በአዲስ አባባ 16 በመቶ ነዋሪዎች ለውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ደንበኛ አይደሉም ተባለ

0
1264

50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ፍሳሽን በመስመር አይጠቀሙም

በአዲስ አበባ 16 በመቶ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ደንበኛ አለመሆናቸውን ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽን በማስወገድ ረገድ በተቋሙ ተደራሽ የተደረጉት 246 ሺሕ የሚሆኑ ደንበኞች ናቸው። ከእነዚህም መካከል 196 ሺሕ የሚሆኑት ደንበኞች ፍሳሽን በመስመር ወይም በዘመናዊ መልኩ የሚያስወግዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 50 ሺሕ ደንበኞች ግን ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ተጠቃሚ አይደሉም ሲሉ የፍሳሽ ማሰባሰብ፤ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ዐቢይ የሥራ ሂደት መሪ መሐመድ ካሳው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በመሆኑም 84 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ደንበኛ ሲሆኑ፤ 16 በመቶዎቹ ግን አይደሉም። ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው መጸዳጃ ቤቶችን ከፍሳሽ ማስወገጃ በመስመር የሚያገናኝ ዝርጋታ አለመኖር ነው። በመሆኑም 602 ሺሕ የሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎቱን መጠቀም ቢችሉም ቀሪዎቹ የውሃ ደንበኛ ያልሆኑ ነዋሪዎች ግን ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ማወቅ ተችሏል።

የፍሳሽ መሠረተ ልማት በአዲስ አበባ በሦስት ማለትም፤ ምዕራብ፤ ደቡብ እና ምሥራቅ አዲስ አበባ ተብለው የተከፋፈሉ ሲሆን፤ ምዕራብ እና ደቡብ አዲስ አበባ ተደራሽ ቢደረጉም ምሥራቅ አዲስ አበባ ማለትም የካ፤ ቦሌ (በከፊል) እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች በቀጣይ ተደራሽ የሚደረጉ ናቸው ብለዋል ኃላፊው። እነዚህ ክፍለ ከተሞችም በቀጣይ የፍሳሽ ማጣሪያ ግንባታ እንዲደረግላቸው ለማድረግ የፋይናንስ ሂደቱ በዓለም ባንክ በኩል በጨረታ ላይ እንዳለ ገልጸዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ፍሳሽ አወጋገድን ለመጠቀም መጸዳጃ ቤቱም ሻወር ቤቱም ከማጣሪያው መስመሩ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ ግዴታ በየቤቱ የመስመር ዝርጋታ ያስፈልጋል ነው የተባለው።

ከ246 ሺሕ ውሃና ፍሳሽ አስወጋጅ ደንበኞችም በቀን 104 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ቆሻሻ ወደ ወንዝ እንደሚለቀቅ መሐመድ አብራርተዋል። በተያያዘም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሰባት በላይ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ያላቸው 42 የውሃና ፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎች እንዳሉ ተነግሯል።
መሐመድ ለአዲስ ማለዳ በተናገሩት መሠረት፤ ውሃና ፍሳሽ ባላቸው አቅም ልክ እየተወገደ እንዳልሆነ ማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ ባለሥልጣኑ በቀን 174 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ፍሳሽን የማስወገድ አቅም እንዳለው አንስተዋል።

በሌላ በኩል ከሚወገደው ውሃና ፍሳሽ በማጣራት ሂደት የሚመረቱ ተረፈ ምርቶች መኪና ለማጠብ፤ በመዲናዋ የሚገኙ አደባባዮች ያሉ አትክልቶችን ለማጠጣት እንዲሁም አስፓልት ለማጠብ ጥቅም እንደሚውሉ ተመላክቷል።

በመሆኑም በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ አካላትን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለሥልጣኑ ማስተር ፕላን አውጥቶ ጥናት ላይ እንደሆነና ተደራሽ እንደሚደረግ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መቆራረጡ እንዳለ ሆኖ በአጠቃላይ በከተማዋ በቀን ከሚሰራጨው 674 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ወደ ቆሻሻ ፍሳሽ ይቀየራል ሲሉም መሐመድ አክለው ተናግረዋል።

ፍሳሽን በተሽከርካሪ ማስወገድ የተጀመረው በ1980ዎቹ ሲሆን፤ ቀስ በቀስ በዘመናዊ መልኩ መጸዳጃ ቤቶችን ከፍሳሽ ማስወገጃ ጋር በመስመር በማገናኘት ፍሳሽን የማስወገድ ተግባር ግን 13 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በመጀመሪያ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 68/163፤ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 10/87 ለኹለተኛ ጊዜ የተቋቋመ ሲሆን፤ ለኹለተኛ ጊዜ በወጣው አዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የውሃና ፍሳሽ አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ እየሰጠ ይገኛል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here