መነሻ ገጽዜናወቅታዊየረዥም ልብወለድ ህትመት መዳከም

የረዥም ልብወለድ ህትመት መዳከም

ኢትዮጵያ ቀደምት የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ካላቸው አገራት ግንባር ቀደም የምትመደብ ትሁን እንጂ፣ በዘመናዊው የአጻጻፍ ስልት ጅማሮ ግን ከዓለም ዘግይታ የጀመረች ስለመሆኗ መረጃዎች ይገልፃሉ።

በተለይ ጥንት በኦሪት ዘመን ሳይቀር የእስራኤላውያንን መጽሐፍት አንባቢ ከመሆኗም ጋር ተያይዞ፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ በሆነው ሰለሞናዊ ሥርዎ-መንግሥት እና በሐይማኖት ተቋማት አማካይነት የራሱን ፈጠራና መልክ የያዘ አያሌ የጽሑፍ ሥራዎች ባለቤት ስለመሆኗ ይነገራል።

ይሁን እንጂ፣ በአገሪቱ ኪነ ጥበብ ታሪክ አኳያ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ ሲነሳ፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አስቀድሞ የተውኔት ድርሰትም ይሁን የልቦለድ ሥራዎች ስለመኖራቸው የተጻፈ መረጃ እንደሌለ ነው በዚህ ዘርፍ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የሚገልጹት።

የቴአትር ትዕይንት ቀደም ብሎ እንደተጀመረ የሚያወሱ ድርሳናት ቢኖሩም፣ ድራማዎቹ ይከወኑ የነበሩት ግን በድርሰት መልክ ተዘጋጅተው ሳይሆን በቴአትሩ ደራሲ በቃል እየተመራና ተዋንያኑና ተዋንያቱ የራሳቸውን ጥበብ ጨምረው ነበር ለመድረክ የሚቀርበው ይባላል።
ይህም ዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የተጀመረው ከዚህ በኋላ ስለመሆኑም ጭምር እንደማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጦቢያ የተሰኘችው ወጥ ልቦለድ በአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ መታተም፣ በብዙዎች ዘንድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የአማርኛ ዘመናዊ ሥነጽሑፍ መሥራች ተደርጋ ትወሰዳለች።
ከዚህ በኋላ የነገሥታትን ዜና መዋዕል እንዲሁም ገድላትን ከመጻፍ በተጓዳኝ በዘመናዊው የሥነጽሑፍ ሥራም ማደግ ተችሏል።

ይህን ተከትሎ በተለይ ከ1950ዎቹ ማብቂያ እስከ ሚሊኒየሙ መግቢያ ድረስ፣ ዘመናዊ የአጻጻፍ ስልትን ተከትለው የሚጻፉ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍት የተሻለ የሚገኙበት ወቅት ነበር ይባላል።
በኹሉም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ያ ዘመን የተሻለ ነበር በሚለው የሚስማሙ አካላት በተለይ በዚህ ወቅት የሙዚቃና የፊልምም ሆነ የረዥም ልብ ወለድ ሥራችን እንደ አገር አስጊ ደረጃ ላይ ነው ይላሉ።
አሁን ባለንበት ወቅት ኹኔታዎችን እየተከተሉ፣ በወራት እድሜ መጽሐፍትን ማሳተም የፈጠራ አቅማችን እየወረደ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በላቀ የምናብ ውጤት እንዲሁም በጠንካራ ሐሳብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እየመረመሩ፣ ውበትና ለዛ በተሞላበት አገላለጽ በዚህ ዘርፍ ለትውልድ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ገበሬዎች ስለመኖራቸው ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
ጌታቸው ባዬ በመዲናዋ መጽሐፍ በማዞር የሚሸጡ ጎልማሳ ናቸው። ከያዛቸው በርካታ መጽሐፍት መካከል አብዛኞቹ በቅርብ ጊዜ የታተሙ ሆነው፣ ከፈጠራ ሥራ የማይመደቡ ናቸው። በብዛት የያዘውም የተለያዩ ፖለቲካ ቀመስ መጽሐፍት፣ በአጫጭር ታሪኮች የተዘጋጁ መጽሐፍት፣ የትርጉም መጽሐፍትና ሌሎች ጥቂት የቀድሞ ጉምቱ ደራስያን ረዥም ልቦለድ ሥራዎች ናቸው።

