በክፍያ ስርዓት ምክንያት መዘግየቱ የተነገረለት የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ የወጪ ዋጋ ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ተናገረ።
በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ያለው “አደይ አበባ ስታዲየም” የሚል ሥያሜ የተሰጠውና ግንባታው በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በመከናወን ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም፣ በታህሳስ 2008 ነው ግንባታው የተጀመረው። የስታዲየሙ የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተጠናቀቀለት ሲሆን፣ 62 ሺሕ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም አለው።
የኹለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በኹለት ዓመት ከስድስት ወር ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ2012 ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን 50 በመቶ እንኳን መከናወን እንዳልተቻለ ተነግሯል።
የዘገየበት ዋና ምክንያት የተባለው፣ ከክፍያ ስርዓት ጋር በተፈጠረ ችግርና በኮሮና ቫይረስ መከሰት ሳቢያ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ አሳውቀዋል። ግንባታው የዘገየው ስታዲየሙ የሥራ ተቋራጩ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግ በመጠየቁ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ 40 በመቶ በውጭ ምንዛሬና 60 በመቶ በብር የነበረውን የክፍያ አፈፃፀም ስምምነት እንዲሻሻል መጠየቁንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
መንግሥት ማሻሻያውን ለማድረግ ዝግጁ ቢሆንም ተቋራጩ የጠየቀው ማሻሻያ ተጋኗል የተባለ ሲሆን፣ የዓለምና የሀገር ውስጥ እቃዎችን መናር ተከትሎ ጥያቄው ግን ተገቢ ነው ተብሏል።
የግንባታ ሂደቱም መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ በተቋራጩ የተጠየቀው የዋጋ ማሻሻያ ከዚህ በፊት ለተሠራው ጭምር በመሆኑ እስከ አሁን ስምምነት ላይ አለመደረሱ ተነግሯል።
በኹለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሠራሽ ሀይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራ መግጠም፣ ሳውንድ ሲስተም መዘርጋት፣ የፓርኪንግ ቦታዎች፣ የተጫዋቾች የመለማመጃ ሜዳ እና ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



