የአደባባይ አጭበርባሪዎች እና ሰለባዎቻቸው

0
1463
BitCoin Mining

በኢትዮጵያ በተለይ ወጣቱን የማኅበረሰብ ክፍል በአደባባይ የሚያጭበረብሩ፣ ራሳቸውን የሰንሰለታማ ንግድና ምልመላ ላይ የተመሠረተ የፒራሚድ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ደርጅት አድርገው የሚያቀርቡ አጭበርባሪዎች በየጊዜው ራሳቸውን እየቀየሩ ማጭበርበራቸውን ቀጥለውበታል። በዚህ ዓመት ደርቶ የታየው የዚሁ ዓይነት የማጭበርበሪያ ስልት የተጠቀመ ራሱን ‹Fias 777› ብሎ የሰየመ፣ የበርካታ ሰዎችን ገንዘብ ሰብስቦ መጥፏቱ ተሰምቷል።

በርካታ ሰዎችን በተለይ ወጣቶችን አጭበርብሮ የጠፋው Fias 777 ከዚህ ቀደም እንደ ‹ቲያንስ ኢትዮጵያ› ዓይነቶቹ የተጠቀሙትን ስልትና መንገድ ይዞ መቅረቡ የቀድሞው ቲያንስ አሰኝቶታል። ራሱን የሰወረው ይኸው ‹ Fias 777› በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የንግድ ፈቃድና እውቅና ሳይሰጠው እንዳሻው በስፋት ሲንቀሳቀስ ማንም ነገሬ ያለው አካል ባለመኖሩ ብዙዎች የማጭበርበሩ ሰለባ ሆነዋል።

አዲስ ማለዳ ባደረገቸው ማጣራት፣ ‹Fias 777› የተለያዩ የማኀበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅሞ በአጭር ጊዜ በርካታ ‹አባላትን› መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ ለዚህም አትራፊ የንግድ (የኮሚሽን ንግድ) ሥራ ይዞ እንደቀረበ አድርጎ ሰንሰለታማ የሽያጭና የምልመላ ስልት የሚባለውን እውነታ የሚመስል ስልት ተጠቅሟል። ከተጠቀማቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሁን ደብዛቸው የጠፋ ድረ ገጽ፣ የሞባይል መተግበሪያ፣ የቴሌግራም፣ ፌስቡክና የዋትሳፕ ገጾችንና ግሩፖችን ፈጥሮ በርካቶችን መሳብ ችሏል።

የዚሁ ሰላባ የሆኑ ወጣቶች፣ የቀረበላቸውን አሳማኝ የሚመስል አትራፊ የንግድ ሥራ ተማምነው ብር ከፍለው የገቡ ወጣቶች፣ አትራፊ የሚሆኑት ወይም በ‹Fias 777› እንደተነገራቸው ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ደረጃ የሚያገኙት፣ በስራቸው ሌሎች አባላትን ሲያስገቡ ነው። ይህ ዓይነቱ ተጭበርባሪዎችን የማብዛት ስልት ከዚህ ቀደም ከ250 ሺሕ በላይ ሰዎችን አጭበርብሮ የነበረው የቲያንስ ኢትዮጵያ ስልት ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ ቀድመው አባል የሆኑ ሰዎች አምነው ስለገቡበት የቅርብ ቤተሰብና ጓደኞቻቸውን አሳምነው አባል ያደርጋሉ።

የዚሁ ሰላባ የሆነችው አጸደ ገብረእግዚአብሔር የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቿ ባቀረቡላት ግብዣ (የአባልነት ጥያቄ) መሠረት አትራፊ የንግድ ሥራ መሆኑን አምና አባል ሆናለች። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገቸው አጸደ መለስ ብላ ስታስታውስ፣ ‹‹ከሦስት ዓመት በፊት የዩኒቨርሲቲ ጓደኞቿ የነበሩ ወጣቶች ትክክለኛ የንግድ ሥራ መሆኑን ስላሳመኑኝ የአባልነት ጥያቄውን ተቀበልኩ›› ትላለች።

በዚህም አባል ከሆነች በኋላ የራሷን ገንዘብ ላለማጣትና ትርፋማ ለመሆን ሌሎች ሰዎችን አባል ማድረግ እንደሚጠበቅባት ስለተነገራት፣ እርሷም እንደ ጓደኞቿ የምታውቃቸውን ሰዎች አሳምና አባል እንዳደረገች ትገልጻለች።

አጸደ እንደምትለው መጀመሪያ አባል ስትሆን ጓደኞቿ ባቀረቡላት አሳማኝ ሐሳብ መስማማቷንና አባል ከሆነች በኋላም አምናበት ለሌሎች ሰዎች ትክክለኛ ሥራ መሆኑን ለማሳመን ባገኘችው አጋጣሚ ትሞክር እንደነበር ታስታውሳለች። ይሁን እንጂ፣ አዋጭ የንግድ ሥራ ይዞ የቀረበ የመሰለው ‹Fias 777› አሳምነው አባል ያደረጓትና እርሷ አሳምና አባል ያደረገቻቸው ጓደኞቿን ጨምሮ እርሷ ራሷም ከጠፋ በኋላ ነው ማጭበርበር መሆኑ የገባኝ ትላለች። አጭበርባሪው አድራሻውን አጥፍቶ ከመጥፋቱ በፊት በተለያየ ሁኔታ የማጭበርበር ስልት መሆኑን ብትሰማም፣ እንደማታምንበትና ትክክለኛ የንግድ ሥራ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት ታደርግ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች።

በኢትዮጵያ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ፣ የተዛቡ መረጃዎችን በማረምና የማጭበርበር ድርጊቶችን በቀዳሚነት በማጋለጥ የሚታወቀው “ኢትዮጵያ ቼክ” ስለ Fias 777 ባደረገው ማጣራት፣ ሥራው ብዙ ሰዎችን ከስር በማስገባት የሚከናወን መሆኑን ይፋ አድርጓል። ቀድመው የገቡ ሰዎች በርከት ያለ ገንዘብ ሲያገኙ በርካቶች ግን ተጭበርብረው ይቀራሉ። ይህም ከዚህ ቀደም በጎልድ ኩዌስት፣ በ Tiens እና QuestNet በተባሉ ድርጅቶች ሲሠራ የነበረ ነው ሲል ኢትዮጵያ ቼክ ያብራራል።

Fias 777 የተባለው ድርጅት በተሰማራበት ድርጊት በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ እንዳጭበረበረ ይገመታል። ድርጅቱ ራሱን “በኮሚሽን የሚሠራ የማስታወቂያ ድርጅት” ብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ “ከተለያዩ የሶሻል ሚዲያ ኔትዎርኮች ጋር አብረን እንሠራለን” ይላል። እንደ ድርጅቱ አባባል ለምሳሌ በVIP 4 ደረጃ ላይ ያለ አንድ አባል፣ 10 ሺሕ ብር ከፍሎ ደረጃ ይሰጠዋል። በቀን ክሊክ የሚያደርጋቸው 17 ሥራዎችን ነው፣ ለአንዱ ሥራ 18 ብር ይከፈለዋል። ይህም በቀን 306 ብር ወይም በወር 9,180 ብር ይሆናል ይላል።

