የ5G ቴክኖሎጂ የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የዲጂታል ዓለሙ የሚፈልገውን ፈጣን ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ እርምጃ ያራመደ ቴክኖሎጂ መሆኑ ይወሳል። የ5G ቴክኖሎጂ የመረጃ መለዋወጫ ፍጥነትን አሁን ካለው የ4G ቴክኖሎጂ አንጻር ከ10 እስከ 100 እጥፍ እንደሚበልጥ የተለያዩ ባለሞያዎች ይገልጻሉ።
ይህም ማለት የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን እስከ ዛሬ ከነበረው የሜጋባይት የሰኮንድ ፍጥነት ወደ ጊጋባይት በሰኮንድ ያሳድገዋል እንደማለት ነው።
በኒውዮርክ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መምህር ሪሽ ክሪሺናስዋሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የ5G ቴክኖሎጂ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል።
በምክንያትነት ሲያስቀምጡ፣ አሁን ባለው የኔትዎርክ ፍጥነት መተግበር ያልቻልናቸውን ከፍተኛ የሆነ የኔትዎርክ አቅምን የሚጠይቁ መተግበሪያዎችን እንድንጠቀም ያስችለናል ብለዋል።
መምህሩ በምሳሌነት እንዳስረዱት፣ በጊጋባይት ደረጃ ያሉ ፊልሞችን በሰከንድ ከኢንተርኔት ለማውረድ እንደሚያስችል እና እንደ ቨርችዋል ሪያሊቲ መተግበሪያ እና ሰው አልባ መኪኖች ላይ ለፈጣን የመረጃ ዝውውር መጠቀም ያስችላል በማለት አብራርተዋል።
በተጨማሪም፣ ዘመኑ እየፈጠራቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎች ማለትም እንደ አጉመንትድ ሪያሊቲ እና ሰው አልባ መኪኖች ያሉ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ፍጥነትን የሚሹ መሆናቸውን ያነሳሉ።
የ5G ቴክኖሎጂ የመረጃ የመዘግየት ሂደት ወደ 1 ሚሊ ሰኮንድ ዝቅ ማድረግን ዓላማ አድርጎ ተነስቷል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎች መረጃን በአንድ ሰኮንድ አንድ አንድ ሺኛ (1/1000) ባነሰ መለዋወጥ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ትውልዶች ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙት የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ጨረርን እንደ ሬድዮ ሞገድ ባሉ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በመሆኑ፣ የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ በከፍተኛ ሁኔታ የኔትዎርክ መጨናነቅ ይፈጠርበታል፡፡
ስለሆነም፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ የሆነ የራድዮ ሞገድ ከመጠየቁም በላይ በሴንቲሜትር የሚለካውን ወደ ሚሊሜትር ሞገድ ዝቅ ማድረግ አስፈልጓል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ቀድመን ከምናውቀው ትልልቅ የሆኑ የኔትዎርክ ምሰሶዎች በማይፈልጉ የሕንጻዎች አናት እና በመብራት አስተላላፊ ምሰሶዎች ላይ ሊገጠሙ የሚችሉ በመሆኑ ቴክኖሎጂዎቹ አዲስ የግንኙነት መንገድ ይከፍታሉ ተብሎላቸዋል።
ነገር ግን እነዚህ የሞገድ ዓይነቶች ሌሎች ተግዳሮቶች አጋጥሟቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ሞገዶቹ በዛፎችና በሕንጻዎች ከመዋጥ አልዳኑም ይላሉ። እነዚህ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ የኔትዎርክ አስተላላፊዎች፣ ለአዳዲስ የምርምር ሥራዎች መፈጠር ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
የአምስተኛው ትውልድ ኔትዎርክ (5G) ቀድሞ በነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ላይ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በመጠን አነስተኛ የሆኑ አንቴናዎችን በመጨመር፣ እንዲሁም የማስተላለፍ አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ መላላኪያ ፍጥነትን በመጨመር የተፈጠረ ነው። እንዲሁም የመረጃ መዘግየትን በእጅጉ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከዚህ በተጨማሪም በፊት ከነበሩት የኔትዎርክ አስተላላፊዎች ያነሰ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀማቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል።
በዓለም 70 አገራት የ5G ቴክኖሎጂውን ሲጠቀሙ፣ ከእነዚህ መካከል አምስት የአፍሪካ አገራትም ተደራሽ ሆነዋል። በኢትዮጵያም ግንቦት 1/2014 ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛ ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት መጀመሩን አስታውቋል።
