መንግሥት ከፍረጃ ይቆጠብ!

0
849

ኢትዮጵያ ውሉ በጠፋበት በማይቆረጥ ገመድ እንዲህ ተተብትባ በተያዘችበት ወቅት፣ እስራቷን የሚያጠብቅባት ሌላም ዙር ውስብስብ ቋጠሮ ውስጥ ገብታለች። ችግሯ ቀስ በቀስ ይፈታል እያለ የሚጠብቀው የኅብረተሰብ ክፍል ተስፋ እየቆረጠ፣ ሁኔታዎችም እየተባባሱ መምጣታቸውን ማንም መመልከት የሚችለው ሀቅ ነው።

አሁን ላለንበት አዙሪት ዋናው ተጠያቂ መንግሥት ነኝ ያለው አካል መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህ ለመሆኑ የማንንም አስተያየት መጠየቅ ሳያስፈልግ መንግሥት ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ መመልከት በቂ ነው። የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ሰኔ 1 ቀን ይፋ ባደረገውና በእለቱ የሕግ ማስከበሩን ዘመቻ ገምግሞ ያንኑ እለት ያወጣው መግለጫ እንደሚያትተው፣ ነገሮች እጅግ እየተባባሱ መምጣታቸውን ነው።

በኦሮሚያ ክልል በጠላት እጅ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ጭምር አስመልሻለሁ ብሎ ሸኔ ምን ያህል መሬት ተቆጣጥሮ እንደነበር ባይጠቅስም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስተዳድረው ይዞታ እንደነበረው መንግሥት አምኗል ማለት ይቻላል። የመንግሥት ጠላቶች የተባሉትን የአገር ውስጥ የኃይል ሚዛንን ከመንግሥት ወደራሳቸው ያዞሩትን ዘርዝሮ አኩሪ ሥራ ተሠርቷል ያለው ይህ መግለጫ፣ ለብዙዎች ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን የሱዳኑንም ሆነ የሰሜኑን ጦርነት ስጋት በተመለከተ ያለው የለም።

መንግሥት ልፍስፍስ ነው ብሎ ሕዝቡ እንዲረዳ ያደረገው ሆደ ሰፊነቱ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው፣ ለምን ይህን ያህል ጊዜ አገር እንዲህ እስክትሆን መንግሥት በትዕግስት እንደጠበቀም የተናገረው ነገር የለም። የመንግሥትን መዋቅር ስለማጥራት የሚያወራው የመግለጫው አካል የተሳካ ባላቸው እርምጃዎች በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልል የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውንና መቀጠላቸውን እንጂ ምን ያህል እንደሚቀረው ሳያስቀምጥ አልፏል።

በአጠቃላይ፣ መግለጫው በታጠቁ ኃይሎች ላይ በሠላማዊ ወቅት ስለሚወሰድ እርምጃ የሚያትት ቢሆንም፣ አሁን አገሪቷ ጦርነት ውስጥ ሳትሆን ሰላም ሰፍኗል ብሎ መንግSeት እንደሚያስብ ማመላከቱን አዲስ ማለዳ ትረዳለች። “አገር ሰላም ስትሆን ደግሞ ሁሉም ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ ይገባል” በማለት ስለወቅቱ ያለውን አረዳድ በግልጽ አንፀባርቋል።

በተለያየ አቅጣጫ የጦርነት ነጋሪት በሚጎሰምበት በአሁኑ ወቅት፣ እርዱኝ ተብለው የታጠቁ ላይ ቀድሞ እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑ ምን ያህል የመንግሥት ትኩረት ከፓርቲ ሕልውና ጋር የተቆራኘ መሆኑንም ያሳያል። ለዚህም አባባል “የፖለቲካ መዋቅሩ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት“ ፈፅሞታል የተባለው ተግባር በመላው ሕዝብ እንደተደረገ ያትታል። ይህ ዓይነት አቀራረብ መንግሥት የፈረጃቸውንም ሆነ ራሱን የሕዝብ አካል እንዳልሆነ የሚያመላክትና የድሮው አስተሳሰብ አሁንም እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ፤ ሊቆም ይገባል።

እንዲህ ያለው የራስን ሕልውና ለማስቀጠል የአገርን ደኅንነት እንደማስፈራሪያ አድርጎ የመጠቀም አባዜ ሊቀር የሚገባ የቀደመው ዘመን መገለጫ ነው። ይህ ስለሆነም ተጠርጣሪ መባል የነበረባቸው እንደ ወንጀለኛ ተፈርጀው በከሰሳቸው አካል ይታደናሉ። የፍርድ ሂደቱም ብዙ ሊያስብል የሚችል የልጆች መጫወቻ ስለመምሰሉም በየችሎቱ የቀረቡ ክሶችና አመክንዮዎች አስረጂ ናቸው።