ጌታቸው በቤታቸው ውስጥ ስምንት መደርደሪያ የሚሆን መጽሐፍ እንዳላቸው ገልጸውም፣ አሁን ላይ በብዛት እየታተሙ ስላሉ መጽሐፍት ሲያወሩ፣ ‹‹በበኩሌ ከመጽሐፍት ጋር በጣም ቅርበት አለኝ። በዚህ ወቅት እንደቀድሞዎቹ ደራስያንና ፀሐፌ ተውኔት እንደነ በዓሉ ግርማ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ከበደ ሚካኤል፣ መንግሥቱ ለማ፣ ማሞ ውድነት፣ አቤ ጉበኛ የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የሚሠሯቸውን ዓይነት የድርሰት ሥራዎችን አሁን ላይ ማግኘት በጣም ከባድ ነው›› ይላሉ።

ለዚህም ይመስለኛል የሚሉትን ምክንያት ሲያስቀምጡ፣ በዋናነት ደራሲዎች ከኑሮ ጫናው የተነሳ ቁጭ ብሎ ለማሰብና ለማሰላስል የሚሆን ጊዜ የላቸውም። እንደምንም ብለው አንድ ምርጥ የሚባል ወጥ ሥራ ቢያበረክቱ እንኳን፣ በደከሙበት ልክ ተጠቃሚ አይሆኑም። ስለዚህም ዘርፉን አይፈልጉትም ሲሉ ይናገራሉ።

ችግሩ የአንባቢ አለመኖር አይመስለኝም የሚለውን ዕይታቸውን አንስተውም፣ በዚህ ወቅት የኑሮ ውድነቱ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ሳይጠቅሱ አልቀሩም። ‹‹መጽሐፍት ግን እኔ እንደማየውና ለረዥም ጊዜ በዚህ ሥራ እንደመቆየቴ፣ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ እየተሸጡ ነው›› ብለዋል። አንባቢውም ጥሩ መጽሐፍትን ገበያ ላይ ካገኘ እንደሚገዛ ነው የገለጹት።

ሆኖም ግን ረዥም ልብ ወለድ የሚጽፉ ደራሲዎች እንዳይኖሩን ያደረገው፣ ትልቁና ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣው ክፉ ልማድ በመጽሐፉ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑት ነጋዴዎች መሆናቸው ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ረዥም ልቦለድ የማንበብ ፍቅር አለኝ የሚሉ አንድ አንባቢም እንዲሁ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲያጋሩ፣ አገራችን ከቀን ወደ ቀን በብዙ መልኩ ኪሳራ ውስጥ ስትገባ እናያታለን ካሉ በኋላ፣ ኹሉም ባለበት አብዛኛው ነገራችን ደግሞ እየባሰበት ነው። ለዚህ ኹሉ እንድንበቃ ያደረገን በኪነ ጥበብ ሥራ ማደግ አለመቻላችን ነው ባይ ናቸው።

ትውልዱ አሁን ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁነት የሚገልጽበትና እርስ በእርስ በቀላሉ የሚጋራበት በርካታ መንገድ ማግኘቱም ደራስያንን ችላ እንዲላቸው አድርጓል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያው ትኩረት አግኝቶ፣ የሚጽፍ የሰላ ደራሲ እንዳይፈጠርና አንባቢም እንዳይኖር በማድረግ አጠቃላይ ኑሯችን እንዳንፈትሽ አድርጎናል ነው የሚሉት።

ይህም የራሳችን ባህል፣ ታሪክ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጸባይ ያለን ሕዝብ እንደመሆናችን፣ የት ላይ እንዳለን ለማወቅ ወደ ራሳችን እንዳናይ በማድረግ፣ ራሳችንን እንዳንመስልና በቴክኖሎጂውም ወደኋላ እንድንቀር ምክንያት ሆኗል ሲሉ ይናገራሉ።
በርካታ ረዥምና አጫጭር ልብወለድ ደርሰቶችን እንዲሁም የግጥም መጽሐፍትን አሳትሞ ለንባብ ከማብቃት በተጨማሪ፣ በርከት ያሉ የተውኔት ድርሰቶችን ለመድረክና ለቴሌቭዥን ድራማ በማበርከት የሚታወቀው አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ) (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ፣ በዚህ ወቅት የረዥም ልቦለድ ድርሰቶች ቁጥር ቀንሷል የሚለውን ለመናገር መረጃ የሚጠይቅ በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻል ሲል ይገልጻል።

ግን ደግሞ ያን ያህል ጥልቅ ጥናት ሳያስፈልገን አሁን ላይ በገበያው ሲንሸራሸሩ የምናያቸው መጽሐፍት በአብዛኛው ፖለቲካ ነክ ድርሰቶች ናቸው ይላል ደራሲው። በተጨማሪም፣ ግለ-ታሪኮችና የቀድሞው መንግሥት ላይ መሠረት ያደረጉ ታሪክ ቀመስ ድርሰቶች እየወጡ ነው። ከዚህ አንጻር ወጥ የሆኑ ልቦለዶችም እየወጡ ነው ለማለት አያስደፍርም ነው ያለው።