ዓለም የደረሰችበት የመጨረሻው ፈጣኑ ኔትወርክ የቻይናው ህዋዌ የፈጠረው አምስተኛ ትውልድ (5G) የተሰኘው የኔትወርክ አገልግሎት ሲሆን፣ የ5G ቴክኖሎጂ የግለሰቦችን እለታዊ እንቅስቃሴ የማሻሻል፣ የኢንዱስትሪዎችን የሥራ ክንውን ለማቀላጠፍ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ተጠቁሟል።
5ኛው ትውልድ ኢንተርኔት ከ4ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ ሲነፃፀር ከ100 እጥፍ ጊዜ በላይ ፍጥነት ሲኖረው፣ በሰከንድ እስከ 100 ጊጋ ባይት መረጃ መለዋወጥ እንደሚያስችልም መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የ4G ሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት በመላው አገሪቱ በማስፋፋት ከ136 በላይ ከተሞችን ተጠቃሚ አድርጓል።
ኩባንያው የዘረጋቸው የ4G ሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፊያ መሠረተ ልማቶች፣ ለ5G ሞባይል ኔትዎርክ ዝግጁ ተደርገው የተሠሩ መሆናቸውም አይዘነጋም።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለፁት፣ ኩባንያው ላለፉት ወራት ያደረገውን ሙከራ አጠናቆ የ5ኛ ትውልድ ሞባይል ኔትዎርክ ጀምሯል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አክለውም፣ አገልግሎቱን በመዲናዋ ውስን ቦታዎች ማግኘት እንደሚቻል ያስረዱ ሲሆን፣ በዩኒቲ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ቸርችል ጎዳና እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም መሥሪያ ቤት አካባቢዎች የ5ጂ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረጉን ማስረዳታቸው ይታወቃል።
ኔትዎርኩ በቻይናው ሑዋዌ ኩባንያ አማካይነት መዘርጋቱን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ እጅግ ፈጣን የሚባለውን የ5ኛ ትውልድ የኔትወርክ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ደንበኞች ከአገልግሎቱ ጋር የተስማማ የእጅ ስልክ እና የ5ጂ ኔትወርክን የሚያቀርብ መሠረተ-ልማት ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
ከ65 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም፣ 25 ሚሊዮን ደንበኞቹ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ሰላማዊት ዲባባ (ሥማቸው የተቀየረ) የዩኒቨርሲቲ መምህርት ሲሆኑ፣ 5G ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ መጀመሩ ጉልህ ሚና እንዳለው እና የሞባይል ኔትወርኮች ዛሬ በጣም የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ምርጡን አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።
5G ተጠቃሚዎች ብዙ ጥቅሞችን እንዲያገኙ የሚያስችል አምስተኛው ትውልድ ሴሉላር አውታር ቴክኖሎጂ ነው።
የስማርትፎን ተጠቃሚዎች መረጃውን ማግኘት ሲፈልጉ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉ የ4ጂ ኔትወርኮችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ቀስ በቀስ በመተካት ላይ ይገኛል። አውታረ መረቡ መተግበሪያዎችን በፍጥነት ለማሰማራት ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ገንቢዎችንም ይጠቀማል።
5G በሞባይል ስልኮች እና ሌሎች መሣሪያዎች ላይ ከ4ጂ እና 4G ኤል.ቲ.ኢ. ጋር ሲወዳደር በፍጥነት ይሠራል። ተጠቃሚዎች ፊልሞችን፣ ቪዲዮዎችን እና ሙዚቃዎችን በጥቂት ደቂቃዎች እንዲያወርዱ ያስችላል ሲሉም አብራርተዋል።
በዓለም አገራት ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙ ድርጅቶች የላቀ የኦንላይን ስብሰባዎችን ጨምሮ የመሳሰሉትን አገልግሎቶች እንዲጠቀሙበት እንዳደረጋቸው እና በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 5G የተጠቀሙ ሸማቾች መረጃዎችን በማውረድ ሂደት በቀን 23 ሰዓታት ይቆጥባሉ ተብሏል።
መምህርቷ አክለውም፣ 5G ከ 4G ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ መዘግየት አለው። እንደ AI፣ IoT እና ምናባዊ እውነታ ያሉ አዳዲስ መተግበሪያዎችን በብቃት ይደግፋሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ድረ-ገጽ ከፍተው ያለምንም ውጣ ውረድ ነገሮችን እንዲቃኙ ያስችላቸዋል። ሌላው ነገር አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎችን በሚፈልጉበት በማንኛውም ጊዜ ወደ በይነመረብ ለመግባት መንገዶችን ይሰጣል ባይ ናቸው።
5G ከ4G በላይ እስከ 100 እጥፍ የበለጠ አቅም አለው። ኩባንያዎች በሴሉላር እና በዋይ ፋይ ሽቦ አልባ ስልቶች መካከል መረጃዎችን እንዲቀያየሩ ያስችላቸዋል። ይህም የተሻለ አፈጻጸምን ለማግኘት ብዙ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ በይነመረብን በከፍተኛ ብቃት ለመጠቀም ዘዴዎችን እንደሚያቀርብም ተናግረዋል።
ከ5G ዋና ጥቅሞች አንዱ መረጃውን በተቻለ ፍጥነት ለማስተላለፍ የሚረዳውን ተጨማሪ የመተላለፊያ ይዘት መጨመር ነው። በተጨማሪም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች የ5ጂ ኔትወርክን ከመረጡ በኋላ፣ በበለጠ የመተላለፊያ ይዘት ያለው ፈጣን ግንኙነትን ማረጋገጥ ይችላሉ።
5G ቴክኖሎጂ ድሮኖችን እና ዳሳሾችን ጨምሮ ከተለያዩ መሣሪያዎች ጋር ለመገናኘት ፍጹም ተመራጭ ነው። ኢንዱስትሪዎች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የአይኦቲ መቀበልን ለማበረታታት መንገዶችን እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
የ5G ዋነኛ ጉዳቱ ውስን የሆነ ዓለም ዐቀፍ ሽፋን ያለው እና በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ የሚገኝ መሆኑ ነው። ከተሞች ብቻ ከ5G ኔትወርክ ብዙ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን፣ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ለተወሰኑ ዓመታት ሽፋኑን ላያገኙ ይችላሉ።
በሌላ በኩል፣ የሰቀላ ፍጥነቱ ከ4G ጋር ሲወዳደር ከ100 ሜጋ ባይት በላይ አይደለም። በተጨማሪም የሞባይል ስልኮች የ5ጂ ግንኙነት ሲጠቀሙ የተሻለ የባትሪ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋቸዋል።
ብዙ የስልክ ተጠቃሚዎች 5ጂ ሲሠሩ፣ በመሣሪያዎቻቸው ላይ ተጨማሪ ሙቀት እንደሚያጋጥማቸው ይናገራሉ።
የሳይበር ደኅንነትን አስመልክቶ ሳይበር ሴኪዩሪቲ የ5G ጉድለት አንዱ ነው፤ ምክንያቱም ጠለፋን ወይም ‹ሀክ› መደረግን ስለሚያስከትል ነው። የመተላለፊያ ይዘት መስፋፋት ወንጀለኞች የመረጃ ቋቱን በቀላሉ እንዲሰብሩነ እንዲገቡ/እንዲጠልፉ ያስችላቸዋል።
ከዚህም በላይ ወደ ተጋላጭ ጥቃቶች የሚያመራውን ሶፍትዌር ይጠቀማል፡፡ 5G ከብዙ መሣሪያዎች ጋር ሲገናኝ የጥቃት እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው።
ስለሆነም፣ ኩባንያዎች እና ቢዝነሶች መሠረተ ልማቶቻቸውን በፀጥታ ማስፈጸሚያ ማዕከል በማስጠበቅ ተጨማሪ ወጪዎችን ያስከትላል። 5G ምስጢር ስለሌለው ጠላፊዎች ጥቃታቸውን በበለጠ ትክክለኛነት ማቀድ ይችላሉ፡፡ ይህም ኩባንያዎቹን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል።
በተጨማሪ የመተላለፊያ ይዘት የአሁኑን የደኅንነት ክትትል ስለሚያበላሽ፣ አውታረ መረቡ የሳይበር ስጋቶችን ለመከላከል የደኅንነት እርምጃዎችን ይፈልጋል።
ደኅንነትን በብቃት ለማሻሻል የሸማቾች ትምህርት አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ከ5ጂ የመጀመሪያ ልቀት ጋር በመሆን ደኅንነትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው። ሁሉንም የአይኦቲ መሣሪያዎች ከደኅንነት መጠገኛዎች ጋር ማዘመን ችግሮቹን በጥሩ ውጤት ለማሸነፍ ይረዳል።
ይህም ብቻ አይደለም፤ የ5G ተጠቃሚዎች ያልተፈለጉ ችግሮችን ለመቀነስ አንዳንድ ሌሎች እርምጃዎችን መከተል አለባቸው ሲሉ መምህርቷ አሳስበዋል።
5G የሞባይል ቴክኖሎጂ አሁን ካለው የ4ጂ ኔትዎርኮች ጋር ሲነፃፀር በዐስር እጥፍ የመረጃ ስርጭት ፍጥነት እንደሚጨምር ቃል ተገብቷል።
የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ጨረሮች ፊዚዮሎጂያዊ ተፅእኖዎች በድግግሞሽ ይቀየራሉ፡፡ ስለዚህ የ5ጂ መምጣት አግባብነት ያለው የጨረር ደኅንነት መመሪያዎችን በተመለከተ ትልቅ ዓለም ዐቀፍ ግምገማ አስነስቷል፡፡ ለዚህም ትርጉም ያለው የጤና ስጋት ግምገማ በቂ መረጃ እንደሌለ ተስማምቷል ባይ ናቸው።
የኮምፕዩተር ሳይንስ ባለሞያው ዮሐንስ ደምሴ በበኩላቸው፣ 5G ማለት 2G፣ 3G፣ 4G እንደሚባሉት ተሻሽሎ የመጣ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለማኅበረሰቡ ጉልህ ጠቀሜታ ያለው ነው በማለት ጠቅሰዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በመሆን ኢንተርኔት ጋር የተያያዙ ሥራዎቻቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ እና ኅብረተሰቡም በስማርት ወይም በዘመናዊ ስልኮችን አማካኝነት ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ፈጣን የድምፅ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙበትን እድል ያጎለብታል ይላሉ።
