በርካቶችን በአጭር የቀጨው ‹‹ውርጃ››

0
1530

የውብዳር ዓለማየሁ በአዲስ አበባ ከተማ በባለሀብት ቤት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። ውርጃን በተመለከተ የደረሰባቸውን ችግር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ከቤተሰቦች ጋር የተለያዩት በ11 ዓመታቸው ሲሆን፤ ከእለታት አንድ ቀን ተቀጥረው ከሚሠሩበት ቤት በደረሰባቸው የመደፈር ጥቃት ልጅ ለመጸነስ እንደተገደዱ ይናገራሉ።

ከሰው ቤት ተቀጥረው ስለሚሠሩና የመታዘዝ እንጂ እምብዛም ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን የመግለጽ እድሉን ስለማያገኙ ሰውነታቸው እንደለመዱት አልታዘዝ ሲላቸው፤ ምግብ አልበላቸው ሲል፤ ጸባያቸው ቅይርይር ሲልባቸው ግራ ተጋቡ። ይህም ሆኖ አርምሞን መርጠው በመቆየታቸው መጸነሳቸውን ያወቁት ከወር በኋላ ነበር።

ከወር በኋላ ተቀጥረው የሚሠሩበት የቤት እመቤት ሁኔታውን በመጠርጠራቸው የውብዳርን በጥያቄ ያፋጥጧቸው ጀመር። “ከማን ነው የጸነሽው? ጓደኛ አለሽ?….. አሁኑኑ ንገሪኝ” የቤቱ እመቤት ሁሌም ለየውብዳር የሚወረውሩት ጥያቄ ነበር።

የውብዳር ከዝምታ የዘለለ ሌላ ምላሽ ባይሰጡም፣ ለመናገር ግራ መጋባታቸውን ግን ሌትና ቀን የሚያነቡት እንባ ግን ሁኔታውን እንዲደብቁ አላገዛቸውም። ወዲህ ጽንሱ ቢወለድ እንኳ እንዴት እንደሚያሳድጉ በሌላ ጎን ደግሞ ለትዳር መበተን ምክንያት መሆናቸው ሕይወታቸውን በሀዘን እንዲሞላ አድርጎታል።

“ሳናጋባሽ የማንን ዲቃላ ይዘሽ መጣሽ?” የሚለው ቤተሰቦቻቸው ሲሰሙ የሚሉት ሥነ ልቦናን የሚጎዳ ምላሽ ድርብ ጭንቀታቸውም ሆኖ ሰንብቶ ነበር። የውብዳር ተረጋግተው በማሰብ ትዳርም ሳይበትኑ፤ ለቤተሰቦቻቸውም ሳይናገሩ የደረሰባቸውን ችግር ለማቃለል አሰቡ። ሐሳባቸውን የሚያሳኩበት ውሳኔያቸው፣ ተቀጥረው ከሚሠሩበት ቤት ጠፍተው በመውጣት ሳይፈልጉት የመጣባቸውን ፅንስ ማስወረድ እንደነበር አልሸሸጉም።

ፅንሱን ማስወረዳቸው ደግሞ በስጋቸውም በነፍሳቸውም ጥያቄ የሚያስነሳባቸው ሌላ ከባድ ፈተና ሆኖ ታያቸው። እንዲህ የተዘበራረቀ ሐሳብ መበራከቱ አእምሯቸውን ሊያፈነዳው ደርሶ እንደነበር የውብዳር በትውስታ ይናገራሉ።

ከውሳኔው በኋላ የተሰማቸው ውዝግብ፣ ነፍሰ ገዳይ ሆኜ ፈጣሪዬ ለሚጠይቀኝ ጥያቄ ምላሼ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ነበር። “እግዚአብሔር እንኳ አይጨክንብንም። ሰውን ከማጣላትና በቤተሰቦችም ተቀባይነትን ከማጣት ልጁ ይውረድ” ባለታሪኳ ለመጨረሻ ጊዜ የወሰኑት ውሳኔ ነው።

ከውሳኔያቸው በስተጀርባ “እውነት ይዘገያል እንጂ ተደብቆ አይቀርም” የሚለው አባባል ትውስ ይላቸውና ጎዳና ተዳዳሪ ሆነውም ቢሆን ልጃቸውን ወልደው ለማሳደግ ሌላ ውሳኔን ወሰኑ።

