ዕረቡ ግንቦት 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ለማሰባሰብና ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኦንላይን እንዲከፍሉ ከኦሮሚያ፣ ወጋገንና ዘመን ባንክ ጋር ሥምምነት ተፈራርሟል።
በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከአራት ባንኮች ጋር እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
ታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን አለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመደገፍ የአገልግሎት አሰጣጡ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በሆነ መንገድ መስጠት ዋናው የተቋሙ ተልእኮ መሆኑን የገለፁት፤ የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ መሰረት መስቀሌ የግብር ሥርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን ሌሎች ባንኮችም ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግብር ከፋዮች ማንኛውንም አገልግሎት ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲጠቀሙ ደራሽ የተሰኘ መተግበሪያ አልምቶ ወደ ሥራ መግባቱን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በሥምምነቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡
ሥምምነቱን የፈረሙት ባንኮችም በበኩላቸው አገልግሎቶችን በኦንላይን በመፈጸም የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሙሉ ዝግጁነትና ኃላፊነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።




