ኦሮሚያ መስተዳድር ሻሸመኔ ከተማ የኮሌራ ወረርሸኝ መስፋፋቱ ተነገረ። በኦሮሚያ አስተዳድር ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የነበሩ አንድ ሰው ትናንት በበሽታው መሞታቸው ተዘግቧል። የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ወረርሽኙን ለመግታት እየጣረ መሆኑን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምዕራብ አርሲ ዞን የሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ወረዳዎች የወረርሽኝ ሥጋት አይሎ መስተዋሉን የሚናገሩት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ደረጀ ምንም እንኳ በጥቂት ወረዳዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ቢቻልም በተቀሩት ወረዳዎች ያለው ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው ብለዋል።
ዶክትር ደረጀ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት “ወረርሽኙ ከአራት ወራት በፊት በሌሎች ክልሎች ተከስቶ ነበር። መጀመሪያ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ነበር የታየው ።ከዚያም ወደ ክልላችን ተዛምቶ መጀመሪያ ቦረና ነበር የታየው ፤ ከዚያ ወደ ምእራብና ምስራቅ ሃረርጌ ተዛመተ ፤ እንዲህ እያለ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መዛመት ቻለ ።
በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ወራት ከ652 ሰዎች የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሲሆን «ከእነዚህ ውስጥም ዐሥር ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። አብዛኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው እቤታቸው ነው። ወደ ህክምና ተቋም ባለመምጣታቸው ነው። የተወሰኑት ደግሞ ለምሳሌ ትናንት በሻሸመኔ አንድ አዛውንት በበሽታው አርፈዋል ፤ እስከ ሦስት ቀን ውስጥ ወደ ህክምና ባለመምጣታቸው ነው።» ብለዋል፡፡
በሽታው በኢትዮጵያ እስካሁን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከ680 በላይ የህመሙ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ሲገኙ፤ ቁጥራቸው ከ20 የሚሻገሩትን ደግሞ ለሞት ዳርጓል።
ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012


