አርብ ግንቦት 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ተወያይቶ በ2015 በጀት 786 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም አኳያ፣ የአገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም፣ ቀጣይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን ማሳካት ማእከል በማድረጋ እንዲሁም የ2015-2019 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፉን መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ለ2015 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ ብር 347 ነጥብ 12 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218 ነጥብ 11 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209 ነጥብ 38 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 12 ቢሊዮን የተያዘ ሲሆን አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ብር 786 ነጥብ 61 ቢሊዮን ሆኖ ቀርቧል፡፡
ይህም ከ2014 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የብር 111 ነጥብ 94 ቢሊዮን ወይም የ16 ነጥብ 59 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበለት የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ፤ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ያስረዳል።