ከዚህ ባሻገር ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የሕክምና ደረጃውን ከፍ ማድረግ ይቻላል የሚሉት ዮሐንስ፣ ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂውን በኦንላይን አማካኝነት በማገናኘት ዜጎች የኦን ላይን ሕክምና እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪ በትምህርት ተቋማት በኢንተርኔት አማካኝነት ቴክኖሎጂውን በመዘርጋት ፍጥነት የታከለበት የኦንላይን ትምህርት ለመስጠት እንደሚረዳ እና ኢትዮጵያንም በቴክኖሎጂው ረገድ ከፍተኛ ውጤት እንድታስመዘግብ ያግዛታል ይላሉ።
የኮምፕዩተር ሳይንስ ባለሙያው ሳሙኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ የ5ጂ ወይም የአምስተኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ እንደተጀመረ እና በአዲስ አበባ ከተማ በውስን ቦታዎች አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ ለአብነትም በጤናው ዘርፍ ላይ ሰፊ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ደረጃ ቴክኖሎጂው ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ ውጤቱም በቀጣይ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኩል የሚገለፅ ይሆናል የሚሉት ባለሙያው ናቸው።
በአጠቃላይ የ5ጂ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂው ከማሳደግ ባለፈ ከሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ከጤና አንፃር ብሎም ከግብርና አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ባለሞያው አክለውም ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆኗን ተከትሎ ለተለያዩ ለማዕድን ናሙና ማውጫዎች በሮቦት ሴንሰር አማካይነት አገልግሎት ላይ ሊውል ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል የት አካባቢ እንዳለ እንዲሁም የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች ለመለየት እንደሚረዳ አመላክተዋል። ማኑፋክቸሪንግ እና የመሳሰሉ ዘርፎችንም ለማሳደግ ቴክኖሎጂው እንደሚረዳ ነው ባለሞያው የጠቆሙት።
ባለሞያው አክለውም፣ የ4ጂ እና ሌሎች ኔትወርኮች በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በሚገባ ሳይሠሩ አምስተኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ እንዴት ተጀመረ የሚሉ ጥያቄዎች አሉ ሲሉ ጠቅሰዋል። ቴክኖሎጂውን ተቀብሎ ሥራ በማስጀመር ሌሎች ቴክኖሎጂዎችንም ማሳደግ የሚቻልበት እድል ሰፊ መሆኑንም ነው አያይዘው ያነሱት።
የኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያው ናትናኤል፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከ2ጂ ወይም ከኹለተኛው ትውልድ ጀምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው ይፋ እያደረገ የመጣ ሲሆን፣ አሁንም የአምስተኛ ትውልድ የቴክኖሎጂ ይፋ ማድረጉን አስታውሰዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ጊዜያት ይፋ ባደረጋቸው በእያንዳንዱ ትውልድ መካከል በቴክኖሎጂው መዘመንና ከፍጥነት ጋር በተያያዘ ሰፊ ልዩነት አለው ባይ ናቸው።
ለአብነት በ4ጂ እና በ5ጂ መካከል በድምፅ አገልግሎትም ሆነ በኢንተርኔት አገልግሎት አንፃር ከፍተኛ የሆነ የአገልግሎት ፍጥነትም ሆነ ዘመናዊነት የታከለበት ቴክኖሎጂ መኖሩን ባለሞያው አስረድተዋል።
ይህ ቴክኖሎጂ መጀመሩ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ረገድ ለውጥን ከማስመዝገቧ ባሻገር ባንኮች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የአሠራር ሂደታቸውን ከማዘመን ባለፈ ደንበኞቻቸውን ሳያጉላሉ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳቸው ገልፀዋል።
ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋም እንዲሁም ዜጎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ረገድ ውጤታማ ትሆንበታለች የሚል ጽኑ እምነትም አላቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