ይህ በባለታሪኳ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ስለታመነበት ተግባራዊ ሆነ። ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ተቀጥረው የሚሠሩበት ቤት ሰዎች በተኙበት በሩን በቀስታ ከፍተው ወጡና ቤተክርስቲያን ተጠልለው አደሩ።

በያዙት ብር የእለት ምግባቸውን እየበሉ ውሎና አዳራቸው በቤተክርስቲያን አጥር ተጠልለው ከሚኖሩ ጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ከሆነ ቀናት ቢቆጠሩም፤ ሰዎች ሲጠቋቆሙባቸው እና ብራቸው እያለቀ ሲሄድ ግን ወልደው ለማሳደግ ከወሰኑት የተሻለ ውሳኔ ማፈግፍግን እንደመረጡ ይናገራሉ።

በመጨረሻም፣ መድኃኒት ተጠቅመው ፅንሱን አስወርደው እንዳመማቸው በመናገር ወደ ቤተሰቦቻቸው ሂደው ማገገም እንዳለባቸው ከራሳቸው ጋር ተመካከሩ። የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን አቀላቅለው በመጠጣት ፅንሱን ለማውረድ ባደረጉት ውሳኔ ብርቱ ሕመም ተጋርጦባቸው በደረቅ ሌሊት መጮህ ጀመሩ።

ሙሉ አዳሩን ጠጣር ደም በማሕጸናቸው ሲፈሳቸው አድሮ በማግስቱ ያዩአቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጤና ጣቢያ እንደወሰዷቸውና በመጨረሻም ቤተሰብ ለመስማት እንደተገደዱ አልደበቁም።

የውብዳር ባደረጉት ድርጊት ማሕጸናቸው እንደተጎዳ ዶክተሮች ነግረዋቸው በመከታተል ላይ እንደሆኑና ከምንም በላይ ደግሞ የገደሉት ልጃቸው በሕሊናቸው እየመጣ የሚጣራቸው እስኪመስላቸው ድረስ በጸጸት እንደሚቃዡ የውስጣቸውን ሳይደብቁ ተናግረው፤ ውርጃን አውግዘዋል።

ሆን ተብሎም ይሁን በአጋጣሚ፣ ወይም በአስገዳጅ ሁኔታ በርካታ ሴቶች ውርጃ ይፈጽማሉ። በዚህም ከእናቶቻቸው ማሕጸን ዓለም ባሻገር ወደ ምድር የመምጣት እድል ከሽፎባቸው በአጭር የተቋጩ ሕፃናት ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህ ድርጊት በርካታ ግራና ቀኝ ጉዳቶችም እያስከተለ ይገኛል።

የመወለድ እድል ቢያገኙ ከራሳቸው አልፈው አገርን መጥቀም የሚችሉ ምሁራን በእናቶቻቸው ማህጸን እንደተቋጠሩ ይቀራሉ። ውርጃ የሚፈጽሙ እናቶች ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆንም ሕይወታቸውን እስከማጣት ይደርሳሉ።

ለውርጃ የተለያዩ ምክንያቶች ሲደረደሩ ይሰማል። ያልተፈለገ እርግዝና ከኑሮ ውድነት ጋር አለመጣጣም፤ የወሊድ መከላከያ አጠቃቀምና አስተማማኝ አለመሆን፤ በአስገድዶ መድፈር የሚመጣ እርግዝና፤ በአመጋገብ ምክንያት የፅንስ ጤናማ አለመሆን እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ለውርጃ መንስኤ ሆነው ይስተዋላሉ።

ቤት ውስጥ በሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሠሩ በርካታ ልጃገረዶች ባልጠበቁት ሁኔታና አጋጣሚ ክብረ ንጽህናቸውን አጥተዋል። ክብረ ንጽህናቸውን ከማጣትም በዘለለ ፅንስ ለማስወረድ ሲገደዱ ተስተውለዋል።

ውርጃ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አገራት እንደሚከናወንና ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንደመጣም ጥናቶች ያመላክታሉ። ተመሳሳይ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ በርካታ ነፍሰ ጡሮች በባህላዊ መንገድ ጽንስ ሲያስወርዱ ይስተዋላሉ።

