ከኹለት ዓመት በፊት ይጀመራል ተብሎ 277 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እስከ አሁን የዘገየው የቀበና ወንዝ ዳር ልማት በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ከተማው (ኢ/ር)፣ ፕሮጀክቱ ከጣሊያን መንግሥት በተገኘ 277 ሚሊዮን ብር እንደሚሠራ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከኹለት ዓመት በላይ ሊጓተት የቻለው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎችን የማልማት ፕሮጀክት በአገራችን አዲስ ስለሆነ እና ሥራውም ውስብስብ በመሆኑ ባህሪውን ተላምዶ ቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ መሆኑን ተከትሎ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም አማካሪ ድርጅቶችን የመቅጠር ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቁመው፣ ኮንትራክተሮች የጊዜ ሰሌዳው እንዲራዘም በመጠየቃቸው በመጪዎቹ 15 ቀናት ውስጥ እናሳውቃለን ሲሉ ገልጸዋል።
በመቀጠልም በአማካሪ ከጸደቀ በኋላ፣ በዘንድሮ ዓመት የጨረታና ዲዛይን ሥራው ካለቀ በሚቀጥለው ዓመት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንገባለን ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚሁ ፕሮጀክት ሥራ ተብሎ ከተማ አስተዳደሩን፣ ጣሊያን ኤምባሲን፣ ፕሮጀክቱ የሚያርፍባቸው ወረዳዎችን እና የካ ክፍለ ከተማን ያቀፈ ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙንም አክለዋል።
በሌላ በኩል፣ በ“ጫካ ፕሮጀክት” ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን የቀበና ወንዝ ለማልማት በኪሎ ሜትር አስቀድሞ የተያዘው ዕቅድ የሚቀንስ መሆኑን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገልጿል።
ፕሮጀክቱ ቀድሞ በተያዘለት ዕቅድ እስከ ወረዳ 10 የሚደርስ እንደነበር አንስተዋል። በቅርቡም በጫካ ፕሮጀክት ሰው ሠራሽ ሀይቆች እና ኩሬዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በሚል ወደዚህ እንዲቀንስ ተደርጓል ነው ያሉት። ሆኖም ምን ያህል ኪሎ ሜትር ሊቀንስ እንደሚችል እስከ አሁን የተገለጸ ነገር እንደሌለ አንስተዋል።
ቢሮው እንዳስታወቀው፣ በፈረንጆች 2020 ይጀመራል ተብሎ የነበረው የቀበና ወንዝ ዳርቻ የማስዋብ ፕሮጀክት፣ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ያህል ይሸፍናል ተብሎ የተያዘ ነበር።
በዚህም ከጀርመን ኤምባሲ እስከ አንቆርጫ (ኦሮሚያ ድንበር) ድረስ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን በመሀል የጫካ ፕሮጀክት በመግባቱ ከጀርመን ኤምባሲ እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ ብቻ የሚሸፍን ይሆናል ነው የተባለው።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ወንዙን ውብና ፅዱ፣ የማኅበረሰብ መዝናኛ ማድረግ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ሥራው ሲጠናቀቅ ከማኅበረሰቡ የሚወጣ ፍሳሽና የሽንት ቤት ቆሻሻ ወደ ወንዙ እንደማይገባ አስረድተዋል። እንዲሁም መሸጋገሪያ ድልድዮችና የስፖርት ማዕከላት፣ የብስክሌት መንገዶች ይኖሩታል ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህ ፕሮጀክት የሚፈናቀሉ ሰዎች እንደማይኖሩ አንስተውም፣ ‹‹የፕሮጀክቱ ዓላማ ማፈናቀል አይደለም፣ የሚፈናቀል ማኅበረሰብ ይኖራል ብለንም አናስብም። በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሳቢያ የሚፈናቀል ሰው ቢኖር እንኳን በጣም ጥቂት ነው።›› ብለዋል።
የቀበና ወንዝ ዳርቻን በማስዋብ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅቶችን ለመቅጠር የወጣው ጨረታ አገር ዐቀፍ ሲሆን፣ ኮንስትራክሽን ድርጅቶችን ለመቅጠር ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ዓለም ዐቀፍ ጨረታ መሆኑም ተጠቁሟል።
የጣሊያን መንግሥት ከበጀት ድጋፉ በተጨማሪ መሉ በሙሉ የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል ነው የተባለው። ፕሮጀክቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚታሰብም ቢሮው አመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014



