“ለንግድ ባንክ 400 ሚሊዮን ብር ገቢ ብናደርግም ምላሽ አላገኘንም”

0
858

የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የትራክተርና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን ግዥ ለማከናወን ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 400 ሚሊዮን ብር ገቢ በማድረግ ለጨረታ አሸናፊዎች የሚከፈል የውጭ ምንዛሬ ቢጠይቅም ማግኘት አለመቻሉን አስታወቀ።

በአማራ ክልል የግንባታ እና ሌሎች መሣሪያዎችን ለመግዛት ከ22 ወራት በላይ የውጭ ምንዛሬ በመጠበቅ ተፈላጊ ማሽነሪዎች ተገዝተው ባለመቅረባቸው በክልሉ ልማት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ሲል የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ገልጾል።

ኤጄንሲው በውጭ ምንዛሪ ማጣት ምክንያት አገልግሎት የሚሰጣቸውን ተቋማት ማርካት ባለመቻሉና ተቋማቱ ግዥ ሳይፈጸም በጀት ዓመቱ ሲያልቅባቸው ሐሳባቸውን እየቀየሩ ጭምር መቸገሩንም አመልክቷል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ዘላለም ልየው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በክልሉ 11 ከተሞች በሚገኙ የግንባታ ተቋማት፣ ለአማራ ክልል የመሠረት ልማት ማስፋፊያ የሚውሉ ዶዘር፣ ሮለር፣ ሎቤድ፣ ኤክስካባተር እና ሌሎች የግንባታ ማሽነሪዎችን፣ እንዲሁም ለአማራ ክልል የቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች ማሠልጠኛ የሚውሉ መሣሪያዎችን ለመግዛት ዓለም ዐቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው ከተለየ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የግዥ ተቋሙ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 400 ሚሊዮን ብር ገቢ በማድረግ ለጨረታ አሸናፊዎች የሚከፈል የውጭ ምንዛሬ ቢጠይቅም ማግኘት አልተቻለም። የግንባታ ማሽነሪዎች እና ማሠልጠኛ መሣሪያዎችን ለመግዛት አንድ ሚሊዮን 771 ሺሕ 500 ዩሮ እና 9 ሚሊዮን 49 ሺሕ የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር አስፈልጎት ጥያቄውን ከ22 ወራት በፊት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢያቀርብም የውጭ ምንዛሬው ስላልተፈቀደለት መቸገሩን አስታውቋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፣ ለመንገድ ግንባታ አገልግሎት የሚውል 16 ማሽነሪዎች በ69 ሚሊዮን ብር ተገዝተው እንዲቀርቡለት የክልሉን ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ቢጠይቅም መሣሪያዎች ተገዝተው ስላልቀረቡለት መቸገሩን ተናገሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here