የሕዝቡ ኑሮ ሩጫ የበዛበት መሆኑም ለመረጃ ቅድሚያ እንዲሰጥ አድርጎታል የሚለው ደራሲው፣ በዚህ የተነሳ ከዲጅታል ስርዓቱ ጋር ተዳምሮ ቁንጽል ነገር የሚፈለግበት ዘመን ላይ እንደመሆናችን ረዥም ልቦለድ ማውጣት አስቸጋሪ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብሏል።
ረዥም ልቦለድ ማሳተም ለሚፈልግ አንድ ደራሲ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንዳልሆነም ይናገራል። በተለይ የማሳተሚያ ዋጋ መናር ዋነኛው መሆኑን አንስቶ፣ የሰው ምርጫ ወደ ሌላ (ዲጅታል) ከዞረ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንደሚታየው ስለተንኮታኮተ፣ ደራሲዎች የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የገቡበት ወቅት ነው ይላል።

ለዚህ ዘረፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነው ደግሞ ድሮ ቢያንስ አሳታሚ ድርጅቶች ነበሩ ሲል ይገልጻል። በደርግ ዘመን የነበረው ሁኔታ ከአሁኑ እንደሚሻል ጠቁሞም፣ አንድ አገር አሳታሚዎች ሊኖሯት የሚገባ ቢሆንም፣ በደርግ የነበሩት አሁን ፈራርሰዋል ነው የሚለው።
በገበያ ላይ የምናያቸው መጽሐፍትን የሚያሳትሙት ነጋዴዎች ሲሆኑ፣ እነሱም ትርፋቸውን በማስላት መርጠው ነው የሚያሳትሙት። የድሮ ተወዳጅ የትርጉም ሥራዎችም መልሰው እየታተሙ ቢሆንም፣ ባለቤት የሌላቸው እስኪመስል ድረስ የአንዱን ሥራ ሌላው እየገለበጠ ሲያሳትም ይታያል ሲል ተናግሯል።

- ይከተሉን -Social Media

ስለዚህም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መድቀቅ፣ የደራሲዎች ሕይወት አለመሻሻል፣ የአሳታሚ አለመኖር፣ አስቸጋሪው የመጽሐፍት ስርጭት ሰንሰለት ይህ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ክፉኛ እንዲጎዳ ምክንያት ነው በማለት አክሏል።
በዚህም ትውልዱ መጽሐፍትን ከማንበብ እየራቀ ወደ ዲጅታል ዓለሙ ተሰንቅሯል። እንኳንስ ወጥ ድርሰት አንብቦ ለመጨረስ አጫጭር ታሪኮችን ለማንበብም ትዕግስቱን ተነፍጓል የሚል ዕይታ አለው።

የአንድ አገር የጥበብ ሥራ ውድቀት የአገሪቱ አጠቃላይ ውድቀት ማሳያ ነው ይላል ደራሲው። አክሎም፣ ኪነጥበብ ትውልድ የሚቀረጽበት፣ ማኅበረሰብን ለማረቅ፣ የመንግሥታት ክፍተት የሚታይበት፣ ሕዝብ ወደ መልካም ጎዳና የሚሄደበት በጥቅሉ የአገር፣ የትውልድና የዘመን መልክ የሚገለጥበት ነው ይለዋል።

ስለዚህ፣ ይህ ዘርፍ ተዳከመ ማለት፣ የሚመጣው ትውልድም እኩል የተዳከመና በክፍተት የተሞላ ይሆናል ባይ ነው። በኢትዮጵያ ይህን የሚያግዝ ተቋም ማየት ብርቅ ነው ይባላል። ደራሲውም ባህልና ቱሪዝም፣ የባህል ፖሊሲያችን ሳይቀር ይህን ዘርፍ ሲደግፉ አናይም ሲል ገልጿል።

5 ሺሕ ቅጅ ህትመት በ480 ሺሕ ብር!
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ተከትሎ የህትመት ገበያውም ክፉኛ እንደተነካ ይነገራል። የማሳተሚያ ዋጋ እጥፍ ሊባል በሚችል ደረጃ ጨምሯል ነው የተባለው።
በቅርቡ (ከአንድ ወር በፊት) አንድ ወዳጄ አንድ የትርጉም ሥራ ሠርቶ አምስት ሺሕ ቅጅ ለማሳተም ፈልጎ 480 ሺሕ ብር ተጠየቀ ይላል ደራሲ አንዷለም አባተ።
‹‹ይህን ገንዘብ ደግሞ እንኳንስ እሱ ዘመዶቹ ተሰብስበው እንኳን ሊያመጡት አይችሉም፣ የወረቀት ዋጋ ጣራ እየነካ ነው። ጉዳቱም ገና እየከፋ ሲሄድ እንመለከታለን።›› ብሏል።

