መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየነጭ ጋዝ ፍላጎት በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ

የነጭ ጋዝ ፍላጎት በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ

የነጭ ጋዝ ወይም ኬሮሲን ፍላጎት በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ። በብዙ ማደያዎች እንዲሁም ነዳጅ ቸርቻሪዎች ዘንድ አለመኖሩን ተከትሎ በተጠቃሚዎች ዘንድ እጥረት እንዳለ ተደርጎ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ተቋሙ ግን እጥረት ሳይሆን ፈላጊ ነው የሌለው ሲል አስታውቋል።

በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በኃላፊነት የሚሠሩና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሥራ ኃላፊ፣ ነጭ ጋዝ ከመጠቀም ኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ በከተሞች በቤት ውስጥ ለማብሰያነት ማገልገሉ እየቀረ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም አሁን ላይ በብዙ ማደያዎች ነጫ ጋዝ እንደማይገኝ ተናግረዋል።

ያለውም ለቀለም መበጥበጫ እና ለኮንስትራክሽን ሥራዎች እንጂ ለኃይል ምንጭነት ገጠር ላይ አልፎ አልፎ ለማብሰያነት ካልሆነ በስተቀር እንደ አጠቃላይ ፍላጎቱ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ይሁን እንጂ፣ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም ቢሆን መንግሥት ከውጭ እያስገባው መሆኑን ጠቅሰው፣ በወር ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ሊትር ነጭ ጋዝ ይሸጣል ነው ያሉት። ይህም ከቤንዚን ጋር ሲነጻጻር አንድ ዐስረኛ መሆኑን ያነሱት የሥራ ኃላፊው፣ ቤንዚን ግን በወር ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ሊትር ይሸጣል ብለዋል። አክለውም፣ ናፍጣ ከ250 እስከ 270 ሚሊዮን ሊትር በአንድ ወር ውስጥ ለፍጆታ እንደሚውል ነው ያመላከቱት።

ከዓመታት በፊት ለምግብ ማብሰያ ይውላል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በመንግሥት ድጎማ ይደረግለት ነበር። ሆኖም ማደያዎች ሳይቀር ከናፍጣ ጋር እየቀላቀሉ በመሸጥ ስላስቸገሩ ዋጋው ከናፍጣ ጋር እኩል ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህም ዋጋው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከናፍጣ እኩል ከ35 ብር እስከ 43 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

እንዲሁም ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከ2012 ዓመት ጋር ሲነጻጸር የናፍጣ ፍላጎት በአራት በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ በአንጻሩ የቤንዚን ፍላጎት ግን በ13 በመቶ መጨመሩን መግለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸው የነዳጅ ምርት ዓይነቶች አምስት ዓይነት ሲሆኑ፣ እነሱም ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ኹለት ዓይነት ናፍጣዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

በዚህም ቤንዚን በዓመት እስከ 700 ሺሕ ሜትሪክ ቶን፣ ናፍጣ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም እስከ 70 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የተለያየ ዓይነት የኢንዱስትሪ ናፍጣ በየዓመቱ እንደሚገባ ነው በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኩል ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት የተጠቆመው።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነጭ ጋዝ ወይም በተለምዶ ላምባ ተብሎ የሚጠራው ነዳጅ በአሁኑ ወቅት ያለው ፍላጎት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በምን ያህል አሃዝ እንደቀነሰ ለማወቅ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ደጋግማ ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች