በኦቲዝም ተጠቂ ሆነው የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መምጣቱ በጥናት እንደተረጋገጠ የዘርፉ ምሁራን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተጠና ጥናት ባይኖርም፣ አንዳንድ አገሮች ባረጋገጡት መሠረት ኦቲዝም አብሯቸው የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በነህሚያ የኦቲዝም ማዕከል ፕሮግራም አስተባባሪና ሳይኮሎጂስት ቴዎድሮስ ጌጥዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ለአብነትም በአሜሪካን አገር ከሚወለዱ 33 ሕፃናት መካከል አንዱ ኦቲዝም ያለበት ሆኖ እንደሚወለድ በ2022 የወጡ ጥናቶች አመላክተዋል ሲሉ ነው ቴዎድሮስ የገለጹት። እንደ ቴዎድሮስ ገለጻ ከሆነ፤ ከእናቶቻቸው ማሕጸን በሽታው ተቆራኝቷቸው የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መሆኑን ነው። ለአብነትም በ2014 በተጠኑ ጥናቶች መሠረት ከሚወለዱ 59 ጨቅላ ሕፃናት አንዱ ከኦቲዝም ጋር ይወለድ እንደነበር ቴዎድሮስ ያስታወሱ ሲሆን፤ 2020 በወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ ከሚወለዱ 50 ሕፃናት መካከል የኦቲዝም ተጠቂ ሆኖ የሚወለደው አንድ ልጅ ብቻ ነበር።
በያዝነው ዓመት ግን የጨቅላ ሕፃናት ከኦቲዝም ጋር የመወለድ እድል ከ50 መካከል አንድ የነበረው ከ33 መካከል አንድ ሕፃን ከኦቲዝም ጋር አብሮ ወደሚወለድበት ደረጃ ከፍ ብሏል ነው ያሉት። ባለው መረጃ መሠረት ቁጥሩ እንደጨመረ ነው የሚያመላክተው ያሉት ቴዎድሮስ፤ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በ90ዎቹ ከ10 ሺሕ መካከል አንድ ልጅ፤ ቀስ በቀስ ከአምስት ሺሕ ሕፃናት አንድ፤ ከዚህም አልፎ በ2000 ደግሞ ከ60 ልጅ አንድ ልጅ ኦቲዝም ተቆራኝቶት ይወለድ ነበር ተብሏል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ አሁን ላይ ከ33 ልጅ አንድ ልጅ ከኦቲዝም ጋር መወለዱ አሳሳቢ ደረጃ እንደደረሰ ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።
ችግሩ አሳሳቢ ነው ያሉት ቴዎድሮስ፣ ከሕፃናቱ ባሻገር ለወላጆችና አሳዳጊዎችም ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለውም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ደረጃ እንኳን የተጠኑ ጥናቶች ዳውን ሲንድረም፤ ኦቲዝም እና ሌሎች እክሎችን ለይቶ የሚታወቅበት ሁኔታም የለም ብለዋል ቴዎድሮስ። አንዳንድ ሆስፒታል አካባቢ ያሉ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ድብልቅ እክሎችን እንጂ ለየት ያለ ስለኦቲዝም የተጠና ጥናት ማግኘት እንደማይቻልም ጠቅሰዋል።
‹‹ስለኦቲዝም ብቻ ተለይቶ ሳይሆን በድብልቅ ደረጃ የዛሬ ሰባት እና ስምንት ዓመት አካባቢ፣ ኦቲዝም ያላቸው ልጆች ብዛት እስከ 500 ሺሕ ይገመት ነበር። በቅርቡ ደግሞ ከ500 ሺሕ እስከ 700 ሺሕ ይገመት ነበር። አሁን ከዚያ ሊበልጥ ይችላል።›› ብለዋል ቴዎድሮስ። በመሆኑም፣ በኢትዮጵያ ጉዳዩን የተመለከተ ጥናት አለመደረጉ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።
ከ20 ዓመት በፊት አንድ የኦቲዝም ትምህርት ቤት ነው የነበረው ያሉት ቴዎድሮስ፣ አሁን ላይ በበጎ አድራጎት ደረጃ አራት ረጂዎች፤ በትምህርት ቤት ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ በመሆኑ መሻሻል ቢታይም፣ ከዚህ የበለጠ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በዘርፉ ሙያ ያላቸው መምህራን እጥረት በመኖሩ ወላጆች ሲያማርሩ ይሰማሉ ያሉት ቴዎድሮስ፤ መንግሥት እንደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች የኦቲዝም እክል ያለባቸው ልጆች የሚማሩበት ተቋም ከፍቶ በሙያው ብቁ የሆኑ መምህራንን በመቅጠር የድርሻውን ቢወጣ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