ችግሩን ማቃለል አስፈላጊ ነው። ለዚህም መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አሳታሚዎች መምጣት አለባቸው። ደራሲዎችን ተጠቃሚ የማያደርገው የመጽሐፍ ስርጭት ሰንሰለቱም ሊስተካከል ይገባል ነው ያለው።
‹‹በዓመት አንድ መጽሐፍ የሚያወጡ ደራስያንን’ኮ እንጥራ ብንል በጣም ጥቂት ናቸው፤ እናውቃቸዋለን። በዓመት ኹለት ጊዜ ማሳተም አይታሰብም። አንድ ጊዜ ያሳተመውን 2 ሺሕ ቅጅ ሸጦ መጨረስ ወይም ገንዘቡን መሰብሰብ እንኳን አይችልም።›› ሲል ጠቅሷል።
ስለዚህም፣ ልቦለዶች ማለት የትውልድን መልክና በወቅቱ የነበረውን ማኅበራዊ አውድ የሚያሳዩ ናቸው የሚለው ደራሲው፣ ለአብነትም በ1940ዎቹ የነበረውን ወቅት እንገንዘብ ሲል መለስ ብሎ ‹‹እንደወጣች ቀረች››ን ያወሳል።

‹‹‘እንደወጣች ቀረች’ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ሴተኛ አዳሪነት ምን ያህል እንደተስፋፋ፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና የሥነ ልቦና ውድቀት ምን ያህል እንደሰፋ የምናይበት ነው። እስከ 1980ዎቹ የነበረውን ዘመን ሁኔታ ለማወቅ የሚረዱንም የታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች አሉን። ያለንበትና የቀጣዩ ትውልድ ዘመን በሚገባ አለመጻፉ ግን ያሳስበናል›› ሲል ሐሳቡን አጋርቷል። ስለሆነም መንግሥት ይህን ዘርፍ ሊታደገው ይገባል ሲል አሳስቧል።

ደራሲያን ይበረቱ ዘንድ!
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዓሊያን የውጭ ዕድል አላቸው፣ የተሻሉም ናቸው። ሙዚቀኞችም እንዲሁ የተሻለ ደረጃ የመድረስ ዕድላቸው የሰፋ ነው። ጦሙን የሚያድር ሙዚቀኛም የለም። ደራሲዎች ግን በፈተና የተሞሉ ናቸው። ድርሰት በባህሪውም ዋጋ ያስከፍላል። ሆኖም ግን ይላል ደራሲ አንዷለም፣ ደራሲያን አላሳተሙም ማለት አይጽፉም ማለት አይደለም።

‹‹ደራሲያን ጽሕፈት ሥራቸው ሕይወታቸው ነው። የመጡበት ነው። ያዩትንና የሚሰማቸውን ለመጻፍ ነው የመጡት። የእግዜር ጣት ሆነው፣ የዘመንና የትውልድ ጣት ሆነው ነው የመጡት። አለማሳተም እንጂ አለመጻፍ አይደለም የማይችሉት።›› ሲል ይናገራል።
ይቀጥላል፤ ‹‹በእያንዳንዱ ደራሲ ቤት ብንሄድ በርካታ ያልታተሙ ቅጅዎችን እናገኛለን። ደራሲ ካልገደልነው በስተቀር የተሰማውንና ያየውን ከመጻፍ ወደኋላ አይልም። ሲጀመርም ደራሲ ጸሐፊ እንጂ አሳታሚ አይደለም።›› ብሏል።
ስለዚህ መጻፍ ሌላ፣ ማሳተም ሌላ ነው። ደራሲያን የዘመናቸውን መልክ አስቀምጠው ማለፋቸው ስለማይቀር፣ እያሳተሙ ባይሆንም እየጻፉ እንደሆነ ግን እንረዳለን ብሏል ደራሲው።
ከዚህ ዘርፍ ድክመቶች አንዱ በየጊዜው ስለሚታተሙ መጽሐፍት ይዘትና አጠቃላይ ዝርዝር መረጃ የሚሰጥ ተቋም አለመኖሩ መሆኑም ይጠቀሳል።

- ይከተሉን -Social Media

አዲስ ማለዳም መረጃው ይኖር እንደሆን በሚል የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት ብትጠይቅም፣ ተቋሙ የረዥም ልቦለድ መጽሐፍት ግብዓት ዕጥረት እንዳለበትና ለደንበኞቹም የሚፈልጉትን መጽሐፍት ለማቅረብ እንደተቸገረ ገልጿል። በየዓመቱ ምን ያህል ረዥም ልቦለዶች እንደሚታተሙና ምን ያህል ቅጅ እንደተሸጡ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት አልቻለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች