ደንበኞች ግብራቸውን ኦንላይን እንዲከፍሉ ከባንኮች ጋር ስምምነት ላይ ተደረሰ

0
1003

የገቢዎች ሚኒስቴር ደንበኞች ግብራቸውን በኦንላይን እንዲከፍሉ ለማስቻል ከኦሮሚያ፤ ወጋገን እና ዘመን ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል ተብሏል።
ስምምነቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የታክስ አሰባሰቡን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እና ደንበኛውም በኦንላይን በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆኖ ግብሩን መክፈል ያስችለዋል ነው የተባለው።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ለማሰባሰብ በሚያደርገው ጥረት ንግድ ባንክን ጨምሮ ከአራት ባንኮች ጋር እየሠራ መሆኑንም ተመላክቷል።
በሚኒስቴሩ የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ መሠረት መስቀሌ፤ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመደገፍ የአገልግሎት አሰጣጡ ግልጽ፤ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በሆነ መንገድ መስጠት ዋናው የተቋሙ ተልእኮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የግብር ሥርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን ሌሎች ባንኮችም ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረባቸው ተዘግቧል።
ግብር ከፋዮች ማንኛውንም አገልግሎት ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲጠቀሙ ‹‹ደራሽ›› የተሰኘ መተግበሪያ አልምቶ ወደ ሥራ መግባቱን በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በስምምነቱ ወቅት መገልጻቸው ተጠቅሷል።
ስምምነቱን የፈፀሙት የባንኮቹ ተወካዮች በበኩላቸው አገልግሎቶችን በኦንላይን በመፈጸም የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሙሉ ዝግጁነት እና ኃላፊነት እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here