በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የሚገኙ 44 ሺሕ 200 ተፈናቃይ ዜጎች ከባለፈው መጋቢት 2014 ጀምሮ ይደረግላቸው የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ተፈናቃይ ዜጎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ እና በየጊዜው በአካባቢው በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 44 ሺሕ 200 ደርሷል።
እነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች በመንግሥት በኩል የሰብዓዊ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ከባለፈው መጋቢት ወር 2014 ጀምሮ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ድጋፉ እንደተቋረጠባቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮች አክለውም፣ የምንበላው አጥተን ባዶ እያደርን እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣ ለሚመለከታቸው አካላት እሮሯችንን ብናሰማም ምላሽ አላገኘንም ብለዋል። በተደጋጋሚ ለወረዳ፣ ለክልል እና ለፌዴራል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቤቱታ በማቅረብ ድምፃችንን ብናሰማም መረጃው እዚህ ግባ የሚባል መፍትሔ አላስገኘንም ሲሉ ተናግረዋል።
ድጋፉ ከተቋረጠ ሦስት ወር ከ15 ቀናት እንዳለፈው በመጠቀስ ለምን እንደተቋረጠ ግን አናውቅም ያሉት ተፈናቃይ ሰብስቤ ቸርነት ናቸው። የወረዳው መንግሥት ከክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ችግራችንን በመረዳት በአስቸኳይ ሕይወታችንን እንዲታደገን እንማጸናለን ሲሉም ጠይቀዋል።
ሌላው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተፈናቃይ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ ከተፈናቀሉ ስድስተኛ ዓመት ደፍኖ ሰባተኛ ዓመት ልንሻገር ቀናት እንደቀሩ ጠቅሰዋል። አሁን ላይ የሚበሉት እና የሚቀመስ እንደሌላቸው እና ጠያቂ አካልም የለም ያሉ ሲሆን፣ እርዳታ ከተቋረጠ አራት ወር እንዳለፋቸው አስረድተዋል።
ተበታትነው በተለያዩ ቀበሌዎች እንደሚኖሩ የገለጹት ተፈናቃዩ፣ ‹‹ሸራ ውስጥ ነበር የምንኖረው። አሁን ግን ተቀዶ አልቋል።›› ብለዋል። አክለውም በረሀብ መቸገራቸውን ገልፀው፣ ሕጻናትና ልጆቻቸው እጅግ የከፋ አደጋ ላይ መውደቃቸውንም ተናግረዋል።
‹‹የውስጡ አይነገርም እንጂ ለሚዲያ መግለጽ የማንችለው ዘረፈ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥሞናል›› ያሉት ተፈናቃዮች፣ በተለይ ስለምግብ ጉዳይ እንደተፈናቃዮቹ ገለፃ ከሆነ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ቢረዳቸው እና በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ያለንበትን ሁኔታ ዐይተው ድጋፍ ቢያደርጉ ነፍስን የመታደግ ዕድል ይኖራል ሲሉ ተናግረዋል።
ችግሩ እንዲባባስ ከፍተኛ ጫና የፈጠረው ቀለብ መቋረጥ እንደሆነ የተናገሩት ተፈናቃዮች፣ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ እልባት እንዲሰጥ ሲሉ ጠይቀዋል።
አዲስ ማለዳ የተፈናቃዮችን ቅሬታ አዳምጣ ስለ ጉዳዩ የጠየቀቻቸው የአማሮ ልዩ ወረዳ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሞያ ከበደ ቱሬ በበኩላቸው፣ የተፈጠረው ችግር እውነት መሆኑን አምነዋል።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከክልሉ መንግሥት ይላክ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ለተሽከርካሪ የሚሆን ቤንዚን እጥረት እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አካባቢው መላክ ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ጋር ችግሩን ለመቅረፍ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ልዩ ወረዳው እንዲገባ እየተነጋገርን ነው ሲሉም አስታውቀዋል። አክለውም፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው እና በተለይም የጃሎና የዶርባደ ቀበሌ ተፈናቃዮች እጅግ የከፋ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በሌሎች ቀበሌዎችም ችግሩ እንዳለ ያነሱ ሲሆን፣ በከፊል ከተፈናቀሉት ጋር ሲነፃፀር ግን ‹‹የእነርሱ ችግር ይብሳል›› ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የጠቀሱት፣ በተጨማሪ የሚቀርብላቸው የሴፍቲ ኔት ልማት ተጠቃሚ ካለመሆናቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014


