”በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለመማር ማስተማር ውለዋል”:- ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

0
862

ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለመማር ማስማር መዋላቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ማዳበር የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ኹለተኛው አገር አቀፍ የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ጉባኤ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል።

ጉባኤው የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ለአገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ያለው ፋይዳና ለመንግስት የቋንቋዎች ፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ እንደተዘጋጀ ተነግሯል።

የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ባህልና ቋንቋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ቋንቋዎቿን ለማልማትና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ውስጥ 53ቱ ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ለትምህርት አገልግሎት መዋላቸውንና በቀጣይም የቋንቋዎቹን ቁጥር ለመጨመር መታሰቡን ተናግረዋል።

ከኹለት ዓመት በፊት የጸደቀውን የቋንቋ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የቋንቋ ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ለማሳደግና ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ላለፈው አንድ ዓመት በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን አመልክተዋል።

በጥናቱ ምክረ ሀሳብ አማካኝነት የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ለማዳበርና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል መነሻ ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን ነው ብርቅነሽ ያብራሩት።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርስቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለማህበራዊ፣ኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳዎች ለማዋል እያደረገ ያለውን ጥረት በጥናትና ምርምር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

የቋንቋዎች ልማት እንዲሁም የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ማጎልበት በቀጣይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኹለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት አስመልክቶ የተዘጋጁ ጥናቶችና የምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here