ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚSራው ሄፍሊ (Hefli Electronic Waste Recycling) የተሰኘ ተቋም የግብዓት እጥረት እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ተቋሙ በአገሪቱ በቂ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት ቢኖርም፣ በግንዛቤ እጥረትና በቢሮክራሲ መብዛት የተነሳ ግብዓቱን እንደልብ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል።
ብዙ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ያሉት የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በመሆኑም፣ ቢሮክራሲውን አልፎ እነዚህን ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ነው ተቋሙ ያስገነዘበው።
የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ካሳው፣ ማንኛውም ኤሌክትሪክ የሚያልፍባቸው ዕቃዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው ካለቀ በኋላ ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ይሆናሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ የተቋማችን ሥራ እነዚህን ቆሻሻዎች የሰውን ጤናና የአካባቢን ደኅንነት በማይጎዳ መልኩ ማስወገድና እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው ብለዋል።
በዚህም እንደገና ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉትን በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል (recycle) እንሠራለን። በእኛ አቅም መሆን የማይችሉትን ደግሞ ወደ ውጭ እንዲላኩ እናደርጋለን ነው ያሉት። ሆኖም ኹሉንም እዚሁ አገራችን ውስጥ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጎ ለመሥራት እየተጫኑ ያሉ ማሽኖች አሉ ሲሉ ጠቁመዋል።
እነዚህ አደገኛ ተብለው የሚጠሩ ቆሻሻዎች ካልተወገዱ ለካንሰር፣ የአዕምሮ ሕመምና ሌሎች በሽታዎች ያጋልጣሉ ሲሉም አመላክተዋል።
አክለውም፣ በሌሎች የአገራት አንድ ደንበኛ የገዛውን ኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ተጠቅሞ ሲጨርስ፣ ሰው እና አካባቢን ሳይጎዳ በሕጋዊ ድርጅት መወገዱን ለአምራች ድርጅቱ ካሳወቀ ይከፈለዋል። ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ አይደለም ብለዋል።
በዚህም ዕቃዎችን የምንገዛው ተወዳድረን በጨረታ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ አንዳንድ ድርጅቶች ናቸው ቅድሚያ እየሰጡን ያሉት ሲሉ ተናግረዋል።
ተወዳዳሪ ሆነን ስንቀርብም እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኢትዮ-ቴሎኮም ያሉ ድርጅቶች ካላቸው የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት በገንዘብ ለመግዛት ቅድሚያ ይሰጡናል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ የነበረ አንድ በመንግሥት የተቋቋመ ድርጅት የነበረ ቢሆንም ከተዘጋ ኹለት ዓመት አልፎታል ካሉ በኋላ፣ በአሁኑ ወቅትም እርሳቸው ከሚመሩት ተቋም (ሄፍሊ) ውጪ፣ በ2010 በወጣው ደንብ መሠረት በዚህ ዘርፍ ሕጋዊ ፈቃድ ወስዶ የሚሠራ ሌላ ተቋም አለመኖሩን አመላክተዋል።
ሆኖም ተቋሙ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በጨረታ በመግዛት እና ጨረታ አሸንፈው ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎችን ከገዙ ሌሎች ድርጅቶች መልሶ በመግዛት ሥራው እንደቀጠለ ገልጿል።
ቀስ በቀስም የተለያዩ ተቋማት ግንዛቤ እየተፈጠረላቸውና ያላቸውን የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት የመሸጥ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተመላክቷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2010 ባወጣው የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ደንብ መሠረት፣ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ማለት ከጨረር አመንጭ መሣሪያዎች ውጪ ኹሉም ዓይነት የተጣለ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ እና የመሣሪያ ክፍል ነው።
በዚህም የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ (E-waste) ከአደገኛ ቆሻሻ ምድብ ውስጥ ተካትቶ ይገኛል።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014



