍቅር እስከ መቃበር የምትታወቀውን ይህችን ደብር ተሳልመን የተመለስነው በዛው መንገድ በመሆኑ የመሬቱን ለምነትና ሜዳማነት ማስተዋል ችለናል።

ከዓባይ ሸለቆ ውጭ አዲስ አበባ እስከምንገባ ለቀናት የተጓዝነው አብዛኛው መንገድ ሜዳማ ቢሆንም፣ አንድም ትራክተር ሥራ ሲሠራ አይታይም። አማራ ሳይንት ውስጥ የምትገኝ ተድባበ ማርያም ከሚወስደው መንገድ ተገንጥለን ስንጓዝ ከምትገኘው እዋ ከተማ አቅራቢያ ቆሞ ካየነው አንድ ትራክተር ውጪ፣ ምንም ዓይነት ዘመናዊ ማረሻ የሌለው ሕዝብ ነው።

ሕዝቡ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ ዳዴ ማለት ከጀመረ አንስቶ ኑሮው በሙሉ መሬት ላይ ነው ማለት ይቻላል። ለትምህርት ሩቅ ሲሄድ በእግሩ፤ ሲያርስ በእግሩ ገበያም ሆነ ለሕክምና ከመንደሩ ሲወጣ እግሩን ተጠቅሞ ከሚወጣው ከዚህ ምስኪን ሕዝብ፣ ከፊሉ አብዛኛውን ጊዜውን በባዶ እግሩ ማሳለፉ ደግሞ ይብስ ያሳዝናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here