መነሻ ገጽአንደበት“ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው እንዳይጨምር፣ ስርዓቱ መቀየር አለበት”

“ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው እንዳይጨምር፣ ስርዓቱ መቀየር አለበት”

በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር)
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር)፣ መምህር እና ፖለቲከኛ ናቸው። አሁን ላይ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። መለስ ብለው ወደ ፖለቲካው የገቡበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ፣ ሰው ኢ ፍትሃዊ ነገር ሲፈጸም እየተመለከተ ዝም ማለት በምድር ወንጀል በሰማይም ኃጢአት ነው ብለው በጽኑ ስለሚያምኑ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ‹‹እንደሰው ኢ ፍትሃዊ ነገርን እያዩ ዝም ማለት አይገባም።›› የሚሉት በቃሉ፣ በግል የደረሰባቸው በደል ወይም ኢ ፍትሀዊ ነገር ባይኖርም፣ ከሚያዩትና ከሚሰሙት፣ በተለያዩ ወገኖች ላይ የሚደርሰው ጥፋት ግን የፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንዳስገደዳቸው ያስረዳሉ።

አዲስ ማለዳም ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዲሁም ወደፊቱን በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ከባልደራሱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ እንዴት ያዩታል?
በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። ሰዎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን እዚህ ግባ በማይባል በወረደ እሳቤ ይህ መፈጠሩ፤ በጣም ልብን ይሰብራል፤ ያሳዝናልም። በየትኛውም ዓለም ላይ ያልተከሰተ ነው በእኛ አገር እየሆነ ያለው። ሰው ታርዶ የሚበላበት፣ አርሶ የሚያድር ገበሬ ቦታህ አይደለም ተብሎ ዘር ማጥፋት የሚካሄድበት፣ ሕጻናት የሚታረዱበት፣ ሰው በማንነቱ ተፈርጆ እንዳያድግ በቢላ የሚቀደድበት ነው።

በዘር ፖለቲካ እና ጅምላ ጭፍጨፋ ላይ የሠራሁትና ያዘጋጀኋቸው የታተሙ ጽሑፎች አሉ። በየትም ያልተከሰተና ያልታየ ድርጊት ነው እኛ አገር የተፈጸመው። በጣም ያሳፍራል። እግዚአብሔር ጣልቃ ካልገባ በቀር እንዴት መስተካከል እንዳለበትም ግራ ነው የሚገባው። በጣም ልብን ይሰብራል።

እንደ ሰው ሆነህ ስታየው፣ በወገኖች ላይ የሚካሄደው ነገር በእኛ ላይ ያልሆነው እኛ በእነርሱ ቦታ ስላልተገኘን ብቻ ነው። እና ሁሉም ሰው ይህን ሊያወግዝ ይገባል። እኛ ፈልገን ባልመጣንበት በቋንቋ ወይም ብሔር ሰዎችን ፈርጆ እንዲህ ፍጅት መፈጸም፣ ከሰው አንሶ እንስሳ መሆን ነው። እንስሳትም ይህን አያደርጉም። አንዱ እንስሳ ሌላው ላይ እንዲህ ባለ መንገድ ጥቃት አይፈጽምም። በጠቅላላ አሳፋሪ፣ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ሁኔታ ነው። በየቀኑ የምሰማውና የማየው ነገር አእምሮዬን በጣም ነው ሰላም የሚነሳው።

ይህ በአገር ውስጥ ያለው እንዳለ ሆኖ በዙሪያም ኢትዮጵያ በጠላት እንደተከበበች ነው። በዚህ ላይስ ምን ዕይታ አላችሁ?
ይህ የመሪ ተክለ ሰውነት ያመጣብን ጣጣ ነው። አገሪቱ በየትኛውም ዘመን እንዲህ ያለ ክስተት አጋጥሟታል ብዬ እኔ አላምንም። ዶክተር ዐቢይ በየትኛውም ዘመን ከታዩ መሪዎች አንጻር፣ ለምንም የማይመጥን፣ አቅም የሌለውና አንደበት ብቻ ያለው፣ በተግባር ግን ልቡ ሌላ በሸፍጥና በተንኮል የተመላ መሪ ነው ብዬ ነው የማምነው።

