ኢትዮጵያ የማዕድን ቋት እያደራጀች መሆኑ ተገለፀ

1
1744

ከውጭ ከሚገቡ የድንጋይ ከሰል ምርቶች በላቀ ደረጃ የሚገኝ የድንጋይ ከሰል በአገራችን እንደሚገኝም ተረጋግጧል

ዕረቡ ግንቦት 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ የማዕድ ሀብቷን በአንድ ቋት መዝግቦ ለማስቀመጥና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል የምትገለገልበት የማዕድን ዳታቤዝ ፕሮጀክት ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

አፍሪካ ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማዕድን ዘርፍ የተሳካ ሥራ የሠሩትን አገራት ፈለግ በመከተል የዳታ ቤዝ ፕሮጀክት ተቀርፆ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደተገባ እና ለገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን፤ የዓለም ባንክም በሃሳብ ደረጃ መቀበሉን የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገልፀዋል፡፡

የማዕድን ዳታቤዝ ፕሮጀክቱ 200 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈጅና እንደ ኢትዮጵያ ምድር በማዕድን ሀብት የበለፀገ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ መሸከም በሚችሉ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ባላቸው ማዕድናት የተሞላ ምድር ላላቸው አገራት አስፈላጊ እንደሆነ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የማዕድን ፍለጋ በዓመታት የሚቆጠር ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ሥራውን ለመምራት አስቸጋሪ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የማዕድን ዳታቤዝ ሲኖር እንደአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን በማጥናት እያንዳንዱ ሃብት በምን ዓይነትና መጠን እንዳለ መረጃ ስለሚኖር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንቨስትመንት ሲመጣ በማዕድን ፍለጋ የሚባክን ጊዜ ሳይኖር በቀጥታ ወደ ምርት ስለሚገባ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የማዕድን ዳታቤዝ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ውድ ማዕድናትን ያሉበትን ቦታ እና መጠን ለማወቅና ለመጠቀም ያስችላል፡፡ ከዚህ ፀጋ መጠቀም እንዲያስችላቸውም ክልሎች የማዕድን ኮርፖሬሽን እንዲያደራጁ እየረዳናቸው ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የመጣችበት መንገድ ከፍተኛ የእሳቤ ችግርና ሳንካዎች የነበሩበት ነው ያሉት ኢንጅነር ታከለ፤ የማዕድን ዘርፉ የጠራ ዕይታ ያልነበረበት እና ማዕድንን እንደ ፀጋ ከመቁጠር ይልቅ እንደግጭት መንስዔ አድርጎ የሚመለከት ሆኖ ቆይቷል ብለው፤ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ እና ጥራት ያለው የማዕድ ሀብት እያለን እንደሌለን ሆነን ቆይተናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እንደ ኢንጅነር ታከለ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ሚዛኑን ያልጠበቀ ትርክት የነበረ፡፡ ይህ የአገሪቱን የማዕድን ሀብት ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ከመገደቡም በላይ ያሏትን ፀጋዎች እንዳትመረምር ጋርዷት ቆይቷል፡፡

ለዚህ እንደማስረጃ የኢትዮጵያን የከሰል ማዕድን ምርት በውጭ አገራት ኩባንያዎች ተመርምሮ የተገኘው ዕውነተኛ ያልሆነ ውጤት አሁን ወደተለያዩ አገራት ተልኮ ትክክለኛ የከሰል ይዘቱ እንደታወቀ ኢንጅነሩ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል ጥራት እንደሚጎድለውና የእርጥበት መጠን ከፍተኛ መሆን እና አሽ መጠኑ ትልቅ መሆኑ ሲነገር እንደነበር የገለፁት ኢንጅነር ታከለ፤ ማዕድኑ ወደቱርክ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቻይና ናሙናዎችን በመላክ በተደረገው ማጣራት ከውጭ ከምናስገባቸው የድንጋይ ከሰል ምርቶች በላቀ ደረጃ የሚገኝ የድንጋይ ከሰል በአገራችን እንደሚገኝ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ የድንጋይ ከሰል ምርቶች 5 ሺህ የማቃጠል አቅም ያላቸው ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል የማቃጠል አቅም 6 ሺህ እና ከዚያ በላይ መሆኑ በመረጋገጡ ለሲሚንቶ ምርት እንደግብዓት ለመጠቀም ከፍተኛ መነቃቃት መታየቱንና ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከውጭ የሚገቡ የድንጋይ ከሰል ምርቶችን ለማስቀረት ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በድንጋይ ከሰል መስክ የታየውን የራስን ፀጋ የመጠቀምና የማወቅ ተግባር በማስቀጠል ሌሎች ሥራዎችም እንደሚሠሩ ሚኒስትሩ ተናግረው፤ ማዕድናችንን እንዳናይ ፀጋችንን እንዳንጠቀም የተነዛው ዓለም አቀፍ ትርክትን ማሸነፍ የምንችለው በመሥራት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

አስተያየት

  1. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ከ10 በላይ ማዕደን እነደሚገኝ አውቃሎ።ስለዚህ በስልክ ቁጥር 0918688531 ወይም 0938466027 ዳውሉ ሙሉ መረጃ ይሰጣቸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here