ብሔራዊ ባንክ በተለያየ ምክንያት ወደ ውጭ አገር ለሚሄዱ ዜጎች የሚፈቅደው የውጭ ምንዛሬ መጠን በጣም አናሳ በመሆኑ ባለጉዳዮች ወጭያቸውን ለመሸፈን አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገለጹ።
በዚህም በቅርቡ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ዕቅድ የያዙ ሰዎች፣ ብሔራዊ ባንክ ወደ ውጭ አገር ለሚሄዱ ዜጎች የሚሰጠው የውጭ ምንዛሬ 200 ዶላር መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንም ለምንም የማይሆን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ፣ በቀጣይ ሳምንት ወደ ሩስያ ሞስኮ በግል ጉዳይ በረራ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ሆኖም ግን ብሔራዊ ባንክ የሚሰጠኝ 200 ዶላር ብቻ እንደሆነ ስለሰማሁ ከሄድኩኝ በኋላ የሚያጋጥመኝ ሁኔታ እጅግ አሳስቦኛል ነው ያሉት።
በትንሹ የሦስት ወር ቆይታ እንዳላቸው የተናገሩት ግለሰቡ፣ ሞስኮ ከደረስኩኝ በኋላ 100 ዶላር የሚወስድ የአገር ውስጥ በረራ ይጠብቀኛል። የቆየሁኝ እንደሆነም የሕክምና ኢንሹራንስ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ 70 ዶላር ወዲያው እከፍላለሁ። ስለሆነም፣ ብሔራዊ ባንክ ከሰጠኝ 200 ዶላር ውስጥ የሚቀረኝ 30 ዶላር ብቻ በመሆኑ፣ ለምግብ፣ ቤት ኪራይ እንዲሁም የትራንስፖርት ወጭ በምን እንደምሸፍን አላውቅም ነው ያሉት። የምሄድበትን ጉዳይም ያለ ገንዘብ እንዴት እንደማስፈጽም ግራ ገብቶኛል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሆኖም የመጨረሻ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ ኤጀንሲ ኮሚሽን እስከ 30 ሺሕ ብር በመክፈል፣ እዚያ ያለኝን ወጭ የሚሸፍን ብር እዚህ ለኤጀንሲው መክፈል ነው ብለዋል። ይህም እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን እየፈተነ ያለ ጉዳይ በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።
ሌላኛው በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው የተመለሱ ባለጉዳይ፣ ብሔራዊ ባንክ 200 ዶላር ነው የምሰጥህ ስላለኝ፣ ይህ ለምንም እንደማይሆነኝ ስላወቅሁ ያለ አንድ ዶላር ነው ከኢትዮጵያ የወጣሁት ብለዋል። የደርሶ መልስ ጉዞም ሆነ እዚያ የነበረኝን ወጭ የጋበዘኝ ተቋም ስለቻለልኝ አልተቸገርኩም። ውጭ አገር ለሚሄድ ባለጉዳይ 200 ዶላር ብቻ መስጠት ግን እንደ አገር አሳሳቢ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራትም፣ ወደ ውጭ አገር የግል ጉዳይ ኖሯቸው ከሚሄዱ ብዙዎች ከጥቁር ገበያ ዶላር ገዝተው በድብቅ ይዘው ለመውጣት ሙከራ ያደርጋሉ። ለትምህርት፣ ለንግድ፣ ለጉብኝት እና ሌሎች ጉዳዮች ከሚሄዱት በተለይ ለሕክምና የሚሄዱ ሰዎች በዶላር እጥረቱ ከፍተኛ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተጠቅሷል።
አዲስ ማለዳ የቀረቡ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ፈልጋ ብሔራዊ ባንክን ብትጠይቅም፣ በቀጠሮ ካልሆነ መረጃው አይሰጥም መባሉን ተከትሎ በወቅቱ መረጃውን ማግኘት አልተቻለም። ስለሆነም፣ በተሰጣት ቀጠሮ ምላሽ ካገኘች ወደፊት የምታሳውቅ ይሆናል።
ገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በዚህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ብሔራዊ ባንክ መሆኑን ጠቅሶ፣ ካለው ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ አንጻር ከዚህ በላይ አልሰጥም ሊል ይችላል ነው ያለው።
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥማቸውን ያልገለጹ አንድ የሥራ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ ብሔራዊ ባንክ በፊት 500 ዶላር ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ወደ 200 ዶላር ዝቅ ያለው በቅርቡ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተጨማሪም፣ ከውጭ አገር የሥራ አበል ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለገንዘብ ሚኒስቴር የመጣ መመሪያ እንዳለና በዚያ መሠረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



