የሀሮ ከተማ አስተዳዳሪ ታስረዋል ተባለ

0
1297

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሀሮ ከተማ አስተዳዳሪ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከኦነግ ሸኔ ጋር ጦር እንዲማዘዙ መክረዋል ተብለው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

በተለያዩ ቦታዎች በኦነግ ሸኔ ቡድን የሚፈጸመውን ጥቃት ለመቆጣጠር እና የአካባቢውን ሰላም ለማስፈን ታስቦ መስከረም 20/2014 የሀሮ ከተማ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ፍቃዱ ወልዴ፣ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ነዋሪዎቹ አስተዳዳሪው ከተማዋን በኃላፊነት ሲያገለግሉ ነበረ ሲሉ ጠቅሰው፣ ግንቦት 24/2014 “የአካባቢው ነዋሪዎችን በየጊዜው በመሰብሰብ እና በማወያየት ከኦነግ ሸኔ ጋር ጦር እንዲማዘዙ መክረሃል” ተብለው በመንግሥት የጸጥታ አካላት ተይዘው ታስረዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች አክለውም፣ የከተማዋ አስተዳዳሪ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ተይዘው ከመታሰራቸው ውጪ የታሰሩበትን ቦታም ሆነ የት እንዳሉ አናውቅም ያሉ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናከረችበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ጭምጭምታ እንዳልተሰማም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ከተማ እና በተለያዩ አካባቢዎች የኦነግ ሸኔ ቡድን ያለ በመሆኑ እና ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በየጊዜው ጥቃት የሚፈጸም ሲሆን፣ አስተዳዳሪው በጸጥታ አካላት ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በሀሮ ከተማ እና በአዋሳኝ ቀበሌዎች የጸጥታ ስጋት መኖሩንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው የሀሮ ከተማን ሲመሩ በቆዩበት ባለፉት ዘጠኝ ወራት፣ በከተማዋም ሆነ በአጎራባች አካባቢዎች በኦነግ ሸኔ ሲፈጸም የነበረውን ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ማለት ባይቻልም፣ መቆጣጠር የተቻለበት ሂደት እንደነበር ተመላክቷል። ነዋሪዎች አክለውም፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ሸኔ ቡድን በዜጎች ላይ ጥቃት እንዳያደርስ የከተማዋ አስተዳዳሪ ኅብረተሰቡ በቅንጅት ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን እንዲጠብቅ በማድረግ ረገድ እያበረታቱ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም አስተዳዳሪው የከተማዋን የኅብረተሰብ ክፍል በየወቅቱ ስብሰባ በመጥራት ያደርጉት የነበረው ውይይት አካባቢውን ከፀጥታ ስጋት ለመከላከል የነበረ ሲሆን፣ ከአስተዳዳሪው በተጨማሪ ሌሎች 28 የከተማዋ ነዋሪዎች ከኦነግ ሸኔ ጋር ተኩስ ተታኩሳችኃል በሚል መከሰሳቸውም ተነግሯል።

በወረዳው በየወቅቱ በቡዱኑ ጥቃት ይፈፀምብናል በማለት ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች አሁንም እንዳሉ እና በወረዳው መረጃውን እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ከ45 ሺሕ በላይ ሰዎች በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ ተብሏል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ኃይል በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ በተለያዩ ቦታዎች ተሰማርተው ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ ቢሆንም፣ ቦታው ከኦነግ ሸኔ ቡድን አለመጽዳቱን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ በኦነግ ሸኔ ቡድን ጥቃት ከመክፈት ባለፈ በወረዳው የሚኖሩ ዜጎች ማንነትን መሠረት በማድረግ ሰዎች እየተገደሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሲናገሩ እንደነበር አይዘነጋም። አዲስ ማለዳ ስለ አስተዳዳሪው እስር መረጃ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here