እንደ ኢትዮጵያ ቼክ ዘገባ ለድርጅቱ ክፍያዎች የሚፈፀሙት በአቢሲንያ ባንክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት ነው። ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባም ሆነ ቢሮ የሌለው መሆኑንና ባለቤቶቹ በግልጽ እንደማይታወቁ ነው። በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስልክ ቁጥር የሚያስቀምጥ ቢሆንም፣ አሁን ላይ አዲስ ማለዳ የሞከረቻቸው ስልኮቸ አገልግሎት አይሰጡም ወይም ዝግ ናቸው።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት በአጭበርባሪ ድርጅቱ አማላይ የንግድ ሥራ ተታለው ገንዘባቸውን የከሰሩ ሰዎች፣ ሥራውን የሚሠሩት አንዱ አንዱን በመሳብ ይሁን እንጂ የድርጅቱን አንቀሳቃሾች በውል እንደማያቋቸው ይገልጻሉ። እያንዳንዱ ሰው መጀመሪያ ያስገባውን እና ከገባ በኋላ ያስገባውን እንጂ በቅርበት የሚያውቀው ከመሠረቱ የሥራውን አንቀሳቃሾች ማንነት አይደለም።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባ እንዳካሄደ ቢገልፅም፣ ይህ ትክክል እንዳልሆነ ከንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ማረጋገጡን የመረጃ አጣሪ ተቋሙ ኢትዮጵያ ቼክ ገልጿል። ኢትዮጵያ ቼክ አነጋገርኩት ያለው የድርጅቱ ተወካይ ነኝ የሚል ግለሰብ፣ ድርጅቱ የሚሠራው ሥራ ምን እንደሆነ ተጠይቆ “ሰዎች የፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቲክቶክ እና ዩትዩብ ምስሎችን ሲጭኑ ተመልካች ይበዛላቸዋል። ለዚህም ከነፌስቡክ ክፍያ እናገኛለን። ከነሱ ጋር አብረን እንሠራለን” ብሏል። ይሁን እንጂ ተወካዩ እንዳለው፣ ወደተባለው የማኅበራዊ ሚድያ የሚወስድ ሊንክ እንደሌለ ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቼክ ኢዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ኤሊያስ መሠረት በበኩሉ፣ ድርጅቱ ከፌስቡክ ጋር መሥራት አለመሥራቱን በግሉ ጠይቆ፣ “ከዚህ ዌብሳይት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም” የሚል መልስ ደርሶኛል ብሏል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች እንዳሉት ሲገልጽ የነበረው Fias 777 በፍጥነት ብዙዎችን ሲያዳርስ እንደ ኢትዮጵያ ቼክ ያሉ የመረጃ አጣሪ ደርጅቶችና ግለሰቦችም ጭምር፣ ትክክለኛ የንግድ ሐሳብ አለመሆኑንና ሰዎች እንዳይጭበረበሩ ሲመክሩ ነበር። ይሁን አንጂ ብዙዎች በዚህ የማጭበርብር ስልት ተጠልፈው የድርጊቱ ሰለባ ሆነዋል። የዚህ ሰለባ የሆኑ ሰዎች “በአማላይ ጥሪ ተታለን ገንዘብና ጓደኞቻችንን አጣን” ይላሉ።
የዚህ ዓይነት የማጭበርበር ድርጊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በየጊዜው ሥማቸውን እየቀያየሩ በሚመጡ አጭበርባሪዎች ሰለባ የሚሆኑ ኢትዮጵያን ቁጥር ቀላል አይደለም። አጭበርባሪዎቹ የሚያቀርቡትን ሐሳብ ተቀብለው ብዙዎቹ ወደ ሥራ ቢገቡም፣ የሕጋዊነት የትክክለኝነት ጉዳዩን በአንክሮ ተከታትለው ሲያረጋገጡ አይስተዋልም።

የብዙዎችን ገንዘብ ሰብስቦ መሰወሩ የተሰማው Fias 777 ታድያ፣ ከዚህ በፊት ሥሙን እየቀያየረ ለዓመታት ሰዎችን ሲያጭበርብር የነበረው ቲያንስ ኢትዮጵያ ሥሙን ቀይሮ መጥቶ ነው የሚሉ የማንቂያ ሐሳቦችም ሲነሱ ነበር። ቲያንስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሥሙን እየቀያየረ ብዙዎችን ማጭበርበሩና መንግሥት በ2008 ደርጅቱን ማገዱ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ድርጅቱ በ2008 ከታገደ በኋላ ሥሙን ቀይሮ ከኹለት ዓመት በፊት የቀድሞ ሥራውን ሲሠራ እንደነበር ፋና ቲቪ በወቅቱ በሠራው የምርመራ ዘገባ አረጋግጫለሁ ብሎ ነበር። ሥራውን በበላይነት የሚመሩ ሰዎች ራሳቸውን በጥብቅ የሚደብቁ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ መቀመጫቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ አድርገው የሚሠሩ ናቸው።

ሥሙን እየቀያየረ አሁንም በማጭበርበር ሥራው መቀጠሉ የሚነገርለት ቲያንስ፣ አባላትን በማፍራት ለማጭበርበር ማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህን ሲያደርግ አንድ አባል በስሩ ቢያንስ አምስት አባላት እንዲያፈራ ያደርግ ነበር። አንድ አባል ወደ ድርጅቱ እንዲገባ ሲደረግ ብር እንዲከፍል ይደረጋል። አባል ወደዚህ ድርጅት ሲገባ የቅርብ ወዳጁን አለበለዚያም ቤተሰቡን አሳማኝ ሐሳቦችን በማቅረብ ወደ አባልነት ያስገባል። በወቅቱ የነበረው የማጭበርበር ስልት የተለያዩ መድኃኒቶችንና አልሚ ምግብ በነፃ ትሰጣላችሁ፣ መኪና ትሸለማላችሁ፣ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ጉርሻ ታገኛላችሁ በማለት ሳቢና አሳማኝ የሚመስሉ ማታለያዎችን ሲጠቀም ነበር።