ከመግለጫው ውስጥ የበለጠ ትኩረት የሚስበው ስለሚዲያና አክቲቪስቶች የተነገረው ሲሆን፣ ሥራቸው አገር ማፍረስ እንደሆነ ሕዝብን ለማሳመንና ለመነጠል የተሞከረበት ነው። የመንግሥትን ንዝህላልነትም ሆነ ጥፋት ማጋለጥ አገርን እንደማፍረስ ተደርጎ በፍፁም ሊወሰድ እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በመግለጫው፣ “ሕገ ወጥነት – የብሔርን፣ የሃይማኖትን፣ የፖለቲካ ቡድንን ወይም የሚዲያና የአክቲቪስትነትን ካባ ቢደርብም፣ ሕገ ወጥነት መሆኑ አይቀርም። አይጥ ምንም ዓይነት ቀለም ብትቀባ አይጥ መሆኗና ንብረት ማበላሸቷ አይቀርም።” ተብሎ ተገልጧል። ሲጀመር ሕገወጥ መንገድን ተጠቅሞ ወደ ሕግ ለማቅረብ የተሞከረበት “የማስከበር” ሂደት ገና ሳይቋጭ፣ እንዲህ ዓይነት ፍረጃ መጠቀም ቢያንስ በጥላቻ ንግግር አዋጁ ሊያስጠይቅ በተገባ ነበር።

አንድ የኅብረተሰብ ክፍልን የተለየ የፖለቲካ አተያይ ስላለውና ከመንግሥት ጎን ስላልቆመ ብቻ እንደጠላት ተፈርጆ ሕገወጥ መባሉ ከቀደመው ስርዓት አሁንም መማር አለመቻሉን ያመላክታል።

በአይጥ የተመሰለውና በፍርድ ቤት ሳይሆን በመንግሥት ሕገወጥ የተባለው የኅብረተሰብ ክፍል መጠቀሚያ ያደርጋቸዋል የተባሉት የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ ሚዲያዎች በቀለም ተመስለው ሽፋን ተደርገው መሳላቸው ምን ያህል ዘመናችን ወደ ቀደመው የኢ-አማንያን ርዕዮተ ዓለም ስርዓት መመለሱን አመላካች መሆኑን አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

“የቀን ጅብ” የሚለው አገላለጽ አሁንም ድረስ ተገቢ አለመሆኑና ያደረሰው ተፅእኖ እየታየ ባለበት በዚህ ዘመን፣ “አይጥ” ብሎ አንድን ወገን መፈረጅም ሆነ አጥፊ ብሎ ጥላቻ እንዲፈጠር መቀስቀስ ከመንግሥት የማይጠበቅ ተግባር ነው። አይጥ መሆኗ ፍጥረቷ ወይም ማንነቷ እንደሆነ እየታወቀ መሰደቢያ ለማድረግና ጥፋት የባህሪዋ እንደሆነ አድርጎ መሳሉ፣ እርዳታዋን የፈለገውን ድር የተበጠሰለትን አንበሳ ጀግና እንደማያደርገው ሊታወቅ ይገባል።

ንብረት ማበላሸቷ እንደማይቀር የተነገረላት “አይጥ” ተብላ በሴት ፆታ የተገለፀችው ፍጡር የተመሳሰለችው በሕገወጥነት ከተፈረጀው የኅብረተሰብ ክፍል ነው። እንደቤተሙከራ አይጥ ወረርሺኝ በሽታ ሲመጣ ብቻ ለመሞከሪያና መፈተሻ መደረጓንም ለጦርነት ጊዜ ከተጠሩት ጋር መመሳሰሉን አገላለጹ የሚያመላክት ነው። በአጠቃላይ ክፉ ጊዜም ሆነ ጠላት መልሶ የማይመጣ ይመስል፣ እንደማይዋደድ ባልንጀራ እንኳን በየወንዙ መማማል የማያስችል ተግባር ላይ ከመሳተፍ መንግሥት ሊቆጠብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

“በረሮ” እየተባለ በሬዲዮ ጭምር ሲቀሰቀስበት የነበረ የሩዋንዳ የኅብረተሰብ ክፍል ምን እንደደረሰበት ዓለም ሁሉ ያውቀዋል። የመንግሥት ባለሥልጣናቱ በሕይወት በኖሩበት ዘመን የተፈጠረውን ይህን የዓለማችን አሳዛኝ የእልቂት ታሪክ መማሪያ ከማድረግ ይልቅ፣ ማጣቀሻ ማድረግ ማስጠየቁ እንደማይቀር መንግሥት ሊገነዘበው ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here