በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ500 ሚሊዮን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።
የቴክኒክ ኮሚቴው እንደገለጸው፣ መርሐ ግብሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ያስችላል ብሏል።
በየዓመቱ 92 ሺሕ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺሕ ሄክታር ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ የዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል ተብሏል።
ይህም ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ እና ላለፉት ሦስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ተመናምኖ የነበረው የተፈጥሮ ሀብት እንዲያገግም መደረጉ ተመላክቷል።
አሁን በመላው አገሪቱ ያሉት የችግኝ ጣቢያዎችም 120 ሺሕ መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በሥራ ፈጠራ ረገድ በርካታ የሥራ እድልን መፍጠር የቻለ ነው ተብሏል።
አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና አፕል በዋናነት ለምግብነት ከሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በዘንድሮው የችግኝ ተከላ የሚተከሉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
እነዚህ ችግኞች በቀጣዮቹ ዓመታት ራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድጉ ነው የተገለጸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014