ቲያንስ ሰዎች ለማጭበርበር ሲጠቀምባቸው የነበሩ መድኃኒቶች በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እውቅና የሌላቸው መሆኑ በወቅቱ ባለሥልጣኑ ይፋ አደርጎ ነበር።

ቲያንስ በዘረጋው የአባልነት መስፈርት መሠረት የቀረበለትን ሐሳብ ተቀብሎና ብር ከፍሎ አባል የሆነ ሰው፣ አምስት አባላትን ማፍራት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም አምስት አባላት ማፍራት ካልቻለ የከፈለው ብር ይከስራል። እያንዳንዱ በስሩ አምስት አባላት ማፍራት የሚችል አባል የተለያዩ ሽልማቶችና ኮሚሽን እንደሚያገኝ ይነገረዋል። ይሁን እንጂ ቲያንስ ኢትዮጵያ እንደተባለው ትርፋማ ማድረግና መኪና መሸለሙ ቀርቶ የሰበሰበውን ገንዘብ መመለስ አልቻለም።

እንዲህ ዓይነት አማላይና አዋጭ የሚመስሉ ድርጅቶች ሲፈጠሩ በየጊዜው አሳማኝ የሚሉትን ሐሳብ ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን፣ ብዙ ሰዎች የዚህ ሰለባ የሚሆኑት ገንዘብ ከመክፈላቸው በፊት ማጣራት የሚገባቸውን መረጃዎች ባለማጣራትና የማጭበርበር ስልት መሆኑን በውል ካለመረዳት ነው።

ብዙዎችን አጭበርብረው የሚሰወሩ ድርጅቶችም ይሁኑ ግለሰቦች፣ በየጊዜው ብቅ እያሉ የሚፈጽሙት የማጭበርበር ወንጀል የማኀበረሰቡን ጥንቃቄና ንቃት፣ እንዲሁም የመንግሥትን ቁጥጥር ክትትል የሚጠይቁ መሆናቸውን ደሊቨር የተሰኘ ድረ ገጽ ራስን ከኢ-ኮሜርስ አጭበርባሪዎች መጠበቅ ላይ ባወጣው ምክር አዘል ጽሑፍ ያትታል። ጽሑፉ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ በየጊዜው የኢ-ኮሜርስ ወይም የዲጂታል አጭበርባሪዎች ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች በብዛት ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ባለመውሰድ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ዓይነት የማጭበርበር ሥራዎች በተደጋጋሚ ሲፈፀሙና በስፋት ሲሰራጩ የመቆጣጠርና የመከታትል ኃላፊቱን መወጣት እንዳለበት ብዙዎች ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ራሱን ከእንዲህ ዓይነት የማጭበርበር ስልቶች የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።

እንደ Fias 777 ዓይነት ድርጅቶች ሲያጋጥሙ፣ ማንኛውም ሰው ሕጋዊነታቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ፣ በግልጽ የሚታወቅ አድራሻ የኃላፊዎችና የድርጅት ቢሮ፣ ስለሚሠራው ሥራ ሕጋዊነት፣ አዋጭነት ቀጣይነትና ደኅንነት የሚሉትንና በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ የተፈቀደና የታወቀ የሥራ ዘርፍ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል።

ሰለንሰለታማ የሽያጭና የአባላት ምልመላ የንግድ ሥራ የተጀመረው በ1990ዎቹ በአሜሪካ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶችን በቅርበት በመከታተልና ምርመራ በማድረግ፣ ሕጋዊ ያልሆነ ሥራ ላይ ያገኛቸውን ክስ ከመመሥረት እስከ ሥራ ማገድ የደረሰ እርምጃ ይወስዳል። ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች አገራት የተሰንሰራፋው ይህ ዓይነቱ ሥራ፣ ኢትዮጵያ ውሰጥ የማጭበርበሪያ ዘዴ መሆኑ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here