ለአብነትም በጎንደር ከተማ ዙሪያ በ2014 በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሦስት ሺሕ 397 ውርጃ የተፈፀመ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ከጤና ባለሙያ ክትትል ውጭ በባህላዊ መድኃኒት መሆኑ ነው የተሰማው። እነዚህ ውርጃ ፈጽመዋል የተባሉት ነፍሰጡሮችም በጎንደር ዙሪያ ከሚገኙ ከ6 ሺሕ 481 ነፍሰጡር እናቶች ውስጥ ናቸው ተብሏል።

ከማስወረድ ወልዶ መጣል ይሻላል የሚሉ አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ከወለዱ በኋላ ወደማይታወቅ አገር ወስደው ሲጥሉ ይስተዋላሉ። አዲስ ማለዳ ወደ አማራ ክልል ተዘዋውራ በነበረበት ወቅት በሰሜን ወሎ ዞን ተኩለሽ ተብላ በምትጠራ ታዳጊ ከተማ ማን እንዳስቀመጠው የማይታወቅ የስድስት ወር ጨቅላ ሕጻን ከግለስብ አጥር ላይ ሲገኝ ተመልክታለች።

በሁኔታው የተደናገጡ ሲሳይ ጌታዬ የተባሉ የቤቱ ባለቤት በወቅቱ ለፖሊስ ባሳወቁት መሠረት፣ ፖሊስ ባደረገው ጥናትና ክትትል የሕጻኑ እናት ከሳምንት በኋላ በቁጥጥር ሥር ሆናለች።

ታዲያ የሕፃኑ እናት በፖሊስ ስትጠየቅ የሰጠችው ምላሽ ልጁን የወለድኩት ከአጎቴ ልጅ ጋር ባደረኩት የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው። ቤተሰብ ይህን ስላልፈቀደና ሊገድሉብን ስለሆነ ከሚሞት ማንም ያሳድገው ብዬ ነው የሚል ነበር።

ውርጃና ሃይማኖት
ውርጃን ዓለማዊ ሕግ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትም በጥብቅ ይቃወሙታል። በርካቶች ይህን ቢያውቁም ዓለማዊንም ሆነ ሃይማኖታዊ ሕጉን ሲተላለፉ ይስተዋላሉ።

ውርጃን የእስልምና ሃይማኖት አይፈቅድም የሚሉት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የእስልምና ሃይማኖት አጥኚና ተማራማሪ አደም ከሪም ናቸው። አደም እንደገለጹት ከሆነ በእስልምና ሃይማኖት ፅንስ ማስወረድ ይቅርና ከመጸነሱ በፊት የሚደረገው ከጋብቻ ውጭ የሆነ ግንኙነትም ፈጣሪ የማይፈቅደው ዝሙት ነው ብለዋል።

‹‹ብዙዎች ግን ከአላህ ፍርድ የሚያመልጡ እየመሰላቸው ጨለማን ተገን አድርገው ዝሙትን ሲፈጽሙ፤ ሳያስቡት ከእቅድ ውጭ የሆነ እርግዝና ይገጥማቸዋል። ስለዚህም ሕግን በመተላለፍ ነፍስንም ስጋን የሚጎዳ ድርጊት ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ።›› ሲሉ ነው አደም ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በተለይም ቅርብ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሰዎች በመሳሳት በሚያደርጉት ድንገታዊ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚጸነስ ፅንስ ተወልዶ እንዲያድግ በቤተሰብ በኩል ተቀባይነት ስለማያገኝ ሴቶች ለማስወረድ ሲገደዱ ይስተዋላል። በስጋ ዘመዳሞች መካከል ጽንስ ቢፈጠር እንኳ ፅንሱ መውረድ የለበትም ያሉት አደም፤ በርካቶች ግን ለዘመናት በድብቅ ይህን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ ነው ያሉት።

ገና ለገና ቤተሰብ አይፈቅድም፤ የሥጋ ዝምድና ይራራቃል እንዲሁም ይፈርሳል ተብሎ ሕይወት ማጥፋትን የእስልምና እምነትም አጥብቆ ይከለክላል ብለዋል አደም።

አላህ በመጀመሪያ የሰውን ልጅ ከመፍጠሩ በፊት ያዘጋጀለት ነገር ስላለና ፅንስን በፍቃድ ማውረድ በእስልምና ሃይማኖት አግባብ አይደለም ነው የተባለው።

በሕመም ውስጥ ያለች ነፍሰጡር ብትሆን እንኳ አላህ ምህረቱን እንዲልክላት መጸለይና በፈጣሪዋ መተማመን አለባት እንጂ፣ ስላመማት ጽንሱን ማውረድና ሙከራ ማድረግ ከእስልምና ሃይማኖት ውጭ ነው ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ ፅንስን ማስወረድም ሆነ፤ ከጋብቻ በፊት ግንኙነት ማድርግ ኃጢአት መሆኑን በአጽንኦት ስትሰብክ ትደመጣለች። ውርጃ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግ መሠረት የማይፈቀድ መሆኑንም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንተ መምህራን ይናገራሉ።

ውርጃ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት መሠረት የእግዚአብሔርን ሕግ መተላላፍ ስለሆነ ኃጢአት ነው ሲሉ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘዋወሩ የሚያስተምሩት አባ ገብረእግዚአብሔር ፈንቴ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቤተ ክርርስቲያን ውርጃን የማትቀበልበትን ምክንያትም ሲያስረዱም፤ ልጆች የፈጣሪ ስጦታዎች እንደሆኑ ስለምታስተምር ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን በዘመዳሞች መካከል የተጸነሰ ፅስን በተመለከተም በቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንኳን በሥጋ ዝምድና በአበልጅነት፤ በመንፈሳዊ ዝምድናም ግንኙት ማድረግ ክልክል እንደሆነ ሊቃውንቱ ገልጸዋል።

ከሰው ስህተት ከእንጨት ዝገት አይጠፋምና ስህተት ተፈጥሮ ከላይ በተጠቀሱት ዝምድናዎች መካከል ጽንስ ቢፈጠር እንኳ ማስወረድ እንደማይቻል ነው የተብራራው።

ይህ የሚሆነውም ውርጃ መፈጸሙ ዝሙት ከመሥራት በተጨማሪ ሌላ ኃጢአት ስለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ ይገኛልም ብለዋል። ከዘመድ ተጸነሰ በሚል ሰበብ ፅንስ ማስወረድ ወይም ማቋረጥ ከኃጢአት ላይ ኃጢአት መጨመር መሆኑን በማንሳት፣ አባ ገብረ እግዚአብሔር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሕጉ ምን ይላል?
ዓለማዊ የሕግ ድንጋጌዎች ደግሞ ውርጃን የሚደግፉበትና የማይደግፉበት ሁኔታ እንዳላቸው የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የፌዴራል የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 521 ውርጃ የሚፈቀድበት ሁኔታ መደንገጉን የሕግ ባለሙያው ብርሃኑ አያሌው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሕግ ባለሙያው እንደገለጹት ከሆነ፤ ውርጃ የሚፈቀደው ፅንሱ በፅንሱም ይሁን ለእናትየዋ ሕይወት አስጊ ደረጃ ላይ ከደረሰ፤ ጽንስ በአስገድዶ መድፈር ሲፈጠር፤ ጽንሱ የአፈጣጠር ችግር እንዳለበት ሲረጋገጥ ነው ብለዋል።

እንዲሁም፤ በስጋ ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል እርግዝና ከተፈጠረ፤ እርግዝናው የተከሰተው ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ሴቶች ከሆነ ለማስወረድ ሕጉ እንደሚፈቅድ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የውርጃ ጦስ
ውርጃ ልጅን ከማሳጣቱ በተጨማሪ በማሕጸን ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት እንደሚያስከትል ደግሞ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ውርጃ ከጤና ባለሙያዎች ውጭ በባህላዊ መንገድ ሲከናወን በማሕጸን ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚሉት ዶክተር አብዱላዚዝ ይማም ናቸው።

በተለያዩ ከፍላጎት ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠሩ እርግዝናዎችን ለማስወረድ ሴቶች ብዙውን ጊዜ በድብቅ በባህላዊ መንገድ ያስወርዳሉ ያሉ ሲሆን፤ ይህም በማሕጸን ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በወሊድ ወቅት ለምጥ መቸገርን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ባህላዊ የማስወረጃ መድኃኒቱ በማሕጸን አካባቢ ቁስለት ሊፈጠር ስለሚችል ይህም ቀስ በቀስ ኢንፌክሽ በመሆን ወደ ከባድ ሕመም ሊያመራ እንደሚችልም አብራርተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here