የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የኢትዮጵያን የምግብ ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ከምርት እስከ ተጠቃሚነት ያለውን ሰንሰለት መጠበቅ እጅግ አስፈላጊና አሳሳቢ ነው ያለው ባለሥልጣኑ፣ ከባለድርሻ አካላትና ከልማት ድርጅቶች ጋር የምግብ ደኅንነትን የሚያስጠብቁ ስትራቴጂዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን ሲል ተናግሯል።
የምግብ ደኅንነትን ከሚያስጠብቁ የስትራቴጂ ቀረጻ ሥራዎች መካከል የምግብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አሳውቋል።
ረቂቁ የምግብ ደኅንነትን ከእርሻ ጀምሮ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚለውን ተሞክሮ ከሌሎች ሀገራት የወሰደ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ከዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት መነሻ የሚሆኑ ሐሳቦችን አካትቶ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ስትራቴጂው በምግብ ምርትና ጤና አጠባበቅ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በተጠናከረ ቅንጅት እንዴት መሥራት አለባቸው የሚለውንም በዋናነት ያቀፈ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉ ተጠቁሟል።
የሚኒስቴር ተቋማትን ጨምሮ የዘርፉን ተዋናዮች ያካተተ ኮሚቴ የምግብ ደኅንነት ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን የማስጸደቅ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ያለው ባለሥልጣኑ፣ የምግብ ምርት ተቋማት በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የሚወጡ የምግብ ደኅንነት ግዴታዎችን በመተግበርና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት አለባቸው ብሏል።
በዓለም ለ4ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ “ደኅንነቱ የተረጋገጠ ምግብ ለመልካም ጤና’’ በሚል መሪ ቃል የምግብ ደኅንነት መጠበቅ እየታሰበ በነበረበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በምግብ ደኅንነት አለመጠበቅ ምክንያት ዜጎች ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ ብሏል።
የምግብ ደኅንነት አለመጠበቅ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው በየዓመቱ ከግንቦት 30 ጀምሮ በዘመቻ መልክ እንዲታሰብ ማድረጉ የተወሳ ሲሆን፣ የምግብ ደኅንነት አለመጠበቅ በኅብረተሰቡ ውስጥ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግርን እንደሚያባብስ ተነግሯል።
በዓለም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች በምግብ መበከል ምክንያት ሲታመሙ፣ 400 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014


