ደብረ ታቦር ሆስፒታል በተለያየ የግብዓት ዕጥረት ምክንያት ለሕሙማን ሲሰጠው የነበረው ሙሉ አገልግሎት በከፊል መቆሙን የተቋሙ ሠራተኞችና ሕሙማን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የተቋሙ ሠራተኛ ከፓራሲታሞል ጀምሮ ትላልቅ የሕክምና ግብዓቶች፤ የጓንት እና የሌሎች መድኃኒቶች ዕጥረት አጋጥሟል ብለዋል። ሠራተኛው የእጅ ጓንት ሳይቀር መድኃኒቶችን ከውጭ (ከግል ፋርማሲ) እንደሚገዛ ጠቁመው፤ በተጨማሪም ሲቢሲ ማሽን ስለማይሠራ አገልግሎቱን ማግኘት የሚቻለው ውጪ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ስፔሻላዝድ ተብሎ የሚጠራው ሆስፒታል ሠራተኞቹንና ሕሙማኑን በጤና ጣቢያ ደረጃ እንኳ ሊያስተናግድ የማይችልበት ደረጃ እንደደረሰ ነው የተብራራው። ታካሚዎች በበኩላቸው፣ የመድኃኒት ማዘዣ ወረቀት ኮፒ አድርጋችሁ በማባዛት አምጡ እንባላለን ነው ያሉት። የማኅበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድኅን አባል መሆን ጥቅሙ የት ላይ ነው? ሲሉ የሚጠይቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ወረቀት ኮፒ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቁሳቁሶችን ከፋርማሲ በመግዛት ለማሟላት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
ድንገተኛ ክፍልን ጨምሮ በእያንዳንዱ የሕክምና መስጫ ክፍል እስከ አራት ሰዓት ድረስ፣ ከካርድ ክፍል ውጭ ሥራ ስለማይጀመር ሕሙማን ሲጉላሉ ይስተዋላሉ ነው የተባለው። አራት ሰዓት ሐኪሞቹ ከገቡ በኋላም የካርድ ክፍል ሰልፍ ሌላኛው ችግር የሚታይበት ቦታ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ድንገተኛ ክፍል የሚታከምም ሆነ በተመላላሽ ሕክምና ክፍል የሚታከም እኩል ነው የሚስተናገዱት ብለዋል።
በለጠ ማሩ ሰሞኑን ወደ ሆስፒታሉ ለመታከም እንዳቀኑ ገልጸው፤ የእጅ ጓንት ፋርማሲ እንደገዙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአካባቢው በሚገኙ ፋርማሲዎችም አንድ የእጅ ጓንት (ግላብ) እስከ 40 ብር እየተሸጠ መሆኑን አንስተዋል።
ሆስፒታሉ መድኃኒትም የመደኃኒት ማዘዣ ወረቀትም ዕጥረት አለበት የተባለ ሲሆን፤ ድንገተኛ ክፍልንና ማዋለጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሕክምና እየተሰጠ አለመሆኑም ተነግሯል።
ሌላኛው ማረው ዓለሙ የተባሉት ቅሬታ አቅራቢ በሆስፒታሉ ውስጥ የማስታገሻ መድኃኒት እንደሌለ አንስተው፣ ከቀላል እስከ ከባድ የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚሹ ሕሙማን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ አብራርተዋል።
ሆስፒታሉ በጀት የለውም የሚሉት ሠራተኞቹ፤ ከሦስት እስከ አምስት ወር የሚሆን ደመወዛቸው አልተከፈለንም ብለዋል። በመሆኑም ሠራተኞች ግንቦት 24/2014 ሰላማዊ ሰልፍ ቢያደርጉም መፍትሄ እንዳላገኙ ነው የተናገሩት።
በሰላማዊ ሰልፉ የተሰጣቸው ምላሽ “በጀት አልቋል፤ የለንም። ወታደሩ ተጠቅሞታል” የሚል መሆኑን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል። ሠራተኞቹ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አበል ጤና ቢሮውን ሲጠይቁ የተሰጣቸው መልስ መጀመሪያ ለምን አገልግሉ ሳንላችሁ በሪፈራል ደረጃ አገልግሎት የመስጠት ሥራ ጀመራችህ የሚል መሆኑን ነው።
እንደ ቅሬታ አቅራቢ ባለሙያዎቹ ገለጻ ከሆነ፤ ሆስፒታሉ ወደ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሲያድግ፣ ጤና ቢሮ ለሆስፒታሉ በሚሰጠው ማሳሰቢያ ጀምሩ ሲል በአዲስ የሥራ መደብ/ደረጃ አገልግሎት መስጠት ትጀምራላችሁ የሚል መሆኑን ነው።
በመሆኑም፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዳሬይሬክተር አዲሱ ዋሴ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ጥያቄ አላቀረበልንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ስለ ችግሩ የሰማሁት ነገር የለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የበጀት ዕጥረት ሊኖርበት ይችላል ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014