አሁን አገሪቱ አንደኛ ተወርራ ነው ያለችው። ይህ ደግሞ የዓመታት ታሪክ ነው። ሱዳን አገሪቱን ወርራ የጎንደርን ክልል ይዛ ነው የተቀመጠችው። ያ አልበቃ ብሎ ደግሞ ትላንት አገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን በደቡብ ምዕራብ በኩል ወርራን ነው ያለችው። ሻዕቢያንም ስንወስድ፣ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ናት፣ የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው። በዛም በኩል ድንበር ተወሯል።

ይህም አልበቃ ብሎ፣ ድንበር ማስከበር ያልቻለና የሰዎችን መብት ማስጠበቅ ያልቻለ፣ የመጨረሻ ደካማና እዚህ ግባ ተብሎ ሊጠቀስ የማይችል፤ በታሪክ ተወቃሽ የሚሆን ስርዓት ነው አሁን ያለን። እና መንግሥት ብለን ልንቀበል የምንችለው መሠረታዊውን መስፈት ማሟላት ሲችል ነው ብዬ አምናለሁ። መንግሥትን መንግሥት የሚያሰኘውና በእኛም በኩል ቅቡልነት የምንሰጠው፣ አንደኛ የዜጎችን ወጥቶ መግባትና ሰላም መጠበቅ ሲችል ነው።

እኔ ከደሞዜ ግብር የምከፍለው ወይም ገበሬው ግብር የሚከፍለው፣ የእኛ ደኅንነት ሲጠበቅ ነው። እንጂ እነሱ እንዲንሸራሸሩ ወይም ከአገር አገር ጉብኝት እንዲያደርጉ አይደለም። እድገትን ስትወስድ፣ መሠረተ ልማት ማሟላትና የመሳሰሉት ኹለተኛ ናቸው። መጀመሪያ የዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ነው። ይህን ማድረግ አልቻለም። ባለፉት አራት ዓመታት በየአካባቢው ከፍተኛ የሆነ እልቂትና ሰቆቃ እየተፈጸመ ነው።

ኹለተኛው ደግሞ አገርን ዳር ድንበር መጠበቅ ነው። ግን መጠበቅ አልቻለም። ዳር ድንበር እየጠበቁ ያሉት ሚሊሻዎች ናቸው። ወታደር ዋና አገልግሎቱ ድንበር መጠበቅ ነው። ይህን ማድረግ ያልቻለ፣ መንግሥት ብለህ ልትቀበለው የማትችለው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አምባገነኖችን የመቀበልና የማሳደግ ባህሪ ስላለው ነው እንጂ፣ አንድ ወር መቀመጥ የማይችል፤ ሊወገድ የሚገባ መንግሥት ነው ብዬ ነው የማምነው።

የኑሮ ውድነቱን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን፣ የአገር ድንበር መጣሱን ስንወስድ፤ በዛም ላይ ሰው በረሀብ እየሞተ ነው። እናም እንዲህ ይህን ሠራ የማትለው፣ በወሬና ውሸት የተሞላ ስርዓት ነው። እና አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነው፤ ይህን ነው ማለት የምችለው።

አንዳንዶች መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚል ሐሣብ ያነሳሉ። ለደረሱ ጥፋቶችም የውጪ ኃይሎች እጅ አለበት ይላሉ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
የስርዓቱ አንዱ መገለጫ ይህ ነው፤ ውሸት። ዝም ብሎ ተረት እየፈበረኩ ሕዝብን ለማታለል መሞከር፣ ይህ ያለፈበት መላምት ነው ብዬ ነው የማምነው። ለአራት ዓመት ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ወያኔ ነው። የወያኔ ቅጥረኞች እየተባለ ነው የሚነገረው።

ወያኔ በመተከል ወይም በወለጋ በኩል መጥቶ ሰዎችን ለማስታጠቅ የሚችልበት ስፖንሰር ወይም አቅም እንደሌለው ይታወቃል። ግን ሁልጊዜ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው እሱ ነው። ልክ እንደ ማስፈራሪያ፣ ግብጽ ናት፣ ወያኔ ነው ይባላል። የራሱን ድክመት መቀበል ያልቻለና ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀሙት ስትራቴጂ ነው፤ ትላንትም የሚጠቀሙት ይህን ነው፤ ዛሬም እየተጠቀሙ ያሉት ነው።

አልቻልኩም ማለት ትልቅነት ነው። የሕዝብ ተወካዮችን ወይም እንደራሴዎችን ሰብስቦ በቃ አልቻልኩም ብሎ የሚመለከተው አካል ሥልጣን እንዲወስድ ማድረግ ነው። እንጂ እንደ ምክንያት የሚቀርቡት ነገሮች ውሃ አይቋጥሩም። ይህን ደግሞ ወያኔም ሲያደርገው የነበረ ነው። በወያኔ ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት። እና እነሱን እነዛ ይጠቀሙ የነበረውን ስትራቴጂ ነው እየተጠቀሙ ያሉት። ይህም ውሃ የማይቋጥር፣ ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት ነው የሚያሳየው እንጂ እንደ በቂ ምክንያት የሚጠቀስ አይደለም።

ብሔርን መሠረት በማድረግ ንጹሐን ላይ የሚፈጸሙ ጅምላ ጭፍጨፋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው። እነዚህንስ ወደፊት ማስቆም ይቻላል ብለው ያስባሉ?
መንግሥት ሕዝቡን ከዚህ ሊያስጥል የሚችል አይደለም። መንግሥት ይህን ለማድረግ አቅም አጥሮታል የሚል እምነት በመሠረቱ የለኝም። የዘር ማጥፋቱ እንቅስቃሴ ራሱ መንግሥታዊ ስትራቴጂ ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዚህም አንዳንድ ማሳያዎችን ማሳየት እችላለሁ። ለምሳሌ ኦነግ ለሀምሳ ዓመት አካባቢ አንድ ወረዳ እንኳ ማስለቀቅ ያልቻሉ፣ በኤርትራ በረሃ ላይ ፍየል ሲጠብቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው። እነሱ ትጥቅ ሳይፈቱ መጥተው፣ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያደረጉ እነ ለማ መገረሳ፣ ወርቅነህ ገበየሁ፤ ኤርትራ ድረስ ሄደው ነው ተደራድረው ያስፈቷቸው። እና ትጥቅ እንዲፈቱ አላደረጉም።

- ይከተሉን -Social Media

መጨረሻ ላይ እንደውም ማን ፈቺ ማን አስፈቺ አለ ነው ያለው። ይህን ሆነ ብለው ኦሮሚያ ላይ አሰማርተው፣ የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡና አካባቢውን ከኦሮሚኛ ውጪ ተናጋሪ ከሆኑ ሰዎች እንዲጸዳ ለማድረግ የተጠቀሙበት የፖለቲካ ስራቴጂ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ተንኮል፣ ሸፍጥ እና ቁማር እንደሆነ መሪዎቹ ራሱ እየተናገሩ ነው።

ስለዚህ፣ የሌሎችን ብሔረሰቦች እና የሌሎች ኢትዮጵያዊያን እሳቤ በፖለቲካ ተንኮል ጠምዝዘው አካባቢውን ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች እንዲለቁ ያደረጉበት ስትራቴጂ ነው። እንጂ መንግሥት ይህን ማጽዳት ሳይችል ቀርቶ አይደለም። መንግሥት በመቶ ዓመት ታሪክ ተገንብቶ የማያውቅ ሠራዊት አለን ብሎ ሲፎክር ነው የነበረው።

የአማራ ልዩ ኃይል ገብቼ ይህን ጥቃት ልመክት ሲል አልተፈቀደለትም። እና ይህ አለመቻል ሳይሆን ፈቃደኝነት ስለሌለ ነው። አለመቻል ሳይሆን የሚደረገው ወይም የሚሰነዘረው ጥቃት መንግሥት መር ስለሆነ ነው እንጂ መንግሥት ስላልቻለ አይደለም። ሁለቱ ተለይቶ መታየት አለበት ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ ይህን ለመመከት ሰው መንግሥትን መጠበቅ የለበትም ብዬ ነው የማምነው፤ መደራጀት ነው ያለበት። ተደራጅቶ ይህን ዘር ማጥፋት ሕዝቡ መመከት ነው ያለበት ነው የምለው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለወደፊት ገና ከዚህ በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል እያሉ የሚናገሩ አሉ። እርስዎስ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ሕዝቡ እስካልተደረጀ ደረስ ይህ ነገር መቀጠሉ አይቀርም። የወጡ መረጃዎችም ጠቋሚ ናቸው። የመንግሥት ባለሥልጣት እጃቸው እንዳለበትኮ የጥቃት ሰለባዎች በተለያየ መንገድ ሪፖርት አድርገዋል። ምዕራብ ወለጋ የተከሰተውን ክስተት ስናነሳ፣ ታጣቂዎች ራሱ የመንግሥት ባለሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት እንደጠቆሙ መረጃዎች እያሳዩ ነው።

ኦነግን “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የዳቦ ስም ሰጥቶ ያስቀመጠው ኃይል ጥቃት እንዲፈጽም ያደረገው መንግሥት ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉበት ደግሞ ተጠቂዎች ሪፖርት እያደረጉ ነው፤ የተለያዩ ሚድያዎች ላይ እየቀረቡ ነው። የጸጥታ ኃይሉ እንዲወጣ አድርገው ኦነግ ሸኔ ፍሪዳ ታርዶለት እንዲገባ ነው ያደረጉት። ይህ በሚድያ ላይ የወጣ፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ያቀረቡት ነው።

ስለዚህ ይህ ጥቃት ነገም ይቀጥላል ወይ፤ አዎን ነው የምለው። መደረግ ያለበት፤ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን መጠበቅ ነው አለበት ብዬ ነው የማምነው። እንጂ የመንግሥት እጅ እንዳለበትና መንግሥት መር እንደሆነ የአደባባይ እውነት ነው።

በዚህ አራት ዓመት እየተበራከተ ከመጣው ንጹሐን ላይ ከሚፈጸም ጥቃት አንጻር፣ ወንጀለኛ ለሕግ ይቀርባል ሲባል እንጂ ሲቀርብ አይስተዋልም። ይህ የክስ ጉዳይ በአገርም ሆነ በዓለማቀፍ ችሎት የመታየት እድሉ ምን ያህል ነው ይላሉ?
ይህን ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንም፣ ወደ ዓለማቀፍ ሕግ መወሰኛ መቅረብ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ መኖሩንም ሰምቻለሁ። ውስጥ ያለነውም መረጃዎችን አጠናክሮ፣ ውጪ ያለውም አካል እንደዛው አድርጎ ወደ ዓለምአቀፍ የፍርድ መድረክ መቅረብ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ይህ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መሆኑ ይቀራል ብዬ አላስብም።

ምክንያቱም ተፈጥሮ ራሱ መልስ ይሰጣል። ዛሬ ሥልጣንና ወንበር ይዣለሁ ብሎ ቢፏልልም፣ በታሪካችንም ባየነው እውነታ፣ መልስ የሚያገኝበት ሁኔታ ይኖራል። ግን ተጨማሪ ሕዝብ እንዳያልቅ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን መመከት አለበት ነው። እንጂ እነሱ ፍርድ ማግኘታቸው ይቀራል ብዬ አልገምትም። በአገር ውስጥም ሆነ በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም የፈሰሰ ደም ዝም ብሎ አይቀርም። የአቤል ደም በእግዚአብሔር ደጅ ትጮኽ ነበር፣ እንኳንና ይህን ያህል ደም በግፍ ፈስሶ። እና እሱ የሚቀር አይመስለኝም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

የጥቃቱ ሰለባዎች ከሆኑት መካከል በሕይወት የተረፉት ተፈናቅለው በተለያየ አካባቢ ይገኛሉ። በዚህ ላይም የተወሰነ ጊዜ ይጮኽና ተመልሶ ይረሳል፤ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ለአራት ዓመትም እንደዛው ነበር። እነርሱ አልፎ አልፎ ድርጊቱም ይፈጽማል፣ እኛም እንጮኽና እንመለሳለን። ይህ መጮኽና ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መቀጠል አለበት። ተፈናቃዮችና የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች፣ መንግሥት እንደ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ መጠለያ እና መሠረታዊ ቁሳቁስ ማሟላት እንኳ አልቻለም። ምክንያቱም መጀመሪያውንም ሲፈናቀሉ ስላልተፈለጉና አካባቢውን ማጽዳት ስለተፈለገ፤ አካባቢውን ‹ሆሞጂንየስ› ማድረግ ስለተፈለገ ነው።

ስለዚህ፣ ለእነሱ የሚደረግ እንክብካቤ አለመኖሩ መንግሥት እጁ እንዳለበትም አንዱ ማሳያ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ታድያ ነገ እንዲህ ያለ ክስተት ሊከሰት ስለሚችል፣ ያለው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴና እንቢተኝነት ቀጥሎ ስርዓቱን መቀየር አለበት ብዬ ነው የማምነው። ነገም የተፈናቃይ ቁጥር እንዳይጨምርና ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው እንዳይጨምር፣ ስርዓቱ መቀየር አለበት። ያ እንዲሆን ደግሞ አሁን የተፈጠረው እንቅስቃሴና ሕዝባዊ አመጽ ተጠናክሮ መቀጠል ነው ያለበት። አንደኛ አማራጭ የማደርገው እሱን ነው።

ኹለተኛ መንግሥት ማስተዳደር ስላልቻለ ሥልጣን ማስረከብ አለበት። ሦስተኛ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዳለ ሁሉ፣ በኦሮሚያ ክልል አማራ ልዩ ዞኖች እንዲቋቋሙና ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ የሕዝባዊ አመጹ አንዱ መፈክርና ዓላማ መሆን አለበት። ይህ እስካልተሳካ ድረስ ሕዝባዊ አመጹ መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ።

አለበለዚያ ነገም እነሱ ይገድላሉ፣ እኛም እንጮኽና ቤታችን እንገባለን፤ እንዲህ እያልን እየቀጠልን ነው የምንሄደው። ይህ እንዳይሆን ሕዝባዊ አመጹ መቀጠል አለበት፣ መንግሥት መልስ እስከሚሰጥ ወይም ሥልጣኑን እስከሚያስረክብ ድረስ ወይም በአመጹ የሚነሱ እሳቤዎች መሬት እስካልረገጡ ድረስ፤ አመጹ እንዲቀጥል ነው እንደ ምክረ ሐሣብ የማቀርበው።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰብ አንቂዎችና ጋዜጠኞች እስርና አፈና ይስተዋላል። ይህን በተመለከተስ ምን የሚሉት አለ?
ማኅበረሰብ አንቂዎችና ንቁ ተሳተፊዎችን ማፈን ከተጀመረ ቆይቷል። የተወሰኑ ተፈትተዋል፣ የተወሰኑ እስከ አሁን ድረስ አልተለቀቁም። ይህ ያለውን እንቅስቃሴና ሕዝባዊ አመጹን ለማፈን መንግሥት የሚጠቀምበት መንገድ ነው። ሰዎችን በመግደል፣ በማሰር እና በማሰቃየት ምንም ዓይነት መፍትሄ አይመጣም። ስርዓቱ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች አስተናግዶ፣ የሰዎችን ደኅንነት ጠብቆ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥረት እስካላደረገ ድረስ፣ እነዚህ ነገሮች ይቀጥላሉ።

ይህ በወያኔ ጊዜም የነበረ ክስተት ነው። እነዚህ ነገሮች የሕዝቡን እንቅስቃሴና አመጽ ሊያስቆሙት አልቻሉም። አሁንም ብልጽግና ማድረጉ እንደማይቀር ጥያቄ የለውም። ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ እንቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጹ መቀጠል አለበት።

መንግሥት ደግሞ ይህን እንቅስቃሴ በጽሑፍም፣ በንግግርም፣ በተቃውሞም ሊመሩ የሚችሉ ኃይሎችን ማሰርና መግደል ሊኖር ይችላል። ይህ የትግሉ አንዱ ገጽታ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይህ ደግሞ ትግሉን ወደኋላ አይጎትተውም፤ ያባብሰዋል እንጂ። ይህን እንደ መፍትሄ አድርጎ ባይወስደው ጥሩ ነው፤ እንደዛ ካደረገው ግን የመውረጃውንና የፍጻሜውን ቀን ያቀርበዋል እንጂ ሰዎችን በማሰር የሚመጣ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም።

ፋኖን በተመለከተ መንግሥት እገሌ ትክክለኛ ፋኖ ነው እገሌ ደግሞ አይደለም የሚል ነገር ያነሳል። በዚህ ላይ ያለውን የመንግሥትን ውሳኔን እንዴት ያዩታል?
ፋኖን በሚመለከት በፓርቲያችን መግለጫ አውጥተናል። ፋኖ ምንም ደሞዝ ሳይከፈለው፣ ምንም ትጥቅ ከመንግሥት ሳይጠይቅ ስለአገርና ወገን ብሎ የተሰዋ ደሙን ያፈሰሰና የሚታገል ኃይል ነው። ይህን ኃይል ለእኔ ለነገ የፖለቲካ ሸፍጥ እንቅስቃሴ እንቅፋት ይሆንብኛል ብሎ ስላመነ ነው የብልጽግና ፓርቲ የሚያሳድዳቸው።

- ይከተሉን -Social Media

ይህን በጽኑ አውግዘናል፤ እናወግዛለንም። በፋኖ ላይ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለምንድን ነው ኦሮሚያ ኦነግ ሸኔ ላይ የማያደርገው? ፋኖ የትኞቹ ንጹሐን ዜጎች ላይ ነው ይህን ጥቃት የፈጸመው? በተከታታይ ንጹሐን ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት የፈጸመው ኦነግ ሸኔ እና በቤኒሻንጉል የጉምዝ አማጺ ነው። ኃይሉን ለምን እነርሱ ላይ አያደርግም? ፋኖ የትኛውን ጥፋት ሠርቶ ነው?
ፋኖ ላይ የሚደረገው ወይም ሊደረግ የታሰበው ጥፋት፣ ነገ ለሚፈጽመው ሴራ ተገዳዳሪ ኃይል እንዳይሆን ታስቦ ነው። እና ይህን ስንቃወም ነበር፤ አሁንም እንቃወማለን።

ባህርዳር ከተማ ላይ የተጣለ ቦምብን ከፋኖ ጋር በማያያዝ ተጠያቂ የሚያደርጉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ይህ ፋኖን ለማጥቃት የሚደረግ አንዱ ስትራቴጂ ነው። ሽብርተኛ ወይም ጥፋተኛ ለማድረግ ቤት ውስጥ ፍተሻ ሲያደርጉ ራሱ ቦንብ ተገኘ፣ ሽጉጥ ተገኘ እያሉ ሰውየውን ወንጀለኛ ለማድረግ የሚያደርጉት የሥም ማጥፋት ዘመቻ አለ።

ፋኖ በየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ጥቃት የሚያደርስ ኃይል እንዳልሆነ ይታወቃል። ግን ፋኖን ጥላሸት ለመቀባት መንግሥት የሚጠቀመው ስትራቴጂ ነው። ይህን ደግሞ ወያኔም ሲጠቀምበት ነበር። ታክሲ ላይ ሁሉ ቦንብ እያፈነዳ ኦነግን ወንጀለኛ ለማድረግ፣ ኦሮሞ ሕዝብ እንዲሸማቀቅ ሆነ ብሎ ያደርጋል። በአማራ ክልል እንደዚሁ እያፈነዳ ግንቦት ሰባት ነው ያደረገው፣ የአማራ አርበኞች ናቸው እያለ ሥም ያጠፋ ነበር።

ይህ ገዢው ስርዓት የሚቀናቀኑትን ለማሸማቀቅ፣ ማኅበረሰቡም አብሮ እንዲያወግዝለት የሚጠቀምበት ስትራቴጂ ነው። ይህ ደግሞ የተበላበት ነው። ፋኖ ቦንም ማፈንዳት አይደለም ምንም ዓይነት ሕገ ወጥ ድርጊት ውስጥ እንደማይሳተፍ ይታወቃል። ይህን ደግሞ መንግሥት ራሱ ያውቃል። ግን ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆምና እነዚህ ነጻ አርበኞችና ታጋዮች ጥላሸት ለመቀባት የሚጠቀምት ስትራቴጂ ነው። ይህን ሕዝቡም ያውቃል።

ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨተርሲቲዎች ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። በእነሱም ላይ እስር ተፈጽሞ አሁን ላይ ዋስትና የተጠየቁ አሉ። ይህን እንዴት ያዩታል?
ይህም ስህተት ነው። የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከ1960ዎቹ ጀምሮ መሬት ለአራሹ የሚል እንቅስቃሴ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአብዛኛው የሚያነሱት ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ ነው። አሁንም አትግደሉን፣ ንጹሐን ገበሬዎች አይገደሉ ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት፤ አይደለም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪ፤ ሰው ሆኖ የተፈጠረ ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነው። አትግደሉን ብሎ መውጣት በጣም ተገቢና ለዜጎች ተቆርቋሪነትን የሚያሳይ ነው።

መንግሥት ይህን አዳምጦ መልስ መስጠት ሲገባው፣ እነርሱን አሳድዶ ማሰር ትግሉን ወደኋላ አይመልሰውም፤ እንደገና እያቀጣጠለ ነው የሚሄደው። በዩኒቨርሲቲዎች ያለው እንቅስቃሴ በጣም ተገቢ ነው፣ ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ይህን እንቅስቃሴ ሊደግፉ ይገባል ብዬ አምናለሁ። የሚደረገው አፈና ግን ትግሉን ወደኋላ ይጎትተዋል የሚል እምነት የለኝም። በተማሪዎቹ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ግን ፍጹም ስህተት ነው፣ አምባገነን ስርዓት መገለጫም ስለሆነ፤ ያንን ነው እያሳዩ ያሉት።

አገራዊ ምክክሩን በሚመለከት ምን ተስፋ ያደርጋሉ? አሁን ያለውን አካሄድስ እንዴት ትገመግሙታላችሁ?
ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፤ እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ። አሁንም ሕዝብን ለማታለል ወይም የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የተያዘ እሳቤ እንጂ በምክክሩ መፍትሄ ይመጣል የሚል እምነት የለንም።

ለምን ቢባል፣ ምክክሩ ይካሄድ ከተባለ፣ አንዱ ተደራዳሪ ሆኖ መቅረብ ያለበት ራሱ ብልጽግና ፓርቲ ነው። ብልጽግና ፓርቲ ራሱ ፕሮግራሙን አዘጋጅቶ፣ ራሱ አስተዳዳሪ ሆኖ ሌሎች ገለልተኛ የሆኑ ግለሰቦች/አደራዳሪ አካላት በሌለበት ሁኔታ፣ ብልጽግና ራሱ ደጋሽ፣ ራሱ ጋባዥ ሆኖ በሚደረግ ድርድር መፍትሄ ይመጣል ብለን አናምንም።

መፍትሄ የምትሉት ምንድን ነው?
የመጀመሪያው፣ መንግሥት ሥልጣን ማስረከብ አለበት። ለአገሪቱ ሰላም አለመሆን ዋና ምክንያት መንግሥት ነው። ስለዚህ አገሪቱ ሰላም እንድትሆን መንግሥት ሥልጣኑን ማስረከብ መቻል አለበት።

ቀጥሎ የጎሳ ፖለቲካ ፍለስፍና መወገድ አለበት። ሕገመንግሥቱም መቀየር አለበት። ሕገ መንግሥቱ ሰዎች ተዘዋውረው፣ አገሬ ብለው የሚኖሩበትና ሀብት የሚያፈሩበትን ስርዓት የሚደግፍ አይደለም። ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ስርዓቱ ከመቀየሩ በፊት ግን ይህን ማድረግ የሚችል ኃይል ወይም አስተዳደር እንዲኖር ስርዓቱ መቀየር አለበት። ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ሁሌም ግጭትና መጋደል አለ።

የፓርቲያችሁ አሁናዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል፣ እንደ ፓርቲስ ምን አቅዳችኋል?
እስክንድር አሁን የዘር ማጥፋቱን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እያሳወቀ ነው። ከደጋፊዎች ጋር የተለያዩ ውይይትና ስብሰባዎች እያደረገ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ ይመጣል ብለን ነው የምናስበው።

እኛም አገራዊ ፓርቲ ለመሆን ከነባሩ የጠቅላላ ጉባኤ ጋር ስብሰባ ካደረግን በኋላ፣ በቅርቡ አገራዊ ፓርቲ እንሆናለን። ለዛም የሚስፈልገውን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።

ከዛ ውጪ ሕዝቡ አማራ በሚደርስበት ጥቃት ላይ፤ ለምሳሌ የጉራጌ ማኅበረሰብ ወጣቶች “የአማራ ደም ደማችን ነው” ብለው ተቃውሞ አሰምተዋል። የጎሳ ፖለቲካ አንዱ ሲጠቃ ሌላው እንዳይቆም ከፋፍለህ ግዛ ዓይነት የነበረውን እንቅስቃሴ ነው፣ ወያኔም ሲጠቀምበት የነበረውን ነው ብልጽግናም እየተጠቀመ ያለው። ስለዚህ ሳንከፋፈል ማንኛውም ዜጋ ጥቃት ሲደርስበት፣ ሁላችንም ለሁሉም ድምጽ ልንሆን ይገባል።

ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምጽ ሊሆን ይገባል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊም ለአንድ ኢትዮጵያዊ ድምጽ ሊሆን ያሻል። በብሔር መከፋፈሉን ትተን በየትኛውም አካባቢ ለሚደርስ ጥቃት፣ ማንም ይጠቃ፣ ድምጽ መሆን ይገባል። በጋራ ለተጠቂዎች ድምጽ እንሁን፣ ተደራጅተን ደግሞ ስርዓቱን እንቀይር ነው የምንለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች