ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ክስ ከመቅረቡ በፊት ለእርስ በእርስ የቁጥጥር ሥርዓት ሊቀርቡ ይገባል ተባለ

0
803

ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ክስ ከመቅረቡ በፊት ለእርስ በእርስ የቁጥጥር ሥርዓት ሊቀርቡ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት አሳሰበ።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ላይ የሚሠሩ 18 ያህል ጋዜጠኞችን ሕግ ከማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር በማድረጉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

መንግሥት በቁጥጥር ስር ያዋላቸን ጋዜጠኞች አንዳንዶቹን ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ አሁንም ፍርድ ቤት ያልቀረቡና የታሰሩበት ቦታ የማይታወቁ ጋዜጠኞች መኖራቸው ምክር ቤቱን እንዳሳሰበውም በመግለጫው ገልጿል።
‹‹በቅርቡ የፀደቀውና ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመገናኛ ብዙኀን አዋጁም ሆነ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፣ ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት መደበኛ ክስ በፊት እንዳይታሰሩ ይከለክላል›› ያለው ምክር ቤቱ፤ ጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ የፈጸሙት የሕግ ጥሰትም ሆነ የሥነ ምግባር ግድፈት ካለ በመገናኛ ብዙኀን ፖሊሲውም ሆነ በአዋጁ እውቅና ለተሰጠው የእርስ በእርስ ቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጊያ አማራጭ ዘዴ ሊቀርቡና ሊዳኙ ይገባል ብሏል።

ነገር ግን ጋዜጠኞችን አስሮ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ በሕገ መንግሥቱ እውቅና ያገኘውን ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይጋፋል ብሎ እንደሚያምንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞች በሕግ ከተደነገገው በተቃራኒ መያዛቸው፤ በቅድመ-ፍርድ ጊዜ ለረጅም ቀናት ያለ ክስ ታስረው መቆየታቸው፣ የታሳሪዎችን አድራሻ መደበቅ እና በቤተሰብና የሕግ ባለሙያ እንዳይጎበኙ መከልከል እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች ማሰር የመገናኛ ብዙኀን አዋጁን የሚፃረር ተግባር በመሆኑም ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከመገናኛ ብዙኀን ሥራቸው ጋር በተያያዘ ከሆነ ክሱም ሊቀርብባቸው የሚገባው በመገናኛ ብዙኀን አዋጁ መሠረት በመሆኑ ጋዜጠኞቹ ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲልም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here