መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛግመል ሠርቆ አጎንብሶ

ግመል ሠርቆ አጎንብሶ

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ የነዳጅ እጥረት አንዱ ነው። ይህ በየወሩ ማለት በሚቻል መልኩ ለሳምንታት የሚዘልቅ ክስተት፣ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ የሚችልበትን የወር መገባደጃ መዳረሻን ተከትሎ የሚፈጠር እንደሆነ ይታያል።

የተሽከርካሪ ባለቤቶች ነዳጅ ለመቅዳት የሚያደርጉት ሰልፍ በመኪና ስለሆነ ይረዝማል እንጂ፣ በየቀኑ ለዳቦ ከሚሰለፉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እንደማይበልጥ የሚናገሩ አሉ። ምቹ ወንበር ላይ ተቀምጠው ወረፋቸውን እየተንፏቀቁ ከሚጠብቁት አሽከርካሪዎች ይልቅ፣ የነዳጅ እጥረቱ ባመጣው እጥረት ብርድና ዝናብ እየተከታተለባቸው በፀሐይም እየተንቃቁ የቀናቸውን የተወሰነውን ክፍል ትራንስፖርት በመጠበቅ የሚያሳልፉ የከተማ ነዋሪዎች ላይ ችግሩ ተባብሶ ይስተዋላል።

የነዳጅ ጭማሪን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ላይ የሚደረገው አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማኅበረሰቡን የሚያማርረው ሳያንስ፣ አሁንም ድጎማው ስለሚነሳ ጭማሪው በሦስት እርከን ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እንደሚካሄድ ተነግሯል። የዓለም ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ እንጂ ማሽቆልቆሉ ያልተለመደ ስለሆነ፣ ድጎማው ሳይነሳ በፊት ገዝተው ዋጋው ሲጨምር ለመቸብቸብ ጥድፊያም የያዙ አሉ።

በፊት በኮንትሮባንድ ጎረቤት አገራት ለመሸጥ አልያም እደላው የማይደርስባቸው የጠረፍ አካባቢ ለመውሰድ ነበር በድብቅ ገበያው ይደራ የነበረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጦርነት ሳቢያ ቦቴዎች እንዳይገቡ የተደረገባቸው አካባቢዎች መበራከታቸውን ተከትሎ፣ ወደ ቦታዎቹ በጄሪካን ጭምር ለማስተላለፍ ግመልና አህያ ጭምር ተዋናይ ሆነው ነበር።

ለማመን የሚያስቸግር የጀሪካን ቁጥር ተጠቅሶ በዱር በገደሉ እንዲሁም በየበረሃው ተሸሽጎ ተገኘ ሲባል ጉድ አስብሎም ነበር። ይህን ተከትሎ በከተማ ማደያዎች በጀሪካን ያለፈቃድ ምንም ዓይነት ነዳጅ እንዳይሸጥ ተደርጎም ነበር። ውጤታማነቱ ባይታወቅም፣ ለዳቦ ቤትና ለግንባታ ማሽኖች የሚውልን ነዳጅ አስፈቅደው መግዛት እንዲችሉ ቢደረግም፣ ምን ያህሉን ተጠቀሙበት? ምን ያህሉንስ በጥቁር ገበያ ሸጡት? የሚለውን ማወቁና መቆጣጠሩ ከባድ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

የጀሪካን ነዳጅ ኮንትሮባንዱ ሲገርመን አሁን ደግሞ ትልልቅ ቦቴዎች እየተደበቁ ነው የሚል ዜና ሰምተን አጀብ እያሰኘን ነው። አንድ ቦቴ ብቻ ሳይሆን 200 ቦቴዎች ተደብቀው ተገኙ የሚለው ዘገባ ያልተገኙና በየቦታው ተወሽቀው ያሉት ስንት ይሆኑ እያስባለ ነው። መኪና ከቆመበት ሰርቀው የሚሰወሩ ባሉበት አገር፣ የራሳቸውን መኪና ቦቴንም ቢሆን ለመደበቅ መቻላቸው ላያስገርም ይችላል።

ነዳጅ አገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ ሂደቱን የሚከታተል ስርዓት አገሪቷ መዘርጋት ባያስችላትም፣ ሰፊ ስለሆነች ተብሎ ሊተው ካልሆነ በስተቀር የሚጠፉት መርፌዎች አይደሉም። ሞተር ሳይክሎች ቦታቸውን ጠቋሚ ጂፒኤስ እንዲገጥሙ ያስገደደ መንግሥት፣ ቦቴ ተደብቆ አገኘሁ ማለቱ አድናቆት ነው ወይስ ውርደት ነው የሚያተርፍለት ያሉም ነበሩ።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች